ፈልግ

የአሌፖ ከተማ ጥቃት ደርሶባት፣        የአሌፖ ከተማ ጥቃት ደርሶባት፣  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሶርያን በጸሎት እንድናስታውሳት ጥሪ አቀረቡ።

በጦርነት አደጋ በርካታ ዜጎቿ በመከራ እና ስደት ላይ የሚገኝባትን ሶርያ በጸሎታችን እንድናስታውሳት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ አቅርበዋል። በሶርያ ውስጥ ጦርነት ባስከተለው አደጋ በርካታ ቤተሰቦች፣ አዛውንት እና ሕጻናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን እና ለስደት መዳረጋቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮች አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ባቀረቡት የሕብረት ጸሎት አስታውሰዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሰማዕታት አገር በሆነች ሶርያ ከዓመታት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ለሞት መዳረጉን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ጥሪያቸውን ያቀረቡት የካቲት 1/2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ወቅት መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ንግግር በሰሜናዊ ምዕራብ የሶርያ ክፍለ ሀገር በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በርካታ ቤተሰቦች የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የነፍስ አድን እርዳታውን እዲያቀርብ ተማጸነው ጦርነቱን በማካኸድ ላይ የሚገኙት ወገኖች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በማመቻቸት፣ የጋራ ውይይቶችን እና ድርድሮችን በማድረግ በሃገሪቱ ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መሰደድ እና የንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲያበቃ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የካቲት 4/2012 ዓ. ም. የደረሰን ዜና እንዳስገነዘበው፣ በሶርያ፣ ኢድሊብ ግዛት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጋ ሕዝብ መፈናቀን ምክንያት የሆነውን እና በሩሲያ የሚታገዝ የሶርያ ጦር ኃይል እያካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚወያይ ልዑክ ወደ ሞስኮ የምትልክ መሆኗን ቱርክ አስታውቃለች።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳስታወቁት ከኢድሊብ ግዛት የተፈናቀሉ የሶርያ ዜጎችን ለማቋቋም የጀርመን መንግሥት 40 ሚሊዮን ዩሮ በእርዳታ መስጠቷን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እንደገለጸው፣ በአካባቢው ጦርነት ከተጀመረ ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ያልታየ የሕዝብ መፈናቀል ባለፉት አሥር ሳምንታት ብቻ መከሰቱን ገልጾ፣ አሁንም ቢሆን የበርካታ ሕዝብ መሸሸጊያ በሆነች በኢድሊብ ከተማ ጦርነቱ ከፍተኛ የሕይወት ጥፋት ሊያስከትል ይችላል ብሏል።

በሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች የሚታገዝ የሶርያ መንግሥት ጦር ኃይል በሃገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ግዛቶች በሆኑት የኢድሊብ እና አሌፖ ከተሞች ባደረሰው ጥቃት በርካታ ቤተሰቦች ወደ ቱርክ ድንበር አካባቢ ሄደው መስፈራቸው ታውቋል። በሶርያ የመንግሥት ተቀናቃኝ አማጽያንን ስታግዝ የቆየች ቱርክ ተጨማሪ የሶርያ ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ መቸገሯን አስታውቃለች።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
12 February 2020, 15:32