ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኢራቅን ሕዝብ በጸሎት የሚያስቧቸው መሆኑን አስታወቁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ካቀረቡ በኋላ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን እና እንግዶች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከፈጸሙ በኋላ በአሁኑ ጊዜ በጦርነት ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የኢራቅ ሕዝብ አስታውሰው፣ ሰላም እና ዕርቅ እንዲወርድ በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር መሠረት፣ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የዓብይ ጾም መግቢያን በሚያስታውስ የአመድ መቀባት ሥነ ሥርዓት የካቲት 18/2012 ዓ. ም. መከናወኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጦርነት አደጋ ውስጥ የሚገኘውን የኢራቅ ሕዝብ አስታውሰው ባሰሙት ንግግር፣ በያዝነው ዓመት ወደ ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸው፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰው ጦርነት ቆሞ ሰላምን እና ዕርቅን በመመኘት ወደ ፈጣሪ ዘንድ ጸሎት የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የጾም ወቅት፣ ራስን በማደስ ውስጣዊ ለውጥ የሚገኝበት ጊዜ ነው፣

የኢራቅ ምእመናን፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማስተንተን፣ ምስጢራትን በመሳተፍ፣ በጾም እና በጸሎት እንዲተጉ በማለት ብርታትን የተመኙላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህን በማድረግ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር እና ከባልንጀራ ጋር ያለውን ግንኙነት ማደስ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የዓብይ ጾም ወቅት መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ላይ ውስጣዊ ለውጥን በማምጣት በመንፈስም እንዲያድግ አደራ ብለዋል።  

26 February 2020, 17:34