ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  

“የገዳም ሕይወት ማለት በሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር መምረጥ ማለት ነው!”

ሕይወታቸውን ለየት ባለ መልኩ በማዘጋጀት መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር መስዋዕት አድርገው ያቀረቡ ቄሳውስት ገዳማዊያን/ዊያት፣ ካህናት እና ደናግላንን በማሰብ ጸሎት የሚደረግበት 24ኛው ዓለም አቀፍ ቀን በጥር 24/2012 ዓ.ም በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ 24ኛው ዓለም አቀፍ ሕይወታቸውን ለየት ላለ መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር መስዋዕት አድርገው ያቀረቡ ቄሳውስት ገዳማዊያን/ዊያት፣ ካህናት እና ደናግላንን በማሰብ ጸሎት የሚደረግበት እለት የዋዜማ ቅዳሴ በጥር 23/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “የገዳም ሕይወት መኖር ማለት በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር መምረጥ ማለት ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን

“ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋል ”(ሉቃ 2፡30)። እነዚህ ቃላት “ ጻድቅና ትጒሕ” ሰው ነው ብሎ ቅዱስ ወንጌል ያቀረበው የስምዖን ቃላት ናቸው። በዚያን ቀን በቤተመቅደስ ውስጥ ካሉ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን እንደ አዳኝ አድርጎ የተመለከተው እርሱ ብቻ ነው። ምን ታይቶት ይሆን? እርሱ ያየው አንድ ትንሽ ልጅ: ለጥቃት ተጋላጭ የሆነ ትንሽዬ ልጅ፣ እንደ ማንኛው ተራ ሕጻን የሆነ ልጅ ነበር የተመለከተው። ነገር ግን በእርሱ ደኅንነትን አየ፣ የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። በእጁ ይዞ በመውሰድ አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በእምነት ተረድቷል። እሱ ስምዖን አሁን በሰላም ባሪያህን አሰናብተው በማለት ከህይወት የበለጠ ዋጋ ያለው ጸጋን አየ (መዝ 63፡ 4) ከእዚህ በላይ የሚጠብቀው ሌላ ምንም ነገር አልነበረም።

ውድ የተቀደሰ ሕይወት የምትኖሩ ወንድሞች እና እህቶች ፣ እናንተ በዓለም ውስጥ ካሉ ውድ ነገሮች ሁሉ የላቀ ዋጋ ያለውን ውድ ነገር የተመለከታችሁ ወንዶች እና ሴቶች ናችሁ። እናም እንደ ንብረት የማፍራት፣ ቤተሰብ የመመስረት ያሉ ውድ ነገሮችን ከኋላችሁ ትታችሁ ይህንን ሕይወት መረጣችሁ። ይህንን ለምን አደረጋችሁ? ይህንን ያደረጋችሁት ደግሞ በክርስቶስ ፍቅር ስለተወሰዳችሁ ነው፣ በእሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ አይታችሁ ቀሪውን ነገር ተዋችሁ። መንፈሳዊ ሕይወት የሃይማኖት ሕይወት ራዕይ ነው። በእውነቱ በህይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን ማየት ማለት ነው። ልክ እንደ ስምዖን የጌታን ስጦታ በተከፈተ እጅ መቀበል ማለት ነው። የተቀደሱ ወንዶችና ሴቶች ዓይኖች የሚያዩት ይህንን ነው፣ የእግዚአብሔር ፀጋ በእጃቸው ላይ ይፈሳል። መንፈሳዊ ሕይወት የሚኖሩ ገዳማዊያን/ዊያት በየቀኑ ራሱን ወይም ራሷን የሚመለከቱት “ሁሉም ነገር ስጦታ ነው ፣ ሁሉም ጸጋ ነው”በሚለው መልኩ ነው። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ይህንን የገዳም ሕይወት ለመኖር የተገባን ሰዎች አይደለንም ነበር፣ ነገር ግን ከእሱ የተቀበልነው የፍቅር ስጦታ ነው።

ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋል። በእየለቱ የማታ ጸሎት በምናድርግበት ወቅት የምንደግማቸው ቃላት ናቸው። እነዚህን ቃላት በመጠቀም እና በእነዚህ ቃላት አማካይነት “ጌታ ሆይ ደህንነቴ የሚመጣው ከአንተ ነው፣ እጆቼ ባዶ አይደሉም ነገር ግን በጸጋህ ተሞልተዋል” በማለት ቀናችንን እናጠናቅቃለን። ጸጋን እንዴት መመልከት እንደሚቻል ማወቁ በራሱ መነሻ ነጥብ ነው። ወደኋላ በመመልከት የራስን ታሪክ እንደገና በማንበብ እና የእግዚአብሔርን ታማኝ የሆነ ስጦታ እዚያ መመልከት፣ በህይወት ውስጥ የሚከሰቱትን ታላላቅ ጊዜያት ብቻ ሳይሆን፣ የእኛንም ደካማነት እና ድክመቶች መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው። ፈታኙ ዲያብሎስ “ድህነታችንን” ነው የሚመለከተው ባዶ በሆነው እጆቻችን ላይ ያተኩራል “በእነዚያ ሁሉ ዓመታት የተሻሉ ጊዜያት አልነበሩህም፣ ማሳከት የሚገባህን ነገር አላከናወንክም፣ እንድትሰራ የተሰጠህን ተግባር አላከናወንክም፣ ማድረግ የሚገባህን ተግባር ሁሉ እንድታከናውን አልፈቀዱልህም፣ ሁል ጊዜም ታማኝ አልነበርክም፣ ችሎታም የለህም . . . ” ወዘተ ሊልህ ይችላል። እያንዳንዳችን ይህንን ታሪክ እና እነዚህን ቃላት በደንብ እናውቃቸዋለን። ይህ በከፊል እውነት መሆኑን እናያለን፣ እናም ወደ እነዚህ ግራ የሚያጋቡ ከመስመራችን ወደ ሚያስቱን ሀሳቦች እና ስሜቶች ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ የተሰጠንን ስጦታ የእግዚአብሔር ነጻ የፍቅር ስጦታ እናጣለን። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይወደናል በድህነታችንም ውስጥ እንኳን ሳይቀር እራሱን ለእኛ ይሰጠናል። ቅዱስ ጄሮም ለጌታ ብዙ ነገሮችን ሰጠ እና ጌታም ብዙ ነገር ከእርሱ ጠየቀ።  ጌታን “ጌታ ሆይ ሁሉንም ነገር ሰጥቼሃለሁ ምንድን ነው የጎደለው?” በማለት ይጠይቀዋል። “ኃጢአቶችህን ፣ ድህነትህ ስጠኝ” በማለት ይመልስለታል። ትኩረታችንን በእርሱ ላይ በምናደርግበት ጊዜ ​​ለሚያድሰን የእሱ ይቅርታ ራሳችንን እንከፍታለን እናም በታማኝነቱ እንረጋጋለን። ዛሬ ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን: - “ትኩረቴን በማን ላይ አድርግያለሁ? በጌታ ላይ ወይስ በራሴ ላይ?” ከምንም ነገር በላይ የእግዚአብሔር ፀጋ ልምድ ያለው ሰው ነገሮችን በዓለማዊ መንገድ ላለመመልከት የሚረዳውን መድኃኒት ሊያገኝ ይችላል።

በገዳም ሕይወት ላይ የተቃጣ ፈተና አለ፡ ይህም ነገሮችን በአለማዊ መንገድ መመልከት ነው። ይህ ከእንግዲህ የእግዚአብሔርን ጸጋ በህይወት ውስጥ እንዳለ መሪ የሆነ ኃይል አድርገን እንዳንቆጥር ያደርገናል፣ ከዚያም እሱን በሌላ ነገር ለመተካት የሆነ ነገር ወደ መፈለግ እንሄዳለን፣ ዝናን እንፈልጋለን፣ የሚያጻናኑንን ነገሮች እንሻለን በመጨረሻም የፈለግነውን ነገር እናደርጋለን። ነገር ግን የገዳም ሕይወት ከእንግዲህ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የማይመላለስ ከሆነ ከራሱ ጋር ይጋጫል። ጣዕሙን ያጣል፣ ይዳከማል፣ ባለበት ቦታ ቀጥ ብሎ ይቆማል። እናም ከዚያ በኋላ ምን እንደሚሆን እናውቃለን - የራሳችንን ቦታ ፣ የራሳችንን መብቶች መጠየቅ ፣ ራሳችንን ወደ ሐሜት እና ስም ማጥፋት እንወስዳለን በሚያጋጥሙን ትናንሽ ነገሮች ሁሉ ቅር እንሰኛለን አልቃሻ የሆንን ካህናት አልቃሻ የሆንን ደናግላን እንሆናለን።  በወንድሞቻችን ፣ እህቶቻችን፣ በማኅበረሰባችን በቤተክርስቲያናችን ላይ ማጉረምረም እንጀምራለን። እኛ በሁሉም ነገር ውስጥ ጌታን አናየውም፣ ነገር ግን የአለም ተለዋዋጭ መንፈስ ልባችንን ያደነድናል። እንግዲያውስ በውስጣችን ሀዘንና መተማመን ሲጎድል በእዚህ ሕይወት ላለመቀጠል እንወስናለን። የአለም እይታ የሚያስከትለው ይህንን የመሰለ አደጋ ነው። ታላቋ ቅዱስት እማሆይ ቴሬዛ በአንድ ወቅት እህቶቻቸውን “በደል ደርሶብኛል በማለት እነዚህን ቃላት የምትናገር እህት ወየውላት!” ብለው ነበር።

በህይወት ላይ ትክክለኛውን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ፣ እንደ ስምዖን ሁሉንም የእግዚአብሔር ፀጋ ማስተዋል እንችል ዘንድ እንዲረዳን እርሱን እንጠይቅ። ቅዱስ ወንጌል በእርሱ ላይ ከነበረው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት እንደነበረው ሦስት ጊዜ ገልጹዋል። እርሱ ከመንፈስ ቅዱስ እና ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር በደንብ ይተዋወቅ ነበር። የገዳም ሕይወት ለጌታ ባለው ፍቅር ላይ ጸንቶ የሚቆይ ከሆነ የሕይወቱን ውበቱን ይመለከታል። ድህነቱ እጅግ ወሳኝ የሆነ እጥረት ሳይሆን ፣ እግዚአብሔር ለእኛ እና ለሌሎች እንደ እውነተኛ ሀብት የሰጠን ከፍተኛ ነፃነት መሆኑን ይረዳል። በድንግልና መኖር መካንነት አለመሆኑን ይረዳል፣ በተጨማሪም ያለምንም ገድብ መውደድ እንደ ሆነም ይረዳል። ታዛዥነት ተግሣጽ ሳይሆን ፣ በኢየሱስ መንገድ ላይ ለመጓዝ ያስችለን ዘንድ በራሳችን ላይ የምንጎናጸፈው ድል ነው።

ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋል። ስምዖን ኢየሱስን እንደ ትንሽ፣ ትሑት ፣ ለመገልገል የመጣ ሳይሆን ለማገልገል የመጣ፣ ራሱን እንደ አገልጋይ አድርጎ እንደ ገለጸ ይመለከታል። በእርግጥ “ጌታ ሆይ ፣ አሁን አገልጋይህ በሰላም አሰናብተው” (ሉቃስ 2፡29) በማለት ይናገራል። ነገሮችን እንደ ኢየሱስ የሚያዩ ሰዎች ማገልገል እንዴት እንደ ሚቻል ይማራሉ። እነሱ በቤተመቅደስ ውስጥ ኢየሱስን እንደፈለጉት ስምዖን ሌሎች ቅድሚያውን እንዲወስዱ አይጠብቁም። በገዳም ሕይወት ውስጥ ባልንጀራችንን የት እናገኘዋለን? ጥያቄው ይህ ነው- ባልንጀራችንን የት ማግኘት ይቻላል? በመጀመሪያ ደረጃ በእያንዳንዳችን ማኅበር ውስጥ ልናገኘው ይገባል። በተሰጡን ወንድሞች እና እህቶች ውስጥ ኢየሱስን እንዴት መፈለግ እንደ ሚገባን ማወቅ እንችል ዘንድ ጸጋውን መፈለግ ይኖርብናል። ያ በትክክል ምጽዋትን ተግባራዊ ማድረግ የምንጀምርበት ቦታ ነው-በምንኖርበት ስፍራ ወንድሞችንና እህቶችን ከእነ ድህነታቸው መቀበል ማለት ስምዖን ሕጻኑን እና ድሃ የነበረውን ኢየሱስን እንደ ተቀበለው ማድረግ ነው። ዛሬ ብዙዎች በሌሎች ሰዎች ውስጥ እንቅፋት እና ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ብቻ መመልከት ይቀናቸዋል። ባልንጀራዎቻችንን ሩቅ በሆነ ስፍራ ሳይሆን አብረውን ከሚኖሩ ሰዎች መካከል መፈለግ ይኖርብናል። የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል በገዳም ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች የራሳቸውን ዕይታ ወደ ዓለም እንዲያመጡ ተጠርተዋል፣ ይህምም የርህራኄ እይታ ፣ ሩቅ ያሉትን ለመፈለግ የመሄድ እይታ ነው፣ የማይኮንን፣ የሚያበረታታ ፣ ነፃ የሚያወጣው መጽናኛ የሆነ ርህራሄ የተሞላው እይታ። ቅዱስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ በተዳገጋሚ ሲናገር እርሱ  “ርህሩህ ነው” ይላል። ይህ እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ልንማር የሚገባው ተግባር ነው።

ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋል። የስምዖን ዐይኖች ደህንነትን አይተዋል፣ ምክንያቱም ለረጅም ጊዜያት ሲጠባበቁ ስለነበረ። እነሱ በተስፋ ተሞልተው ይጠባበቁ የነበሩ ዓይኖች ናቸው። ብርሃንን ይፈልጉ ነበር እናም የዓለም ብርሃን የሆነውን እርሱን ይመለከታሉ።  እነሱ በዕድሜ የገፉ ዓይኖች ነበሩ፣ ነገር ግን በተስፋ ይጠባበቁ የነበሩ ዐይኖች ነበሩ። የገዳም ሕይወት የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች ዕይታ አንድ ብቻ ሊሆን ይችላል። እንዴት ተስፋ ማድረግ እንደሚቻል ማወቅ። ዙሪያቸውን መመልከት፣ ነገሮች ሁሉ መልካም ላይሆኑ ይችላሉ፣ ለመንፈሳዊ ጥሪ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ . . . ወዘተ። ተስፋችንን የሚያደበዝዝ ዓለማዊ የሆነ እይታ ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። በእዚህ ጊዜ ቅዱስ ወንጌልን እንመልከት የስምዖንን እና የሐናን ታሪክ እንመልከት። እነሱ አረጋውያን ብቻ የነበሩ ሳይሆን ነገር ግን ከጌታ ጋር ህብረት ስለ ነበራቸው ጭምር ተስፋ አልቆረጡም። ሐና “ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች” ። ምስጢሩ ይህ ነው -የተስፋ ምንጭ ከሆነው ጌታ ራሳችንን መነጠል በፍጹም አይገባንም። እግዚአብሔርን ካላቀረብን በየቀኑ ወደ ጌታ ካልተመለከትን ዕውር እንሆናለን። ጌታን ማምለክ ይሳነናል ማለት ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች የገዳም ሕይወት እንድንኖር ሕይወቱን በስጦታ የሰጠንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፣ እናም እርሱን በአዲስ መልክ መመልከት የምንችልበትን መንገድ እንዲያሳየን እንጠይቀው።  ፀጋን እንዴት እንደምናይ ፣ ባልንጀሮቻችንን መፈለግ፣ ተስፋ ማድረግ እንችል ዘንድ እንዲረዳን እንጠይቀው። በእዚህ ሁኔታ የእኛም ዓይኖች ማዳንን ያያሉ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 February 2020, 14:39