ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ “የዐብይ ጾም ወቅት፣ ቴሌቪዥናችንን አጥፍተን መጽሐፍ ቅዱስን የምንከፍትበት ወቅት ነው” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በየካቲት 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ በጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር መሰረት የላቲን ስርዓተ አምልኮ በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በየካቲት 18/2012 ዓ. ም. የሚጀመረውን የዐብይ ጾም አስመልክተው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ነበር ታውቋል። በዚህም መሰረት ከሉቃስ ወንጌል “ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው፤ በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ቆይቶ በመጨረሻ ተራበ” (ሉቃ 4፡1-2) በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተምህሮ እንደ ነበር ታውቋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየካቲት 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አስናድተነዋል፥

“የዐመድ መቀባት ስነ-ስረዓት በምናደርግበት በዛሬው፣ ረቡዕ እለት የዐብይ ጾም ወቅትን የምንጀምር ሲሆን በእነዚህ የአርባ ቀን ጉዞ የአመቱ ስርዓተ አምልኮ እና የእምነታችን ልብ ወደ ሆነው ወደ ፋሲካ በዓል የምናደርገውን ጉዞ እንጀምራለን። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በምድረ በዳ ለመጾም እና ለመጸለይ በሄደበት ወቅት በዲያቢሎስ ተፈትኖ የነበረው ኢየሱስ የተጓዘበት መነገድ ነው።  ስለ ምድረ በዳ መንፈሳዊ ትርጉም ዛሬ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። በረሃው ለሁላችን ምን ማለት ነው? በከተማ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ ምድረ በዳ ምን ማለት ነው።

ምድረ በዳ ውስጥ እንዳለን አድርገን እናስብ። በመጀመሪያ የሚሰማን ስሜት እራሳችንን በታላቅ ፀጥታ የተከበበን ሆኖ እንዲሰማን የሚያደርግ ስሜት ነው፣ ከስትንፋሳችን እና ከነፍሳችን በቀር ጫጫታ የማይሰማበት ስፍራ። ምድረ በዳ በዙሪያችን ከሚሰማው ጫጫታ የምንላቀቅበት ስፍራ ነው። ምንም ዓይነት ቃል ሳንናገር ለሌላ ቃል ማለትም ለስለስ ላለወ የእግዚአብሔር ቃል ስፍራ የምንሰጥበት ቦታ ነው (1 ኛ ነገሥት 19፡ 12)። ምድረ በዳ፣ ቃሉ የሚገኝበት ስፍራ ነው። በእውነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታ በምድረ በዳ እኛን ማነጋገር እንደ ሚወድ ያሳያል።  በምድረ በዳ ለሙሴ “አስር ቃላቱን”  ዐሥቱን ትእዛዛት ሰጠው። ሕዝቡም እንደ ከዳተኛ ሙሽራ እርሱን በተውበት ወቅት ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “እነሆ ወደ ምድረ በዳ አመጣቸዋለሁ፣ ለልባቸውም እናገራለሁ።  በዚያ በወጣትነቱ እንደ ነበረ እርሱ ይመልስልኛል” (ሆሴ 2 16-17) ፡፡ ለስለስ ያለውን፣ በምድረ በዳ ያለውን የእግዚአብሔር ቃል እንሰማለን። መጽሐፈ ነገሥት ውስጥ “የእግዚአብሔር ቃል እንደሚሰማ ዝምታ ክር ነው” ይላል። በምድረ በዳ ውስጥ፣ በበረሃ ውስጥ ለስለስ ባለ ዝምታ ውስጥ እንደሚሰማ ይናገራል። ኢየሱስ ለመጸለይ ራቅ ወዳሉ፣ ምድረ በዳ ወደ ሆኑ ስፍራዎች መሄድ ይወድ ነበር (ሉቃ 5፡ 16)። በፀጥታ የሚያናግረውን አብን እንዴት መፈለግ እንደምንችል አስተምሮናል። እናም በልብ ውስጥ ዝም ማለት ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ሁል ጊዜ ትንሽ መናገር እና ከሌሎች ጋር ለመሆን እንሞክራለን።

የዐብይ ጾም ወቅት ለእግዚአብሔር ቃል ቦታ የምንሰጥበት ወቅት ነው። ቴሌቪዥናችንን አጥፍተን መጽሐፍ ቅዱስን የሚንከፍትበት ወቅት ነው። ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር ያለንን ቁርኝት አስወግደን ከቅዱስ ወንጌል ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው። በልጅነቴ እኛ ቤት ቴሌቪዥን አልነበረም። ነገር ግን ሬዲዮ የማዳመጥ ልማድ ነበረን። ነገር ግን እርሱንም ቢሆን በዐብይ ጾም ወቅት ማዳመጥ እናቆማለን።  እራሳችንን ከሞባይል ስልክ አላቀን ከወንጌል ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው። አላስፈላጊ ቃላትን ፣ ወሬዎችን ፣ አሽሙሮችን፣ ሐሜትን ለመተው ከ“ጌታ” የምንነጋገርበት ወቅት ነው። ለልባችን ጤንነት የሚሆን መልካም ስነ-ምዕዳር የምንፈጥርበት ወቅት ነው። ልባችንን የምናጸዳበት ወቅት ጭምር ነው።  አሁን የምንኖርበት ሁኔታ ብዙ የቃላት ጥቃቶች የሚፈጸሙበት፣ በብዙ አፀያፊ እና ጎጂ ቃላት በተበከለ አካባቢ ውስጥ ነው። ዛሬ ስድብ እንዲያው እንደ ቀላል ነገር አድርገን “መልካም ቀን” ብሎ እንደመናገር አድርገን ቆጥረን ቀለል አድርገን እንሳደባለን። እኛ ባዶ በሆኑ ቃላት፣ በማስታወቂያዎች እና በስውር በምናስተላልፋቸው መልእክቶች ተሞልተናል። ስለ እያንዳንዱ ሰው ሁሉንም ነገር ለመስማት እንፈልጋለን። በዚህ የተነሳ ልባችንን ወደ ዓለማዊ መንፈስ ውስጥ እንከተዋለን። ይህንን ለመፈወስ የሚያስችለን ግን ዝምታ ነው። የሚናገረውን የጌታን ድምፅ ፣ የሕሊናን ድምጽ ፣ መልካም የሆነ ድምጽ ለመለየት እንታገላለን። ኢየሱስ በምድረ በዳ ውስጥ ሲጠራን አስፈላጊ ያልሆኑ ድምጾችን በመተው አፈላጊ የሆኑ ድምጾችን ብቻ እንድንሰማ ይጋብዘናል። ኢየሱስ በምደረ በዳ ለፈተነው ዲያቢሎስ-“ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴ. 4፡ 4) በማለት ምላሽ ሰጥቷል። የእግዚአብሔር ቃል ከሚያስፈልገን እንጀራ በላይ የሆነ ቃል ነው። ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር አለብን ፣ መጸለይ አለብን። ምክንያቱም የልብን ዝንባሌ ወደ ብርሃን በማምጣት ልባችን እንዲፈወስ የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው። ከጌታ ጋር በጸጥታ መነጋገሪያ መልስ እንድናገኝ ስለሚያደርገን ሕይወትን ይሰጣል፤ ምድረ በዳ የሆነውን ያለመልማል።

እስቲ አሁንም ስለ ምደረ በዳ እንደ ገና ለማሰብ እንሞክር። ምድረ በዳ የግድ አስፈላጊ ቦታ ነው። ኑሯችንን እንመልከት - ምን ያህል ጥቅም የሌላቸው ነገሮች በዙሪያችን አሉ! ለእኛ አስፈላጊ የሆኑ የሚመስሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ነገሮች የሚገኙ ሲሆን እነዚህንም ነገሮች እናሳድዳለን፣ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በእውነቱ ጠቃሚ ነገሮች አይደሉም። በጣም አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ በዙሪያችን የሚገኙትን ሰዎች ፊት ፈልጎ ማግኘት መልካም ነው። በተጨማሪም በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌ ይሰጠናል። ጾም፣ ከንቱ የሆኑ ነገሮችን በመተው ወደ አስፈላጊ ነገሮች መሄድ እንዴት እንደሚቻል የምንማርበት ወቅት ነው።

በመጨረሻም፣ ምድረ በዳ ብቻችንን የምንሆንበት ስፍራ ነው። ዛሬም ቢሆን በአጠገባችን ብዙ ምድረ በዳዎች አሉ። እነርሱ ብቸኛ እና የተተዉ ሰዎች ናቸው። በአጠገባችን የሚኖሩ የተገለሉ እና የተጣሉ ስንት ድሆች እና አዛውንቶች አሉ! ስለ እነርሱ ማውራት አድማጮችን አይስብም። ነገር ግን ምድረ በዳ በዝምታ የእኛን እርዳት የሚማጸኑ ሰዎችን እንድንገናኝ ይመራናል። የእኛን እርዳታ የሚጠይቁ ብዙ ዝም ያሉ እይታዎች አሉ። በዐብይ ጾም ወቅት በምድረ በዳ ውስጥ የምናደርገው ጉዞ የበጎ አድራጎት መንገድ ነው። ጸሎት ፣ ጾም ፣ የምሕረት ሥራዎች: - በዐብይ ጾም ወቅት በምድረ በዳ ውስጥ የምንጓዝባቸው መንገዶች ናቸው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች! በነቢዩ ኢሳይያስ ድምፅ አማካይነት እግዚአብሔር “እነሆ ፣ አዲስ ነገር አደርጋለሁ፣ በምድረ በዳ መንገድን እከፍታለሁ” (ኢሳ. 43፣19) በማለት ይናገራል። ከሞት ወደ ሕይወት የሚመራን መንገድ በምድረ በዳ ውስጥ ይከፈታል።  ከኢየሱስ ጋር ወደ ምድረ በዳ እንገባለን ፣ በፋሲካ በዓል በደስታ እንወጣለን። ይህም ህይወትን የሚያድስ የእግዚአብሔር ፍቅር ኃይል ነው። እኛ የምንበቅለው በፀደይ ወቅት እንደ ሚያብቡ አበቦች እና እፅዋዕት ድንገት እንበቅላለን። በብርታት ወደ እዚህ የዓብይ ጾም ምድረ በዳ ውስጥ እንግባ ፣ኢየሱስን በምድረ በዳ ውስጥ ሆነን እንከተለው፣ እርሱም ምድረ በዳውን ያለመልማል”።

26 February 2020, 17:20