ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ቤተክርስቲያን የድሆችን ጩኸት ልታዳምጥ ይገባል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ የካቲት 1/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በዕለቱ ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ቤተክርስቲያን የድሆችን ጩኸት በማዳመጥ ብርሃኗንም በዓለም ሁሉ ልታበራ ይገባል ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን (የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ከዚህ በታች) ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን። አርቅርበንላችኋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት ከማቴ. 5፡13-16 ተወስዶ የተነበበው ንባብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ በማለት የተናገራቸውን ያስታውሰናል፤ (ማቴ. 5፡13 እና 14)። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌያዊ ንግግሩ በዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስችላቸውን እና ምስክርነታቸውን መግለጽ የሚፈልጉ ሰዎች መከተል ያለባቸውን መንገድ ለማመልከት ፈልጓል።

ይህን መንገድ ለማስረዳት ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀመው የመጀመሪያ ምሳሌ ጨው ነው። እንደሚታወቀው ጨው ምግብ እንዲጣፍጥ እና ሳይበላሽ እንዲቆ ያግዛል። ደቀ መዛሙርትም እንደዚሁ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ በተለያዩ አደጋዎች እንዳይጠቃ፣ የሰዎች ሕይወትም በአንዳንድ ጎጂ በሆኑ ተግባራት እንዳጎዳ የሚከላከሉ ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ በምግባረ ብልሹነት፣ በክፋት እና በአመጽ፣ በኃጢአት ውስጥ ወድቀው ለሚገኙት በሙሉ የታማኝነትን እና የወንድማማችነት  እሴቶችን በመመስከር፣ በዓለማዊ ምኞቶች፣ በእውቀት፣ በሥልጣን እና በሃብት መመካት እንደማያስፈልግ መመስከርን ያካትታል። የምድር ጨው የሆነው ደቀ መዝሙር ዕለታዊ ፈተና እና ውድቀት ቢያጋጥመውም፣ ሁላችንንም እንደሚያጋጥመን ማለት ነው፣ በስህተቱ የተነሳ ከወደቀበት ተነስቶ፣ ተስፋን ሳይቆርጥ በየዕለቱ አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ድፍረት ያለው፣ ከሌሎች ወንድሞቹ  እና እህቶቹ ጋር አብሮ ለመኖር ጥረት የሚያደርግ ነው። እንደ ምድር ጨው የሚታይ ደቀ መዝሙር ራሱን ከፍ ከማድረግ ወይም ዝናን ከመፈለግ ይልቅ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ራሱን ዝቅ የማድረግ፣ ትህትናን የሚገልጽ፣ ለመገልገል ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል የመጣውን የኢየሱስ ክርስቶስ አስተህሮች በታማኝነት የሚጠብቅ ነው። ይህን የመሰለ የሕይወት አካሄድ አስፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶአል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀመው ሁለተኛው ምሳሌ እና ደቀ መዛሙርቱንም የመከራቸው፣ ብርሃን መሆንን ነው። ‘እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ’ የሚል ነው። ብርሃን ጨለማን በማስወገድ ሁሉን በግልጽ እንድናይ ያግዛል። ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማን ያስወገደ የዓለም ብርሃን ነው ፣ ይህ ብቻ አይደለም የእርሱ ብርሃን በእያንዳንዱ ሰው ላይ በማረፍ  ሁል ጊዜ እያበራ ይኖራል። የአንድ ክርስቲያን ተልዕኮ እና ጥሪ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እየመሰከረ፣ ከእርሱ የተቀበለውን ብርሃን በሌሎች ዘንድ እንዲበራ ማድረግ ነው። ይህ የወንጌል ማብሰር ተልዕኮ እና ለሌሎች ብርሃን ሆኖ የመገኘት ጥሪ የቃል ምስክርነት ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ምስክርነታችን በመልካም ሥራችን የታገዘ ሊሆን ይገባል። “እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴ. 5:16) አንድ ደቀ መዝሙር ወይም ማኅበረሰብ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚመራ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን መልካምነት፣ የእርሱን የምሕረት መንገድ እንዲከተሉ የሚያደርግ ከሆነ የዓለም ብርሃን ይሆናሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የዓለም ብርሃን መሆን የሚችለው እምነቱን በተግባር መኖር ከቻለ፣ በሰዎች መካከል የሚታየውን ጭፍን ጥላቻን ለማስወገድ የሚያስችል ዕርዳታ በሚያደርግበት ጊዜ ነው። አንድ ደቀ መዝሙር ከመጥፎ ተግባራት በመራቅ፣ የግብዝነት ሕይወት በማስወገድ እውነተኛ ብርሃን የሚታይበትን ሕይወት በተግባር የሚያስመሰክር ከሆነ ለሌሎች ብርሃን ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ለሌሎች የምናበራው ብርሃን የራሳችን ብርሃን ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነው ብርሃን ነው። እኛ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ወደ ዓለም ሁሉ እንዲደርስ የምናደርግ የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን።

ዓለማዊ ሕይወታችን እንኳን ውጣ ውረድ እና ኃጢአት የበዛበት ቢሆንም፣ በዚህ ሳንደናገጥ እና ሳንፈራ በድፍረት እንድንኖር ኢየሱስ ክርስቶስ ይጋብዘናል። ዓለማችን አመጽ እና ጦርነት የበዛበት፣ ፍትህ የጎደለበት፣ ጭቆና እና ግፍ የሚፈጸምበት ቢሆንም ክርስቲያን በዚህ ሳይበገር፣ ከስቃይ ራሱን በመነጠል የራሱን ደህንነት ብቻ የሚመለከት መሆን የለበትም። ቤተክርስቲያንም ብትሆን ራሷን ከእግዚአብሔር ሕዝብ በመነጠል ከተሰጣት የወንጌል አገልግሎት ራሷን ወደ ጎን ልታደርግ አይገባትም። ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው የእራት ግብዣ ላይ ወደ አባቱ ዘንድ ባቀረበው የምስጋና ጸሎቱ  ደቀ መዛሙርቱን ከዓለም እንዳያወጣቸው በዓለም ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቆታል። ቤተክርስቲያንም ለድሆች እና አቅመ ደካማ ለሆኑት ቸርነትን እና ርህራሄን በማድረግ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችውን የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው የመሆን ምስክርነቷን በተግባር መግለጽ ይጠበቅባታል። ቤተክርስቲያን የድሆችን እና ከማሕበረሰቡ መካከል የተገለሉትን ሰዎች ጩሄት የምታዳምጥ ልትሆን ይገባል። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት በዘመናት ሁሉ እንዲገለጥ ለማድረግ የተጠራች ናትና።

በሕዝቦች መካከል የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው መሆን እንድንችል፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበትን መልካም ዜናን በቃል ሆነ በተግባር ለዓለም ሁሉ የምንገልጽበትን ኃይል በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን”።               

10 February 2020, 18:06