ፈልግ

ቅዱስነታቸው የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን በተቀበሉበት ጊዜ፣ ቅዱስነታቸው የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን በተቀበሉበት ጊዜ፣ 

የቫቲካን የሕግ ማሻሻያዎች የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ አካል መሆኑ ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዳሜ ጥር 7/2012 ዓ. ም. የቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት የፍርድ ዓመት መከፈቻን ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር በቫቲካን መንግሥት የተደረጉ የሕግ ማሻሻዎች የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ አካል መሆኑን አስታወቁ። ቅዱስነታቸው በማከልም በቅርቡ በፋይናንስ ዘርፍም ቢሆን የተደረጉ የተሃድሶ ተግባራት ከቫቲካን መንግሥት በኩል የቀረቡ ሪፖርቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 7/2012 ዓ. ም. የቫቲካን ከተማ ፍርድ ቤት አባላትን፣ የፍትህ አስተዳደርን እና የሕግና ስርዓት አስከባሪ ክፍል ሃላፊዎችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ፍትህ የሚጀምረው ከግል መለወጥ ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዱስ ወንጌልን መሠረት በማድረግ ለአባላቱ ባቀረቡት ንግግር ሁለት ነገሮችን ያስገነዘቡ ሲሆን ከእነዚህም የመጀመሪያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው የፍትህ መንገድ ሕጎችን በማስተዋወቅ ብቻ ተግባራዊነታቸውን መከታተል ሳይሆን ሃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች በሙሉ በትክክለኛው መንገድ የሚመሩበትን ሕግ በልባቸው ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያሳስብ ነው ብለው፣ ፍትህ የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ሰው ውስጣዊ መለወጥ መሆኑን አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ፍትህ በሌሎች መልካም ባህሪያት፣ በተለይም በጥበብ እና በልባዊ በጎነት የታገዘ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ዳኞችም የፍርድ መልሶቻቸውን በምሕረት በታገዙት የፍትህ መንገዶች በኩል ማግኘት ይኖርባቸዋል ብለው ዳኞች ፍርድን ከመስጠት አስቀድመው ሕጉን የጣሱት ሰዎች ድክመት በመረዳት የስህተታቸውን መንስኤ ለይተው ለማወቅ ጥረት እንዲያደርጉ ብርታትን ሰጥተዋቸዋል።     

የሕግ ማሻሻያዎች የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ አካል ናቸው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት ሁለተኛው የአስተንትኖ ግንዛቤ፣ የግለሰቦችን ግንኙነቶች የሚከታተል የህጎች ማዕቀፍ እና ለእነዚያ ህጎች የሚሰጡ የሥነ-ምግባር እሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። በቫቲካን መንግሥት የተደረጉ የሕግ ማሻሻዎች ጉልህ ለውጦችን እንዳመጡ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም በሕግ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት ለማዘመን፣ በተለይም ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን ለማክበር ስትል በቫቲካን መንግሥት በኩል ቅድስት መንበር የምታደርገውን ጥረት ያመለክታል ብለዋል። የቅድስት መንበር ጥረትም በቀዳሚነት የሰውን ልጅ እና የማሕበራዊ ትቋማትን ደህንነት ማስጠበቅ ነው ብለዋል። ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የሆነበት ዋና ዓላማ የህግ አወቃቀር እና የፍርድ አሰጣጥ ሂደት በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ እንዲካተት እንዲሁም ወሳኝ በሆኑ የቤተክርስቲያን አገልግሎት አካል እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።

የተሃድሶ ፍሬያማነት፣

በቅርቡ የተካሄዱ የተሃድሶ እርምጃዎች በቫቲካን መንግሥት ፋይናንስ ተቋም ላይ የበለጠ ግልጽነት እንዲታይ አድርጓል ያሉት ቅዱስነታቸው የተሃድሶ ሂደቱ አሁንም በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። በማከልም በቅርቡ በፋይናንስ ዘርፍም ቢሆን የተደረጉ የተህድሶ ተግባራት ከቫቲካን መንግሥት በኩል የቀረቡ ሪፖርቶችን የተከተለ መሆኑን ገልጸው፣ የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ የተደረገበት ምክንያትም የቫቲካን መንግሥት የፋይናንስ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም መሠረት የቫቲካን መንግሥት የደህንነት ቡድንም ከፍትህ ጽሕፈት ቤት ጋር እንዲተባበር መደረጉን አስታውቀዋል። በቫቲካን መንግሥት ውስጥ በተደረገው የተሃድሶ ሂደት የተሰማቸውን እርካታ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መልካም ውጤቱ የሚለካው ሃላፊነትን በተረከቡ ሰዎች ቅንነት ነው ብለዋል። በመሆኑም የፍትህ አገልግሎት ማደግ የሚችለው ትክክለኛ ሰዎች በዘርፉ የተሰማሩ እንደሆነ ነው ብለዋል።

መለኮታዊ ፍትህን መጠበቅ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 7/2012 ዓ. ም. ለቫቲካን ከተማ ፍርድ ቤት አባላትን፣ የፍትህ አስተዳደር እና የሕግና ስርዓት አስከባሪ ክፍል ሃላፊዎች ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃሉ ባሰሙት ንግግር “በምትፈርዱበት መለኪያ ይፈረድባችኋል” የሚለውን የቅዱስ ወንጌል መልዕክት አስታውሰው፣ ምድራዊ ፍትህ በመጨረሻው ቀን እንዲመጣልን ከምንጠብቀው መለኮታዊ ፍትህ ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተው ይህም ወደ ፍርሃት ሳያስገባን ሥራችንን ወይም አገልግሎታችንን በታማኝነት እና በትህትና እንድናከናውን ያግዘናል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 February 2020, 15:17