ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ሰው ሠራሽ አእምሮ ስጦታ ሲሆን፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ሊሆን ይገባል”።
የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤቶች በሆነው ሰው ሰራሽ አዕምሮ እድገት ላይ ውይይት የሚያደርግ አውደ ጥናት ከየካቲት 18-የካቲት 20/2012 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን መካሄዱ ታውቋል። በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ የተለያዩ ምሁራን፣ የሳይንስ ጥበብት እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ተወካዮች እና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ተወካዮችም መካፈላቸው ታውቋል። “በመልካም ስነ ሒሳብ ቀመር የታነጸ ሰው ሰራሽ አዕምሮ” በሚል ርዕስ የተካሄደው አውደ ጥናቱ ስነ ምግባርን፣ ሕግን እና የሰው ልጅ ጤናንም ጭምር ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል። ትናንት የካቲት 20/2012 ዓ. ም. በአውደ ጥናቱ ላይ ለተገኙት መልዕክታቸውን የላኩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰው ሠራሽ አዕምሮ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ ስጦታ በኩል ለሰው ልጅ የሚቀርብ አገለግሎት ስነ ምግባርን የተከተለ መሆን ይገባል በማለት አሳስበዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የዴሞክራሲ ሂደት እና ዲጂታል ዓለም፣
የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት የሆነው ሰው ሰራሽ አዕምሮ በማኅበራዊ ኤኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ጫና የተመለከቱት ቅዱስነታቸው፣ በርካታ ቁጥር ያለው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሚ ማህበረሰብ የጥቂት ሰዎችን ኤኮኖሚያዊ ፍላጎቶች የሚያሟሉ ናቸው ብለዋል። በድረ ግጾች በኩል ስነ ሒሳባዊ ቀመሮችን ተከትለው የሚሰራጩ መልዕክቶች የሰዎችን የአስተሳሰብ ባሕርን በመቆጣጠር ወደ ንግድ እና ፖለቲካ ዘርፎችም ዘልቀው በመግባት የእያንዳንዳችንን ፍላጎት ለይተው ማወቅ ችለዋል ብለው በሌላ ወገን እኛ ስለ እነስርሱ ማንነት የምናውቀው ምንም የለም ብለዋል። የሰዎችን የእኩልነት ሚዛን ያልጠበቀ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የገንዘብ ሃብት በጥቂት ሰዎች እጅ ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉ በላይ ለዴሞክራሲያዊ ማሕበረሰብ አደጋን ያስከትላል ብለዋል። በቅድስት መንበር የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼሶ ፓሊያ በበኩላቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በመጥቀስ እንደተናገሩት፣ ዲጂታሉ ዓለም የሰው ልጅ በቦታ፣ በጊዜ እና በግዙፍ አካል ላይ ያለው ግምት እንዲቀየር ማድረጉ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመምጣት ጉዳዩን የበለጠ አስቸጋሪ እንዲሆን አድሮታል ብለዋል።
ከሁሉም በፊት የሰው ልጅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፣
የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለሰው ልጅ የሚሰጡት አገልግሎቶች ከፍተኛ መሆናቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሥነ ሕይወት ሳይንስም በሰው ሰራሽ አእምሮ መታገዝ ይኖርበታል ብለው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለሰው ልጅ የሚሰጡት አዳዲስ የአገልግሎት ዓይነቶች የሰውን ልጅ አካላዊ እና አዕምሮአዊ የዕድገት ደረጃን በመከተል በጠቅላላው የማሕበርሰብ ሕይወት የሚቀይሩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሥነ ምግባር ከሥነ ሒሳብ ቀመር ጋር ሲገናኝ፣
በቤተክርስቲያን ሕይወት ዘወትር በአዲስ መልክ ሲጠቀስ የሚኖረውን፣ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር አምሳልነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ማዕከላዊ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተው፣ ቴክኖሎጂ ዕድገት ውስጥ መታሰብ ያለበት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያመርት ክፍል ብቻ ሳይሆን የምርቱ ተጠቃሚም ትኩረት ሊሰጠው ይግባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን አስመልክተው ባሰሙት ንግግር በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እና በቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማወቅ የቤተክርስቲያንን ማኅበራዊ አስተምህሮን መሠረት ያደረገ ሰፊ ጥናቶች በሰብዓዊ ክብር፣ በፍትህ እና በማኅበራዊ አንድነት ዙሪያ መድረግ አለባቸው ብለዋል።
የሰው ልጅ መብቶች እና ግዴታዎች በድጋሚ ሊጠኑ ይገባል፣
አሁን በደረስንበት የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ የሰው ልጅ መብቶች እና ግዴታዎች በድጋሚ ሊጤኑ ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገቶች የግለ ሰብን እና ማህበራዊ ስነ ምግባር ላይ ሰፊ ጥናቶች እንዲደረጉ የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጸዉ፣ አውደ ጥናቱን የተካፈሉት የተለያዩ ምሁራን፣ የሳይንስ ጠበብት እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በአውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ላይ ወደ ፊት አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸው “የሥነ ምግባር ጥሪ” የጋራ ስምምነት ሰነድም በሦስት አበይት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸው እነዚህም፣ ሥነ ምግባር፣ ትምህርት እና ሰብዓዊ መብት መሆናቸውን አስታውቀዋል።