ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የዓለም ሕዝቦች ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር የገባቸዋል አሉ!

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል የተባበሩት የአረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ በሆነችው በአቡ ዳቢ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሐይማኖት መሪዎች በጥር 26/2011 ዓ.ም ስብሰባ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእዚህ ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የግብፅ የአልዓዛር ታላቁ መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ አስተዳዳሪ የሆኑትን ታላቁ ኢማም አህመድ አል ጣይብ ጨምሮ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን በእዚህ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሕዝቦች መካከል ያለውን ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለማጠናከር በማሰብ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ አንድ ሰንድ ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ይህ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የተለያየ ሐይማኖት ተከታይ በሆኑ ሕዝቦች መካከል ሐይማኖትን እና ዘርን ባላማከለ መልኩ ሕዝቡ በአንድነት እና በወንድማማችነት ፍቅር ላይ ተመስርቶ በሰላም እና በአንድነት ይኖር ዘንድ ታስቦ የተካሄደው ስብሰባ አንደኛ አመት በጥር 26/2012 ዓ.ም በቫቲካን በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦች በሰላም እና በአንድነት እንዲኖሩ የተጀመረው ጥረት በመሆኑ የተነሳ ይህ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በጥር 26/2012 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ያፋ አድርገዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተካታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

         ለሁላችሁም እዚህ ለተገኛችሁት በሙሉ ሰላምታዬን እያቀረብኩኝ በተለይም ድሃ ፣ ህመምተኛ ፣ ስደተኛ እና አቅመ ደካማ የሆኑ በማኅበርሰብ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ምንም ዓይነት የሃይማኖት ፣ የቆዳ ቀለም ፣ የዘር ፣    ልዩነት ሳታደርጉ እርዳታ እያቀረባችሁ የምትገኙ ሰዎች ሁሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

         ከአንድ አመት በፊት ወንድሜ ከሆኑት ታላቁ የአል አዛር ኢማም ዶክተር አል ታይብ ጋር በመሆን የተባበሩት የአረብ ኢሚሬቶች ዋና ከተማ በሆነችው አቡ ዱቢ ውስጥ ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በተመለከተ ካደረግነው ስብሰባ በመቀጠል ያወጣነውን አንድ ሰንድ በፊርማችን አጽድቀናል። ዛሬ ከጥላቻ፣ ከዘር፣ ከአክራሪነት እና ከአሸባሪነት ነፃ የሆነ ፣ የሰላምን ፣ የፍቅርን እና የአክብሮት እሴቶችን የሚያጎናጽፉንን የዚህን ታላቅ የሆነ ሰብአዊነ ወንድማማችነት የሚያጠናክረው ሰንድ የተፈረመበት የመጀመሪያውን ዓመት ዛሬ እናከብራለን።

         ዛሬ ይህ ሰብዓዊ ወንድማማችነት በሚል አርእስት የተፈረመው ሰነድ የመጀመሪያ ዓመት በምናክብርበት ወቅት ይህ ሰነድ ይፋ ይሆን ዘንድ የአብርሃም ቤት በመባል የሚታወቀው እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ የሚገኘው ተቋም ሰብዓዊ ወንማማችነት እንዲጠናከር ለወሰደው ተነሳሽነት አመስንግናለሁ።

         ስለሆነም በዚህ ዓለም ውስጥ ለሌሎች ሰዎች መልካም ተግባሮችን እና መስዋትነትን በመክፈል ፍቅርን በዓለም ውስጥ የሚያንፀባርቁ ወንዶች እና ሴቶች ለሚያሳዩት በጎ አራያ ሁሉ እንዲበረታቱ፣ በዓለም አቀፉ ደረጃ የሰብዓዊ ወንድማማችነት መንፈስ እንዲበረታታ ይህ ሰንድ ይፋ በመሆኑ መደሰቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።            በሐይማኖት ወይም በጎሳ እና በባህል ምንም ያህል ልዩነቶች ቢኖሩም ሁሉን ሰዎች ሰብአዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር ወደ ፊት እንድንጓዝ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር እንዲባርክን እጠይቃለሁ። አመስግናለሁ!

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በጥር 26/2011 ዓ.ም ተካሂዶ ባለፈው ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተካፋይ እንደ ነበሩ ቀድም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የእስልምና እምነት መነሻ በሆነው በአረብ ባህረ-ሰላጤ ተገኝተው እርሳቸው በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታይ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጋራ የሆነ የእምነት እውቀት እና በተጨማሪም በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የነበሩ ግንኙነቶች እና ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ፣ ልዩነቶችን ለማጥራት ቁርጠኛ በመሆን፣ እነዚህ ጉዳዮች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የመሸጋገሪያ ድልድይ የሚገነባ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች እርስ በእርሳቸው እንዲተማመኑ በማድረግ ወንድማማቾች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ የሚረዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገው እንደ ነበረ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አብዛኛው ሕዝባቸው የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች እና ልዩ ልዩ ስብሰባዎች በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሕዝቦች እና ለመላው ዓለም ሳይቀር የሰባዊ ፍጡር ሊኖረው ስለሚገባው ፍቅር ትምህርት የሰጠ አጋጣሚ ነበር።

በእስልምና እምነት ውስጥ የሚታዩ በጎ ነገሮች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ አብዛኛው ሕዛባቸው የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ አገራት ውስጥ ተገኝተው ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን እ.አ.አ በ2014 ዓ.ም ወደ ቅድስት አገር አድርገውት ከነበረው ሐዋርያዊ ጉዞ በመቀጠል ዮርዳኖስን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን በዚያ ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላ ሁለተኛ ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው “በእስልምና እምነት ውስጥ የሚገኙ መልካም ባሕሪያት እና ስነ-ምግባሮች፣ የተለያየ እምነት ተከታዮች ሰላማዊ አንድነት እንዲመሰርቱ የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥር በመሆኑ የተነሳ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያላቸውን ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት” ገልጸው እንደ ነበረ ይታወሳል። በዚህ አጋጣሚ "በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ጥሩና የወዳጅነት ግንኙነት እንዲሰፍን" አስተዋጾ እንደሚያበረክት ተስፋ እንደ ሚያደርጉም መግለጻቸው ይታወሳል።

መከባበር እና መተባበር

እ.አ.አ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአልባኒያ ዋና ከተማ የሆነችውን ቲራና በጎበኙበት ወቅት በአገሪቷ "በአልባኒያ ያለው ቱባ ባሕል ለሁሉም የአገሪቷ ሕዝብ እንክብካቤ እና ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን በመመልከቴ እና በመገንዘቤ ተደስቻለሁ” በማለት ማናገራቸው የሚታወስ ሲሆን “የተለያየ እምነት በሚከተሉ ሰዎች መካከል ሰላማዊ ትስስር እና ትብብር” እንዳለ መመልከታቸውን በደስታ መግለጻቸው ይታወሳል። በካቶሊክ፣ በኦርቶዶክስና በሙስሊም እምነት ተከታዮች መካከል ያለው የመከባበርና የመተማመን መንፈስ ለአገሪቷ እጅግ የከበረ ሐብት ሲሆን አሁን ከፍተኛ ትኩረት ለሚፈልገው ዓለማችን ደግሞ መልካም የሆነ አብነት እና አስተምህሮ የሚሰጥ ተሞክሮ እንደ ሆነ” መግለጻቸው ይታወሳል።

ለሰላም የሚደረግ የጋራ ጸሎት

እ.አ.አ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቱርክ ዋና ከተማ በሆነችው በስታንቡል ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው በእዚያ አድርገውት የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ቫቲካን በመመለስ ላይ በነበሩበት ወቅት በወቅቱ በቱርክ የነበራቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሚከተለውን ብለው ነበር “እኔ ወደ ቱርክ የሄድኩት እንደ አገር ጎብኝ ሆኜ ሳይሆን እንደ አንድ መንፈሳዊ ተጓዥ በመሆን ነበር። መስጊድ ለመጎብኘት በሄድኩበት ወቅት በወቅቱ ይህንን መስጊድ ስያስጎበኘኝ የነበረው ሙፍቲ በታላቅ ትህትና በመስጊዱ ውስጥ ያሉትን ነገሮች አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ሲገልጹልኝ እና ሲያብራሩልኝ በነበረበት ወቅት በቁርዓን ውስጥ ስለማርያምንና ስለመጥምቁ ዮሐንስን የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሚገባ አብራርቶልኝ ነበር። በዚያን ወቅት እኔም በዚያው ስፍራ ሆኜ መጸለይ እንደ ሚገባኝ ተሰማኝ። ሙፍቲውን ‘ትንሽ እንጸልይ ወይ?’ ብዬ ጠየኩት። እርሱም እንዴታ! አዎን ይቻላል! በሚገባ መጸለይ ይችላሉ! ብሎ መለሰልኝ። እኔም ለቱርክ፣ ለሰላም፣ ለሙፍቲው፣ ለሁሉም እና ለእራሴ ጭምር ጸሎት አድርጌ ነበር። እኔም እንዲህ ብዬ ጸልዬ ነበር "ጌታ ሆይ እነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ማብቂያ እንዲያገኙ አባክህን አድርግ” ይህ ከልብ የመነጨ ጸሎት ነበር” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

የክርስቲያኖች እና የሙስሊሞች ወንድማማችነት

እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጉዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በእዚያው በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ በባንጉዊ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሕዝቦች መካከል ግጭት ተነስቶ በርካታ ሰዎች ለዕልፈት፣ ለስቃይ እና ለስደት መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአገሪቷ ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሁለቱን እምነት ማለትም የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተቋማት መሪዎችን ፊት ለፊት በማገናኘት ግጭቶች ሁሉ በውይይት ይፈቱ ዘንድ፣ ተገናኝቶ በመወያየት ግጭቶችን የመፍታት ባሕል ያዳብሩ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ በነበራቸው ቆይታ ይህንን ሰላም የማውረድ ጥረታቸውን በመቀጠል በባንጉዊ በሚገኘው መስጊድ ውስጥ ተገኝተው የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡ “እኛ ክርስቲያኖች እና እናንተ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆናችሁ ሁላችሁ እኛ ወንድማማቾች ነን። ስለዚህ እራሳችንን እንደዚህ አድርገን በመቁጠር በዚህ አግባብ መኖር ይኖርብናል። በቅርቡ በአገራችሁ የተከሰቱት አሰቃቂ ክስተቶች እና ግጭቶች በሃይማኖት ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች እንዳልሆኑ በሚገባ እንገነዘባለን። በአምላክ አምናለሁ የሚል ማነኛውም ሰው የሰላም ሰው መሆን ይኖርበታል። በአገራችሁ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች እና ባህላዊ የሆኑ እምነቶችን የሚከተሉ ሕዝቦች ሁሉ ለብዙ አመታት በሰላም አብረው ኖረዋል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

አምላክ ለሐይማኖት አካራሪዎች እውቅና አይሰጥም

ምንም እንኳን በአገሪቷ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቁጥር 900 ያህል ብቻ የነበረ ቢሆንም እ.አ.አ በ2016 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩባት አዘረበጃን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ የአዘረበጃን ዋና ከተማ በሆነችው ባኩ የሚገኘውን መስጊድ ከጎበኙ በኋላ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡ “የግል ፍላጎቶቻችንን ለማሳከት እና የራስ ወዳድነት ስሜቶቻችንን ለሟሟላት እግዚአብሔርን ልንጠቀመው አንችልም፣ እርሱ ማንኛውንም ዓይነት አክራሪነት፣ መነኛውንም ዓይነት አስገዳጅ ጫናዎችን እና የሐሳብ ቅኝ አገዛዝን እምላክ በፍጹም አይቀበልም። በድጋሚ ይህ ቦታ በጣም ትልቅ የሆነ ትርጉም ያለው ቦታ በመሆኑ የተነሳ በእግዚአብሔር ስም ምንም ዓይነት ግፍ መፈጸም አይገባም! የሚል ድምጽ ያሰማል። የእርሱ ቅዱስ ስም የሚፈልገው እንዲሰገድለት ነው እንጂ በሰዎች ላይ ግፍ እና ጥላችን እንድነዛራ ግን አይፈቅድም” ማለታቸው ይታወሳል።

ግፍ መፈጸም የቅድስናን መንፈስ ያርቃል

እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግብፅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደርጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የአልዓዛር ታላቁ መስጊድ እና ዮኒቬርሲቲ ታላቁ ኢማም ከሆኑት አህመድ ሙሀመድ ኣል ታይብ ጋር በተገናኙበት ወቅት የሚከተለውን ንግግር አድረገው ነበር “የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደመሆናችን መጠን ማነኛውንም ዓይነት ቅድስናን የሚያጎድፉ ብጥብጦችን እና ግጭቶችን፣ የኋጢኣት ሁሉ መንስሄ የሆነውን የራስ ወዳድነት መንፈስን በማውገዝ እውነተኛ የሆኑ የውይይት መድረኮችን መክፈት ይኖርብናል። በሰው ልጆች ክብር እና ሰብአዊ መብት ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማውገዝ፣ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ጥላቻዎችን በመፍጠር፣ እነዚህን ጥላቻዎች በሐይማኖትና በእግዚኣብሔር ስም እውነተኛ እንደሆኑ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደርጉትን ጥረቶች በሙሉ ለማጋለጥ እና እነዚህን ጉዳዮች የእውነተኛው አምላክ ፍላጎቶች ሳይሆኑ ነገር ግን የጣዖት አምላክ ፍላጎቶች መሆናቸውን በማሳወቅ፣ የእውነተኛው እግዚኣብሔር ስም ቅዱስ፣ እርሱ የሰላም አምላክ፣ እግዚኣብሔር ሰላም መሆኑን በድፍረት መመስከር ይኖርብናል። ስለዚህ የተቀደሰ ነገር የሚባለው ሰላም ብቻ ነው፣ ስለሆነም በእግዚአብሔር ስም ምንም ዓይነት ግፍ፣ ብጥብጥ፣ ግጭት ሊፈጸም አይችልም፣ ምክንያቱም በእግዚኣብሔር ስም የሚፈጸሙ ግፎች ቅዱሱን የእግዚኣብሔር ስም ያረክሱታልና” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 February 2020, 15:16