ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የክርስቲያን ተልዕኮ ኢየሱስን ማወጅ ነው” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሰርት ቅዱስነታቸው በጥር 24/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 2፡ 22-40 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ማርያም እና ዮሴፍ ሕፃኑን ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ መውሰዳቸውን በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው አስተንትኖ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት የክርስቲያን ተልእኮ ኢየሱስን ለዓለም ማወጅ ነው ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸኮስ በጥር 24/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተናዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቀደስ የተወሰደበትን እለት የሚታሰብበትን በዓል እናከብራለን፣ አዲስ የተወለደው ኢየሱስ በድንግል ማርያም እና በቅዱስ ዮሴፍ አማካይነት ወደ ቤተመቅደስ ተወሰደ። በዚህ ተመሳሳይ ቀን የቅዱስ ወንጌል ምክሮችን በመቀበል ጌታን በቅርበት በመከተል በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘውን ታላቅ ሀብት የሚያስታውሰውን የገዳም ሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን እናስባለን።

ዛሬ ከሉቃስ ወንጌል 2፡22-40 ላይ ተወስዶ የተነበበው የእግዚኣብሔር ቃል እንደሚገልጸው ከተወለደ ከአርባ ቀናት በኋላ የኢየሱስ ወላጆች በአይሁድ ሕግ እንደተደነገገው ሕጻኑን ለጌታ ለማቅረብ እሱን ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ ይለናል። እናም በባህላዊው እሴት ላይ ያተኮረውን የአምልኮ ሥርዓት ሲገልፅ ይህ ክፍል የአንዳንድ ገጸ-ባህሪያትን ምሳሌ ያስታውሰናል። እነሱ እርሱ ራሱን በሚያቀርብበት እና ለሰዎች ቅርብ በሚሆንበት ስፍራ ራሳቸውን ያገኛሉ።  እነዚህ ማርያምና ​​ዮሴፍ ፣ ስምዖን እና ሃና ህይወታቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ ሰዎችን የሚወክሉ ናቸው፣ እነዚህ አራት ሰዎች አንድ ዓይነት ሰዎች አይደሉም፣ ሁሉም የተለዩ ነበሩ ግን ሁሉም እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፣ እናም ሕይወታቸው በጌታ እንዲመራ ፈቅደዋል።

ወንጌላዊው ሉቃስ እነዚህን ዐራት ሰዎች የነበራቸውን ባሕሪይ በሁለት መንገድ ይገልጸዋል፣ የመንቀሳቀስ ዝንባሌ እና የመደነቅ ዝንባሌ።

የመጀመሪያው አመለካከት እንቅስቃሴ የሚለው ነው። ማርያምና ​​ዮሴፍ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። በበኩሉ ስምዖን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ ቤተመቅደስ ሄደ፣ አና ቀን ከሌት እግዚአብሔርን ሳታቋርጥ ታገለግለው ነበር። በዚህ መንገድ በወንጌሉ የተጠቀሱት አራቱ ሰዎች ክርስቲያናዊ ሕይወት እንቅስቃሴን እንደሚፈልግ እና በእራሱ መንፈስ ቅዱስ እንዲመላለስ በመፍቀድ በእግር ለመጓዝ ፈቃደኛነትን እንደሚፈልግ ያሳያሉ። አለመንቀሳቀስ ለክርስቲያናዊ ምስክርነት እና ለቤተክርስቲያን ተልእኮ የሚመጥን ነገር አይደለም። ዓለማችን የሚንቀሳቀሱ የሚያነሳሱ የሚያበረታቱ ክርስቲያኖች ይፈልጋል፣ የኢየሱስን አፅናኝ ቃል ሁሉ ወደ ዓለም ለማምጣት በጭራሽ የማይታክቱ ክርስቲያኖችን ይፈልጋል፣ የተጠመቀ ሰው ሁሉ የመናገር ችሎታ አግኝቷል - አንድ ነገር ማወጅ ይህም ኢየሱስን ማወጅ ነው፣ የወንጌል ተልእኮ ኢየሱስን ማወጅ ነው! የቤተክርስቲያኗን ሕይወት እና ተልእኮን እንደ አንድ አበራታች ኃይል በመሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስትና ተሞክሮ እንዲኖረው በቁምስናዎች ውስጥ እና የተለያዩ የቤተክርስቲያኗ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶች ፣ ቤተሰቦች እና አዛውንቶች ቁርጠኝነትን እንዲያበረታቱ ተጠርተዋል።

ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል ውስጥ የጠቀሳቸው አራት ሰዎች የነበራቸው ሁለተኛው ዝንባሌ መገረም የሚለው ነው። ማርያምና ​​ዮሴፍ “ስለ እርሱ [ስለ ኢየሱስ] በተነገሩት ነገሮች ተደነቁ” (ሉቃስ 2፡33) ይለናል።  መገረም የሚለው አስቀድሞ ስምዖን የሰጠው ግልፅ የሆነ ምላሽ ነው ፣ እርሱም በልጁ ኢየሱስ በሕዝቡ ዘንድ እግዚአብሔር ያደረገውን መበዤት በገዛ ዓይኑ አየው፣ እርሱም ለዓመታት ሲጠብቀው የቆየው ደህንነት ነው። የሐናም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፣ እርሷም “እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመረች” ይለናል ቅዱስ ወንጌሉ፣ ሄዳ ሰዎች ኢየሱስን እንዲመለከቱ ጋበዘቻቸው፣ በጥሩ ሁኔታ የተናገረች ቅዱስት ናት። እሷም ኢየሱስን አመጀች።  እነዚህ ሰዎች ለአማኞች መልካም ምሳሌ ጥለው ያለፉ ሰዎች ሲሆኑ በዐይናቸው ያዩትን ክስተቶች ለሌልቾ ለመመስከር መሄዳቸውን ያሳያል። በዙሪያችን ባሉት ነገሮች የመደነቅ ችሎታ የሃይማኖታዊ ልምድን የሚደግፍ እና ከጌታ ጋር ያለን ግንኙነት ፍሬያማ ያደርገዋል ። በተቃራኒው እኛ መደነቅ አለመቻላችን ግድየለሾች እንድንሆን እና በእምነት ጉዞ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት መካከል ያለውን ርቀት ያስፋብናል። ወንድሞች እና እህቶች ፣ ሁሌ በእንቅስቃሴ ላይ በመሆን እና በእርሱ መልካም ሥራ ለመደነቅ ራሳችንን እንክፈት!

በወንድሞቻችን አገልግሎት ውስጥ ህይወታችን በሙሉ እግዚአብሔርን ለማመስገን እንድንችል ፣ በሕይወታችን በሙሉ የእግዚአብሄር ስጦታ ሆነን መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በየእለቱ የእግዚአብሄርን ስጦታ ለሌሎች በማስተላለፍ በእንቅስቃሴ ውስጥ እንድንሆን እና በእርሱ አገልግሎት ውስጥ ተካፋይ ሆነን መኖር እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
02 February 2020, 14:45