ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሮም ከተማ ማዘጋጃ በጎበኙበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሮም ከተማ ማዘጋጃ በጎበኙበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የሮም ከተማ ፣ ሰዎች በወንድማማችነት ፍቅር በጋራ የሚኖሩባት ናት”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 25/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ተገኝተው፣ ሮም የጣሊያን ዋና ከተማ በመሆን የተሰየመችበትን 150ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለከተማው ከንቲባ ለሆኑት ወ/ሮ ቬርጂኒያ ራጂ እንዲሁም ለምክር ቤቱ ሠራተኞች ባሰሙት ንግግር፣ ሮም ሰዎች በወንድማማችነት ፍቅር በጋራ የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። ሮም የጣሊያን ዋና ከተማ ሆኖ የተሰየመው በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ዋዜማ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በወቅቱ የከተማው ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ጂቫኒ ባቲስታ ሞንቲኒ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ስማቸው ጳውሎስ ስድስተኛ በንግግራቸው የሮማ ከተማ የጣሊያን ዋና ከተማ እንዲሆን መደረጉ አንዳንድ ቅሬታዎችን ያስነሳ ቢሆንም ቆይቶ ለአገሩ መልካም ሆኖ ተገኝቷል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ የሮም ከተማ በዋና ከተማነት ይሰየም እንጂ በጣሊያን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርቲያን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተችበት አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በ150 ዓመታት ወስጥ የሮም ከተማ ከፍተኛ እድገቶችን ማስመዝገቧን እና በርካታ ለውጦችን ማሳየቷን፣ ነዋሪዎቿንም የተመለከትን እንደሆነ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ተጎራብተው የሚኖሩባት፣ የተለያዩ የክርስትና እምነቶች ተከታዮች እና ክርስቲያን ያልሆኑትም ከካቶሊክ እምነት ተከታዮች ጋር አብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት” በማለት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ጥር 15/1998 ዓ. ም. በሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተገኝተው ባቀረቡት 21ኛ አስተምህሮአቸው፣ በቁ. 1 ላይ መናገራቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታወሰዋል። ባለፉት 150 ዓመታት ውስጥ ቤተክርስቲያን የተለያዩ የደስታ እና የሐዘን ወቅቶችን ያሳለፈች መሆኑን ያሳታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጋራ ታሪካችን ምሳሌ የሚሆኑ ሦስት ገጠመኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህም የመጀመሪያው የሮም ከተማ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በናዚ ቅኝ አገዛዝ መውደቋን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ1943 – 1944 ድረስ በከተማይቱ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ እምነት ተከታዮችን ለማባረር ተብሎ በተወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ስቃይ መድረሱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በወቅቱ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ጥገኝነትን በመስጠት በርካታ ነፍሳትን ከሞት እና ከስቃይ አደጋ መታደጓን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ጀምሮ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በአይሁድ ማህበረሰብ መካከል ዘላቂ ወዳጅነት መኖሩን በሮም ከተማ የሚገኘውን ታላቁን የአይሁዶች ምኩራብ በጎበኙበት ወቅት መናገራቸውን አስታውሰው ከዚህም በተጨማሪ ቤተክርስቲያኗ በከተማው የሚኖሩትን የእግዚአብሔር ልጆች የምትወክል መሆኗን አስረድተው በሮም ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ታላቅ ሃላፊነትን በመውሰድ ለሌሎች እምነት ተከታዮች በሙሉ ትህትናን እና ቸርነትን ለማሳየት መጠራታቸውን አስታውቀዋል።

በከተማዋ ታሪክ የተመዘገበውን ሁለተኛው ገጠመኝ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስችኮስ፣ የሮም ከተማ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ1962 – 1965 ዓ. ም. በተካሄደው ሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ላይ የተገኙትን የጉባኤው ብጹዓን አባቶች፣ ታዛቢዎች እና ሌሎች እንግዶችን ተቀብላ መልካም መስተንግዶ ማድረጓን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሮም ከተማ እነዚህን ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት፣ ማህበረሰብ ክፍሎች የመጡትን እንግዶች በማስተናገድ በእምነቶች መካከል የሰላም እና የጋራ ውይይቶች የሚደረግባት ከተማ መሆኗን አስረድተው በመሆኑም የሮም ከተማ ለቤተክርስትያን እና ለዓለም በሙሉ ከፍተኛ ትርጉም የተሰጣት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሮም ከተማን እንደ አንድ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት በመመልከት በተናገሩት ሦስተኛ የታሪክ ገጠመኛቸው እንደተናገሩት፣ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 1974 ዓ. ም. የከተማው ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ኡጎ ፖሌቲ አንድ ጉባኤ እንዲካሄድ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ በጉባኤው ላይም በከተማው ውስጥ ለሚገኙት ድሃ ማሕበረሰብ አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግላቸው ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል። ቤተክርስቲያን ድሃ እና ሃብታም ሳትል ሁሉንም በአንድ ዓይን መመልከቷ ኩላዊነቷን ይገልጻል ያሉት ቅዱስነታቸው የሮም ከተማ የሁሉ ሰው መኖሪያ ልትሆን ይገባል ብለው በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የድህነት፣ የብቸኝነት እና የተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮችን አስታውሰዋል።

የተለያዩ ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ እርዳታ እየተደረገላቸው በሮም ከተማ የሚገኙ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በከተማዋ የሚኖሩ እራዳታ ፈላጊዎች ከተማዋን እንደ ሕይወታቸው መመኪያ አድርገው በመመልከት ትልቅ ተስፋ የጣሉባት መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሮም ከተማ ለመላው የሰው ልጆች ውድ ሃብት ሆና መገኘቷን አስታውሰው፣ ልዩ ውበት ያላት ከተማ ናት በማለት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በታኅሳስ ወር 2013 ዓ. ም. የአምላክ እናት በእመ ቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ያደረጉትን ንግግር አስታውሰዋል። ሮም እስካሁን ድረስ ያቆየችውን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሏን ማደስ አለባት ብለው ይህም ከአምስት ዓመት በኋላ ለሚከበረው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ያዘጋጃታል ብለዋል።

ሮም የጣሊያን ዋና ከተማ እንድትሆን የተሰየመችበት 150ኛ ዓመት በሚከበርበት ባሁኑ ወቅት የጋራ ራዕይ ሊኖረን ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሮም የተጠራችበትን ተልዕኮ ማሳካት የምትችለው የወንድማማችነትን ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ነው ብለዋል። የሮም ከተማ በእርግጥ የወንድማማችነት ከተማ ናት ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እጅግ አድርገው ይወዷት እንደነበር አስታውሰው፣ ያ ፍቅር ከሌሎች ጋር በአንድነት እንድንኖር የሚያደርግ ፍቅር ነው ብለዋል።

“የሮም ከተማ የአንድነት ከተማ ናት” በማለት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ እሑድ ሐምሌ 9/1978 ዓ. ም. በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት የተናገሩትን 16ኛ አስተምህሮአቸው አስታውሰው፣ ሮም የአንድነትን እና የሰላምን ምሳሌነት ለዓለም በመግለጽ የወንድማማችነት ከተማነቷን በተግባር ማሳየት ትችላለች ብለዋል።    

ሮም የጣሊያን ዋና ከተማ ሆና ያስቆጠረቻቸው 150 ዓመታት ረጅም መሆናቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚህን ዓመታት መለስ ብሎ ማስታወስ ወደ ፊት የሚመጡ ዓመታትን በጋራ ለመኖር የሚያግዝ መሆኑን አስረድተው፣ ሁሉ አቀፍ ከተማ በመሆን፣ ራሷን ለዓለም ሕዝብ ክፍት በማድረግ ለሰው ልጆች በሙሉ የጋራ መገናኛ ከተማ ልትሆን ይገባል ካሉ በኋላ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ሮም የወንድማማችነት እና የሰላም ከተማ ናት ማለታቸውን አስታውሰው፣ ይህን በማስታወስ፣ ተስፋንም በማድረግ ለከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ መልካሙን በመመኘት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሮም ከተማ ሰዎች በወንድማማችነት ፍቅር የሚኖሩባት ናት።
03 February 2020, 15:48