ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቀረት የሚቻለው በጋራ ጥረት ነው”።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን በያሉበት ሆነው በጸሎታቸው እንዲተባበሯቸው የሚያግዝ ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸውን በቪዲዮ መልዕክታቸው ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ምዕመናን በየካቲት ወር በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ ወድቀው በስቃይ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው፣ ጩሄታቸውንም መላው የዓለም ሕዝብ እንዲያዳምጥ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በዓለማችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኛ ወንዶች እና ሴቶች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተጠውቁ እና በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው ይህን የማኅበረሰባችን አስከፊ ገጽታ በጽኑ መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት 2020 ዓ. ም. ከገባ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ የጸሎት መልዕክት ከጸሎት አስተባባሪ ክፍል ጋር በጋራ ያዘጋጁት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑ ታውቋል። በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚገኙት መምሪያዎች አንዱ የሆነው የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ የሚከታተል ቢሮ ይህን ወርሃዊ የጸሎት ዝግጅት ለማስተባበር የተነሳበትን ዓላም ሲገልስ በዚህ ወንጀል የተጠቁ ሰዎች ልዩ ትኩረት እንዳልተነፈጋቸው እና በሕዝቡም መካከል ያልተዘነጉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው ብሏል። የየካቲት ወር የጸሎት ሃሳብን የያዘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት፣ የዘመናችን አስከፊ ማሕበራዊ ችግር የሆነውን ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል የሚዋጋ “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን ማህበር ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን የሚያጠናክር መሆኑ ታውቋል። የጸሎት ሥነ ስርዓቱ ጥር 30/2012 ዓ. ም. በመላው ዓለም መከናወኑ ታውቋል።

ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ ከትውልድ አገራቸው ወጥተው በሌላ አገር በስደት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 271.6 ሚሊዮን መድረሱን እና በ2017 ዓ. ም. 258 ሚሊዮን እንደነበር አስታውቋል። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል 47.9 ከመቶ ሴቶች፣ 13.9 ከመቶ ዕድሜአቸው ከ19 ዓመት በታች የሆናቸው መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል። ግሎባል ሪፖርቱ በማከልም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስመልከት ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ጥር ወር 2019 ዓ. ም. በቪዬና ይፋ ባደረገው ዘገባ እንዳስታወቀው፣ ከጎርጎሮሳውያኑ 2014 – 2016 ዓ. ም. ድረስ ጥናት ባደረገባቸው 142 ሀገሮች ውስጥ የወንጀሉ ወይም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ቁጥር 24.000 መድረሱን አስታውቆ፣ ይህ ቁጥርም እጅግ በጣም መሆኑን እና በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ትክክለኛ ጥናት ለማካሄድ ካለመቻሉ የተነሳ አሁንም በስውር ተደብቀው የሚገኙ የወንጀሉ ተጠቂዎች መኖራቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ይህን አስከፊ ማኅበራዊ ገጽታን ለመዋጋት እንቅፋት ሆነው ከቆዩት ምክንያቶች መካከል አንዱ ሙስና እንደሆነ የጠቆሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ችግሩን ለማስወገድ አቅሙ ያላቸው ሰዎች በገንዘብ ትርፍ ላይ ማትኮራቸው ችግሩን ለማስወግድ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ በቅድስት መንበር፣ የሕዝቦች ማሕበራዊ እድገት ጽህፈት ቤት፣ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ክፍል ምክትል ጸሐፊ፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የሚያግዙ ሐዋርያዊ አቅጣጫዎችን የያዙ መመሪያዎች መኖራቸውን ገልጸው እነኣዚህ መመሪያዎች ለቤተክስቲያን እና ከቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ችግሩን ለማስወገ ፍላጎት ላላቸው ክፍሎች ተዘጋጅተው የቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ ሐዋርያዊ መመሪያዎችን በማስመልከት፣ በ“ወንጌል ደስታ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “በሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ሰለባ የሆኑት ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታ ሁል ጊዜም ያስጨንቀኛል፤ ሁላችንም እግዚአብሔር ለቃኤል “ወንድምህ የት አለ”? በማለት በዘፍጥረት 4:9 ላይ ያቀረበውን ጥያቄ ብናስተውል ደስ ይለኛል፤ በባርነት ሕይወት ውስጥ በስቃይ ላይ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የት ናቸው? እነዚህን ሰዎች ከገቡበት የስቃይ ሕይወት ነጻ ለማውጣት የሁላችን ተሳትፎ ሊኖር ያስፈልጋል” ማለታቸውን ብጽዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ አስታውሰዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው ቅዱስነታቸው ወደ ታይላንድ እና ጃፓን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋቢ በማድረግ ባስተላለፉት መልዕት የማህበራቸው አባል የነበሩት ክቡር አባ ፔድሮ አሩፔ የታይላንድ ሕዝብ ነቢይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በኢየሱሳዊያን ማሕበር የሚመራ የስደተኞች አገልግሎት ማዕከል መስራች መሆናቸውን አስረድተዋል። አባ ፔድሮ አሩፔ ይህን የስደተኞች የዕርዳታ አገልግሎት በመሠረቱበት ጊዜ ከሁሉም በላይ መጸለይ እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ መሆኑን ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አስታውሰዋል። ይህን በሚገባ ማወቅ አለብን ያሉት ክቡር አባ ፍሬደሪክ በማከልም በምንም ዓይነት ችግር ውስጥ ብንገኝም ብርታትን የምናገኝበት መንፈሳዊ ጎዳናን መዘንጋት የልብንም ብለዋል። ማሕበራዊ ፍትህ በጎደለበት፣ ነገሮች ባልተስተካከሉበት ሁኔታ ላይ ፍትህን ማምጣት የሚቻለው ከጸሎት በምናገኘው ብርታት በመታገዝ መሆኑን አስታውቀዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በመጨረሻም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ወድቀው በስቃይ ሕይወት የሚገኙትን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው፣ ጩሄታቸውንም መላው የዓለም ሕዝብ እንዲያዳምጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ማለታቸውን ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
08 February 2020, 16:41