ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰባት ቀናት ሐዋርያዊ ክንውኖች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዚህን ሳምንት ሐዋርያዊ ተግባራት በጀመሩበት ጊዜ ባሰሙት ስብከት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ሰው ሆኖ በመገለጥ እና በሰዎች መካከል በመገኘት፣ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለውን ርቀት በማስወገድ፣ ፍቅሩን የገለጸበትን መንገድ በማስረዳት የሳምንቱን ሐዋርያዊ ክንውኖችን የጀመሩት። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው እሑድ፣ የወሩ ሦስተኛው ሳምንት ሰንበት በዋለበት ጥር 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸው ይታወሳል። “የእግዚአብሔር ቃል እለተ ሰንበት” በሚል መጠሪያ፣ ከወትሮ ለየት ባለ መልክ ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልምዳቸውን ለማዳበር እና ሕይወት ሰጪ ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል ጋር ያላቸውን የሕይወት ትስስር ለማጎልበት እንዲረዳቸው በማሰብ በይፋ መጀመራቸው ይታወሳል። በዚህ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት “የእግዚአብሔር ቃል አጽናኝ እና ቀስቃሽ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሻገር ያደርገናል” ማለታቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስናዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የሚነበብበት እና ለምዕመናኑ በበቂ ሁኔታ የሚዳረስበት ዕለት እንዲሆን በቅርቡ መወሰናቸው ይታወሳል። በዚህም መሠረት “የእግዚኣብሔር ቃል እለተ ሰንበት” በመባል የሚጠራው የመጀመሪያው ሰንበት ዘንድሮ ጥር 17/2012 ዓ. ም. በይፋ መጀመሩ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት “የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ያለው፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሻገር የሚያደርግ፣” በንድፈ ሃሳብ ላይ ሳይሆን በዕለታዊ የሕይወት አካሄድ ላይ ተመርኩዞ የሚናገር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የእግዚአብሔር ቃል እለተ ሰንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 17/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ካሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኋላ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ምዕመናን የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ አበርክተውላቸዋል። ከዚህም በመቀጠል ጥር 17/2012 ዓ. ም. በፖላንድ አገር አውሽ ቪዚ ቢንኬርናው በመባል በሚታወቀው ስፍራ፣ በጀርመን ናዚዎች በተገነባው እና ከመላው አውሮፓ የተሰበሰቡ አይሁዳዊያን የታጎሩበት፣ የተጨፈጨፉበት፣ የተወሰኑት ደግሞ ነጻ የወጡበት 75ኛው ዓመት የሚታሰብበት ዕለት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ አስከፊ ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ማቀረባቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንድንታመን፣ ራሳችንን ለአብ ምሕረት እንድንከፍት እና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በመታገዝ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ገልጸው በዓለማችን ዙሪያ እንዲህ ያሉ አሰቃቂ የሚባሉ ድርጊቶች ተመልሰው እንዳይፈጠሩ በትጋት መሥራት እና መጸለይ ይገባል ብለዋል።

ማሕበራዊ መገናኛ መልካም ዜና የሚነገርበት መንገድ ሊሆን ይገባል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ጥር 15/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን 54ኛ ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ቀንን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ትናገሩ ዘንድ” (ዘጸአት 10፡2) በሚል አርእስት እና “ሕይወት ታሪክ ይሆናል” በሚል መሪ ቃል ተመርኩዘው ባስተላለፉት መልእክት የማሕበራዊ መገናኛ መንገዶች እውነትን መሠረት በማድረግ፣ የመልካም ዜናን እውነትነት የሚገልጹ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ጥር 16/2012 ዓ. ም. የልዩ ልዩ ፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ከጳጳሳት፣ ከቀሳውስት እና ከምእመናን ወገን ከተወጣጡት ጋር በመሆን ከርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ከሚመነጩ አስተሳሰቦች በመነሳት በጋብቻ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላልከል እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው።

በክርስቲያኖች መካከል በመልካም ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕል ሊያድግ ይገባል፣

በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለክርስቲያኖች አንድነት በየዓመቱ የጋራ ጸሎት የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል። ዘንድሮ ከጥር 9/2012 ዓ. ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የቆየ የጸሎት ሥነ ሥርዓት በልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች ሲደረግ ቆይቷል። ጥር 16/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ በተዘጋጀው 53ኛ የጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ስብከት “በክርስቲያኖች መካከል አንዱ ሌላውን በመልካም ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕል ሊያድግ ይገባል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ሃሳብ መሰረት በማድረግ በዕለቱ በተከናወነው የጋራ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት የቁንስጥንጥኒያው የውህደት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ተወካይ ለሆኑት ለብጹዕ ወ ቅዱስ ጀናዲዎስ፣ በሮም የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳሳ ተወካይ ለሆኑት፣ ለብጹዕ አቡንነ ያን ኤርነስት እና ለልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ለክርስቲያን ማኅበረሰብ ተወካዮች በሙሉ ልባዊ ሰላምታዬን አቅርበው “ሙሉ አንድነት የምናገኝበት ጸጋን እግዚአብሔር እንዲሰጠን ሳንታክት ዘወትር በሕብረት ጸሎታችንን ወደ እርሱ እናቅርብ” ብለዋል።           

ቅዱስነታቸው “ከክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት የምንማረው፣ የበለጠ እንግዳ ተቀባዮች መሆንን፣ ከሁሉ በፊት በክርስቲያኖች መካከል የመልካም አቀባበል ባሕል እንዲኖር፣ ቀጥሎም ለሌሎች የእምነት ተከታዮች መልካም አቀባበል ማድረግ እንደሚገባን እንማራለን” ብለው “ሌሎችን በእንግድነት መልካም አቀባበል ማድረግ የቆየ የክርስትና እምነት ባሕል ነው ብለዋል። የቀድሞ የእምነት አባቶቻችን ተቸግሮ እርዳታን ለሚጠይቅ ሁሉ እገዛን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስተምረውናል” ብለዋል። ይህን ክርስቲያናዊ ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንጂ እንዲጠፋ ማድረግ የለብንም።

ቤተክርስቲያን ደስተኛ የወንጌል አገልጋዮች ያስፈልጋታል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 19/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ከተገኙት ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ “ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የሚሰማቸውን ደስታ አውጥተው መግለጽ ያስፈልጋል” ብለው፣ በማከልም “ቅዱስ ወንጌል በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገባ ሊሰበክ የሚችለው የወንጌል አገልጋዮች በቃሉ ደስታ የሚሰማቸው ሲሆኑ ነው” ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን ስብከት ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት፣ “ቤተክርስቲያን ወደ ፊት መራመድ የምትችለው፣ ቅዱስ ወንጌልም በሚገባ ሊሰበክ የሚችለው ደስተኛ የሆኑ የወንጌል አገልጋዮች ሲኖሩ ነው” ብለው፣ “ደስታው የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንደሆነ አስረድተው በክርስትናችን፣ በክርስትና ሕይወታችን ሳናፍር ደስተኞች መሆን ይገባል እንጂ የስም ክርስትናን ብቻ ይዘን መጓዝ አያስፈልግም “ብለዋል።

በጠቅላላ የትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ፣ “የተራራ ላይ ስብከት”። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ጥር 20/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ በማቴ. 5: 1-11 ላይ በተጻፈው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት  አስተምሯቸው እንደገለጹት የብጽዕና መንገዶች፣ የሰው ልጆች በሙሉ እንዲጓዙባቸው የተዘጋጁ ናቸው ብለዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል እንዳስረዱት ኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ትምህርቱን ያቀረበበት ከፍታ ሥፍራ፣ እግዚአብሔር አስሩን ትዕዛዛት ለሙሴ የሰጠበትን የሲና ተራራ እንደሚያስታውሰን አስረድተው ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት አዲስ ሕግ ይዞ ቀርቧል ብለው ይህ አዲስ ሕግ ደሃ መሆንን፣ የዋህ፣ ርህሩህ እና ይቅር ባዮች መሆንን ያስታውሰናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን አዳዲስ ትዕዛዛት ሲያስተዋውቅ ግዴታን በማከል፣ በሰዎች ሕይወት ላይ ጫናን በመፍጥረ ሳይሆን ነገር ግን ትክክለኛ ደስታ የሚገኝበትን የራሱን መንገድ፣ “ብጽዓን ናቸው” በማለት ስምንት ጊዜ ደጋግሞ በመናገር መሆኑን አስገንዝበዋል።

በምንሰፍረው መስፈሪያ ይሰፈርልናል።

ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ የሕይወታችን አካሄድ እና ለሰው ልጆች በሙሉ ያለን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ክርስቲያናዊነትን የተላበሰ፣ ቸርነት እና እውነተኛ ፍቅር የሚታይበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ለዕለቱ በተመደበው፣ በማር. 4: 21-25 ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸው “በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል” በሚለው ጥቅስ ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁላችንም በሕይወት ዘመናችን ውስጥ የምናደርጋቸውን ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ እናስገባለን ብለው በተለይም ወደ ሕይወት ፍጻሜ ስንደርስ ያከናወንናቸው አንድ በአንድ እናያቸዋለን። በመጨረሻው ዘመን የሚሰጠን ፍርድ እንዴት እንደሚሆን ወይም ምን እንደሚመስል የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በማቴ. 25 ላይ የተገለጸው የብጽዕና መንገድ፣ በሕይወት ዘመናችን ምን ማድረግ እንዳለብን፣ እንዴትስ ማድረግ እንዳለብን፣ በምን ዓይነት መንገድ መኖር እንዳለብን ሁሉ፣ በመጨረሻው ዘመን የሚሰጠን ፍርድ በዚያው መጠን እንደሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መናገሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም “መስፈሪያችን ክርስቲያናዊ ከሆነ፣ ኢየሱስን የተከተለ ከሆነ፣ የእርሱን መንገድ የተጓዘ ከሆነ፣ የሚሰፈርልን መስፈሪያም ብዙ ርህራሄ እና ብዙ ምሕረት ያለበት መስፈሪያ ይሆናል። ነገር ግን መስፈሪያችን ዓለማዊ መንገድን የተከተለ፣ ክርስትናዊ እምነትን ለስም ብቻ የምንጠቀመው ከሆነ በዚያው መጠን ይሰፈርልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሲል የተጓዘበትን የውርደት መንገድ በማስታወስ፣ በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥመንን መስቀል እና ውርደት መሸከም የምንችልበትን ጸጋ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቅ” ብለዋል።

 

 

01 February 2020, 17:01