ፈልግ

በብራዚል ግዛት ከሚገኙ ደናማ የአማዞን አካባቢዎች መካከል አንዱ፣ በብራዚል ግዛት ከሚገኙ ደናማ የአማዞን አካባቢዎች መካከል አንዱ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ያላቸውን መልካም ምኞት ገለጹ።

ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ያሳተፈ ጉባኤ መካሄዱ ይታወሳል። ጉባኤው የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት፣ የአካባቢው አገሮች ሕዝቦች ሥነ-ምህዳር እና ቅዱስ ወንጌል ምስክርነትን ለማዳረስ በሚያግዙ አዳዲስ ሐዋርያዊ የአገልግሎት መንገዶች ላይ በስፋት የተወያየ መሆኑ ይታወሳል። ውይይት ከተካሄደባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፣ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በፍሬያማነት መፈጸም የምትችልበት የባሕሎች ግንዛቤ ሊኖራት ይገባል የሚል ነበር። ይህ ማለት የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ጠቅላላ ማኅበራዊ ሕይወትን፣ ባሕልን እና እምነትን ያገናዘበ፣ በተለይም በአካባቢው የሚኖሩ ድሃ ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታን ያገናዘበ የወንጌል ተልዕኮ ማዳረስ አስፈላጊነትን የተመለከተ ነበር።  ለአካባቢው አገሮች ሕዝቦች የወንጌል መልካም ዜናን ማብሰር እና ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ እጅግ አስቸኳይ መሆኑ ተመልክቷል። ሌላው ለሥነ ምሕዳር ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል የሚል ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በላቲን አሜሪካ የአማዞን አካባቢ አግሮች የሚታየው ሃላፊነት የጎደለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ከሁሉ አስቀድሞ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን አደጋ ላይ መጣሉ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስጋት ላይ የጣለ መሆኑ ተመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእነዚህን ሕዝቦች ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ታኅሳስ ወር 2018 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት እውነትን ፈልጎ ለማግኘት የሚደረግ ሕልም እና ምኞት ተቀባይነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው “እግዚአብሔርም ብዙን ጊዜ ስለ ሕልም መናገሩን ገልጸው ፤ ቅዱስ ዮሴፍን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ ቅዱስ ዮሴፍ የዝምታ አስተዋይነት ውሳኔ መልካም ምሳሌ ሊሆነን ይችላል” በማለት በአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ድህረ-ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በኩል ገልጸዋል።   

የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የድህረ-ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ አንባቢያን ስለ አማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ባሕል እና ጠቅላላ የኑሮ ሁኔታ፣ በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ለማድረግ የተለያዩ ግልጽ የሆኑ የማስረጃ መንገዶችን ተጠቅመዋል። ስለ አካባቢው የተፈጥሮ ውበት ከማስረዳት በተጨማሪ የነዋሪ ሕዝብ ዕለታዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል መተንተንም አስፈላጊ ሆኖ ተግኝቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እንዲካሄድ የፈለጉት ለምንድር ነው? የአማዞን አካባቢ አገሮች ተፈጥሮአዊ ሃብት ለተቀረው የዓለማችን የሚሰጠው ፋይዳ ምን ድነው ብሎ መጠየቅ መልካም ይሆናል።

የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የድህረ-ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ገልጠን ስንመለከት በቂ ምላሽ ማግኘት እንችላለን። ከሁሉንም አስቀድሞ ስለ አማዞን አካባቢ አገሮች ተፈጥሮአዊ ይዘት ስንናገር ከሌላው የዓለማችን ክፍል ጋር የሚያገናኘው ምንድር ነው ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ በእውነቱ የዓለማችን ሚዛን በአማዞን አካባቢ አገሮች ደህንነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንገነዘባለን። የሰው ልጅ ጤንነት ከሚኖርበት የሥነ-ምህዳር ስርዓቶች ሊለያይ እንደማይችል ሁሉ ፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚገኙ የነባር ሕዝቦች ውድ ሰብዓዊ እና ባሕላዊ ሃብቶች ተረስተው እንዲቀሩ ወይም ከነአካቴው እንዲጠፉ አሳልፎ መስጠት የሚቻል አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ግድ በሌላቸው እና ከጋራ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን ብቻ ለማስከበር በተነሱ ግለሰቦች እና የተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔዎች ምክንያት የአካባቢው አገሮች የተፈጥሮ ደኖች ያለ ምሕረት ሲጨፈጨፉ እና አካባቢውም ሲራቆት በዝምታ መመልከቱ የሚቻል ሆኖ አልተገኘም። የአማዞን አካባቢ አገሮች ድህንነት ለሌላው የዓለማችን ክፍሎች ወሳኝ እንዲሆን የሚያደርግ ሌላው ምክንያት ወደ ዓለም አቀፋዊነት የተዛወረው የዓለማች የኤኮኖሚ ሥርዓት ለሕዝቦች ዘላቂ እድገት እና ለተፈጥሮ ጥበቃ ዋስትናን የሚሰጥ ባለመሆኑ፣ በህዝቦች እና በባህሎች መካከል ሰፊ እና ጥልቅ ልዩነት መኖሩ፣ ዓለማችንን ያጋጠማት የስደት ቀውስ እና መተኪያ የሌለው የተፈጥሮ ሃብት ላይ የደረሰው አደጋ የሚሉ ይገኙባቸዋል።

“ውድ አማዞን” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ለመላዋ ቤተክርስቲያን ባቀረበው ጥሪ፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች ሊዳረስ በታቀደው አዲስ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በዚህ አዲስ የወንጌል ስርጭት አማካይነት፣ እግዚአብሔር አብ ዓለምን ለማዳን እና ምሕረቱን ለመግለጽ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ እስኪሞት ድረስ ዓለምን እንደወደደ ለመመስከር ነው። የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች በተፈጥሮ ላይ የሚከሰተውን በሽታ ለመዋጋት እንደሚያገለግል መሣሪያ መታየት የለበትም። በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚኖሩ የቀደምት ሕዝቦች ባሕል እና ልማድ ተከብሮ እና ተጠብቆ መቆየት አለበት። ከዚህም በተጨማሪ የተሟላ የወንጌል አገልግሎት የማግኘት መብታቸውም የተጠበቀ መሆን አላበት። ቤተክርስቲያን ከምታበረክተው ሐዋርያዊ አገልግሎት የታገዱ መሆን የለባቸውም። የቀድሞ የወንጌል ልኡካን ረጅም መንገድ ተጉዘው የሚያበረክቱት የወንጌል አገልግሎት፣ የቅዱሳት ምስጢራት ማዳረስ እና የእግዚአብሔር ፍቅር ምስክርነት ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ማግስት ባቀረቡት የምስክርነት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ሲኖዶስ ማለት የሕዝብ መብት እና ስሜት በነጻነት የሚገለጽበት መድረክ አድርጎ በመቁጠር፣ የትዳር ሕይወት ያላቸውን ካህናት መሾምን አስመልክቶ የተነሳው ሃሳብ ትክክለኛ አለመሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ይህ ጥያቄ ወይም ሃሳብ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ የነበረ እና ፊትም ሲነሳ የሚኖር ነው። በየጊዜው የሚነሳ ሃሳብ ከሁሉ አስቀድሞ የክህነትን ምስጢር በሚገባ ያገናዘበ እንዳልሆነ  ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በግልጽ ያስረዳል።  

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪን ማዘጋጀት በተመለከተ፣ ከሁሉ በፊት ጥልቅ አስተንትኖ ካደረጉ እና ከጸለዩበት በኋላ የሚወስደው የማይታጠፍ ውሳኔ የሚለወጥ ሳይሆን በቤተክርስቲያን አስተምህሮ የጸና እና መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች የመነጨ ነው። በተግባር ላይ የተመሠረተ እምነት፣ ለእግዚብሔር ምርጫ ቅድሚያን የሰጠ የጸጋ ስጦታ ፍሬ እና ለወንጌል አገልግሎት ያለው ፍላጎት የሚታደስበት እንጂ በማንኞውም መንገድ በሐይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ተጽዕኖን የሚፈጥር መሆን የለበትም።          

በመሆኑ “ውድ አማዞን” በማለት ይፋ ይሆነው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስክስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ለተለያዩ ማሕበራት እና ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች ግልጽ መልስ በማቅረብ ግንዛቤ እንዲያገኙ ይጋብዛል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሃላፊነትን በመጠየቅ፣ የወንጌል ስርጭት እና በየሰንበቱ የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንዳይጓደል በማለት አዲስ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን በማመቻቸት የቤተክርስቲያን ዕውቅናን ባገኙ ሴት ምዕመናን አገልጋዮች የሚታገዝ አዲስ የወንጌል አገልግሎት የሚቀርብ መሆኑን አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ቃለ ምዕዳናቸው ሴት እህቶቻችን እምነትን በታማኘት በማቆየት ስላደረጉት ትልቅ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።                                  

13 February 2020, 17:01