ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዓለም የገንዘብ እና ፍይናንስ ተቋማት መሪዎች እና ሚኒስትሮች ጋር፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዓለም የገንዘብ እና ፍይናንስ ተቋማት መሪዎች እና ሚኒስትሮች ጋር፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዓለም የገንዘብ ተቋማት የኤኮኖሚ አለመመጣጠንን እንዲያስተካክሉ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 27/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው የዓለም የገንዘብ እና ፍይናንስ ተቋማት መሪዎች ባደረጉት ንግግር፣ በማሕበራዊ ሕይወት ወደ ኋላ ለቀሩትን፣ ለተገለሉት እና ለተናቁት ቅድሚያን የሚሰጥ የኤኮኖሚ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ጥር 27/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የማህበራዊ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከፈረንሳይ፣ ከአርጄንቲና፣ ከሜክስኮ፣ ከፓራጓይ፣ እና ከኤል ሳልቫዶር የመጡ የገንዘብ ሚኒስትሮች መሆናቸው ታውቋል። ከእነዚህ የገንዘብ ሚኒስትሮች በተጨማሪ ከአለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም ዳይሬክተሮች እና በኤኮኖሚ የኖቤል ተሸላሚ ግለሰቦች መገኘታቸው ታውቋል።

የዓለማችንን መዋዕለ ነዋይ በማንቀሳቀስ ተግባር ቁልፍ ሚናን የሚጫወቱ ግለሰቦችን ያሳተፈው ይህ ጉባኤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ልዩነት፣ ይህም ሲባል የኤኮኖሚ ሥርዓቱ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደርግ ሁሉንም የሚያካትት ፣ ሕዝቦችን የሚያቀራርብ እና የሚያዋህድ፣ የሁሉንም ሰው የፈጠራ ችሎታ እንዲያድግ የሚያደርግ፣ እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዕድል የከፈተ መሆኑ ታውቋል።     

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማሕበራዊ ኤኮኖሚ ዙሪያ የጋራ ጥቅሞችን አስመልክተው ባደረርጉት ንግግር በእያንዳንዱ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የሰው ልጅ እንዳለ መዘንጋት የለበትም ብለው ስለ ኤኮኖሚ ስናስብ ለሰው ልጅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በማከልም ጤናማ ኤኮኖሚ ከምርት ውጤት ጥራትና ከኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሊነጥል አይችልም ብለው ጤናማ የኤኮኖሚ ሥርዓት ሁል ጊዜ በመልካም ሥነ ምግባር የታገዘ ነው ማለታቸው ይታወሳል። 

ቅዱስነታቸው በጳጳሳዊ ምክር ቤት የማህበራዊ ሳይንስ አካዳሚ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለተገኙት የጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር በርካታ የኤኮኖሚ ሞዴሎች ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና የኤኮኖሚ ሞዴሎችን በማስተካከል በደሃ እና ሃብታም መካከል የሚታዩ ክፍተቶችን ለማጥበብ የሚያግዙ መንገዶችንም ጠቁመዋል።

እያደገ የመጣው የኤኮኖሚ አለመመጣጠን፣

ዓለም ሃብታም ብትሆንም ነገር ግን በድህነት ሕይወት የሚኖሩ የዓለማችን ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ባሁሉ ጊዜ በዓለማችን ከብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦች በከፍተኛ የድህነት ሕይወት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ በቂ ምግብ፣ መጠለያ፣ የጤና እንክብካቤ፣ የትምህርት ዕድል፣ መብራት እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል። በያዝነው ዓመት በዓለማችን ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት ከድህነት ጋር በተዛመደ ችግር እንደሚሞቱ ገልጸው ቅዱስነታቸው በማከልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ባለው የኤኮኖሚ እድገት አለመመጣጠን ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለሴተኛ አዳሪነት እና ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የመፍትሄ ማግኛ መንገዶች አሉ፣

በእነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች የተነሳ ተስፋ መቁረጥ የለብንም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ ለመውደቅ የተገባን አይደለንም ብለው፣ ከችግሮች የምንወጣበት የምፍትሄ መንገዶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ድህነትን መቀነስ ይቻላል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኤኮኖሚ ሥርዓታችን ለተራቡት በቂ ምግብን በማቅረብ፣ ለታመሙት ተገቢ ሕክምናን፣ ለታረዙት ልብስን ማቅረብ የሚያስችል የኤኮኖሚ ሥርዓት ከተገነባ ድህነትን መቀነስ ይቻላል ብለዋል። እነዚህ ማሕበራዊ አገልግሎቶች በቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎችን መለየት አልብን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በማሕበራዊ ኑሮ መካከል የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ማሕበራዊ ፍትህን ይህ ካልሆነ ደግሞ አመጾችን ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ አስረድተው፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቶች ሰብዓዊ ሕይወትን ያማከሉ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የኃጢአት አወቃቀር፣

ከፍተኛ የሃብት ክምችት በሚገኝበት ዓለማችን ድህነት ምኑን ያህል ገንኖ እንደሚገኝ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአሁኑ ጊዜ በዓለማ እጅግ ሃብታም የተባሉ ሃምሳ ግለሰቦች 2.2 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በእጃቸው ይዘው እንደሚገኙ ገልጸው፣ ይህ የገንዘብ መጠን በዓለማችን ለሚገኙ ደሃ ሕጻናት በቂ የህክምና አገልግሎቶችን በማቅረ፣ የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት እና የብዝዎችን ሕይወት ከሞት ማትረፍ የሚችል መሆኑን አስረድተው የኃጢአት ምንጭ የሆነበትን መንገድ ሲያስረዱ ፣ በየዓመቱ በግብር መልክ የሚሰበሰብ የገንዘብ መጠን የጤና ተቋማት እንኳ መደጎም እየቻለ፣ ይህ ሳይደረግ ቀርቶ ወደ ጥቂት ግለሰቦች እጅ ይገባል ብለዋል።

የጋራ ሃላፊነት እና ወንድማማችነት ሊኖር ይገባል፣

አሁንም ወደ መፍትሄው ሃሳብ የተመለሱት ቅዱስነታቸው፣ ለዓለም የገንዘብ እና ፍይናንስ ተቋማት መሪዎች ባቀረቡት ሃሳብ የጋራ ሃላፊነትን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ ይገባል ብለው በተቋማቱ መካከል መተማመን ሊኖር ይገባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እድገትን እንዲያሳዩ ማገዝ ያስፈልጋል ብለው ሰብአዊ አንድነት ፣ የገቢ መጠንን ማሳደግ ፣ የጤና አገልግሎትን ማዳረስ ፣ ሁለንተናዊ የትምህርት ዕድሎችን ማመቻቸት ፣ ለሰው ልጆች አንድነት መሠረት የሆኑ “የኢኮኖሚ መብቶች” ናቸው ብለዋል።

የተገለሉትን ማገዝ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት ተማጽኖአቸው፣ የዓለም የገንዘብ እና ፍይናንስ ተቋማት መሪዎች እና የገንዘብ ሚኒስትሮች በሙሉ በድህነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት የዓለማች ሕዝቦች ቅድሚያን በመስጠት፣ ከዕዳ ጫና ለመላቀቅ ደፋ ቀና የሚሉ አገሮችን በመደገፍ እና በዓለማችን የተከሰተው የአየር ለውጥ ያስከተለውን ችግሮች መቋቋም እንዲቻል የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። ሰብዓዊ ክብርን በማምጣት ታሪክን መለወጥ በሚችል የእግዚአብሔር ሥራ ዕቅድ መሳተፍ ያስፈልጋል በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 February 2020, 13:49