ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሰባት ቀናት ሐዋርያዊ ክንውኖች።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አደረጉ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ያከናወኑቸውን ሐዋርያው ተግባራት ስንመለከት “ውድ አማዞን” በማለት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ያለፈው ረቡዕ የካቲት 4/2012 ዓ. ም. የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የተደረገበት ዕለት፣ ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ የተካሄደው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በይፋ የተዘጋበት ዕለት እንደሆነ ተገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው የአካባቢው አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት፣ ምዕመናን እና ሕዝባዊ ተወካዮች በስፋት ተወያይተውባቸው ያቀረቡትን አራት ርዕሠ ጉዳዮች በማጽደቅ ይፋ አድረገዋል። እነርሱም የአማዞን አካባቢ አገሮች የተፈጥሮ ሃብት፣ የሕዝቦች ሥነ-ምህዳር፣ ባሕል እና የቅዱስ ወንጌል ምስክርነት የሚሉ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ኢየሱስ የትህትናን መንገድ አስተምሮናል”!

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣  ጥር 29/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተቅዳሴ ጸሎት ላይ  ከማር. 6፡14-29 ላይ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባደረጉት ስብከት  ኢየሱስ ክርስቶስ የትህትናን መንገድ እንዳስተማረን ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ እና መጥምቁ ዮሐንስን በሕይወታቸው ያሳዩትን ከፍተኛ የትህትና መንገድ መከተል ያስፈልጋል ብለዋል። የቤተክርስቲያን አባቶች ሳይቀር ለዓለማዊ ክብር ሳይገዙ በሕይወት ሂደት የሚያጋጥማቸውን ፈተና በትህትና መጋፈጥ እንደ ሚገባቸው ጨምረው ገልጸዋል። ለክርስቶስ ስንል “ውረደትን መቀበል” በፍጹም መፍራት የለብንም፣ ትሁታን እንሆን ዘንድ እንዲረዳን ጌታን ልንጠይቀው ይገባል፣ በእዚሁ መልኩ ብቻ ነው ኢየሱስን መምሰል የምንችለው ብለው፣ ትሁት ያልሆነ ክርስቲያን ክርስቲያን ነኝ ሊል በፍጹም አይችልም ብለዋል።

የሥርዓተ ትምህርት ስምምነቶች፣

ጥር 30/2012 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የትምህርት ደንቦችን በማስመልከት የተካሄደውን ጉባኤ ለተካፈሉት የትምህርት ባለሙያዎች ባሰሙት ንግግር አዲሱን ትውልድ ከአስተማሪዎቻቸው፣ ከወላጆቻቸው፣ ከባሕላዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት በሚያገኙት ድጋፍ በመታገዝ ከተቀረው ዓለም ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የመማምር ማስተማር ስምምነት በመቋረጡ ምክንያት ማሕበራዊ ግንኙነት እና ተሳትፎ መጓደሉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ትምህርትን ለማዳረስ እና ማሕበራዊ ተሳትፎን ለማሳደግ የአዕምሮን፣ የልብን እና የእጆቻችንን ቋንቋ በሚገባ መቻል ያስፈልጋል ብለዋል።    

“ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቀረት የሚቻለው በጋራ ጥረት ነው”።

ዓለም አቀፍ ጸረ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን ታስቦ በዋለበት ጥር 30/2012 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቀረት የሚቻለው በጋራ ጥረት ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በዓለማችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኛ ወንዶች እና ሴቶች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተጠውቁ እና በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው ይህን የማኅበረሰባችን አስከፊ ገጽታ በጽኑ መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት 2020 ዓ. ም. ከገባ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ የጸሎት መልዕክት ከጸሎት አስተባባሪ ክፍል ጋር በጋራ ያዘጋጁት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑ ታውቋል። በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚገኙት መምሪያዎች አንዱ የሆነው የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ የሚከታተል ቢሮ ይህን ወርሃዊ የጸሎት ዝግጅት ለማስተባበር የተነሳበትን ዓላም ሲገልስ በዚህ ወንጀል የተጠቁ ሰዎች ልዩ ትኩረት እንዳልተነፈጋቸው እና በሕዝቡም መካከል ያልተዘነጉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው ብሏል። የየካቲት ወር የጸሎት ሃሳብን የያዘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት፣ የዘመናችን አስከፊ ማሕበራዊ ችግር የሆነውን ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል የሚዋጋ “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን ማህበር ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን የሚያጠናክር መሆኑ ታውቋል። የጸሎት ሥነ ስርዓቱ ጥር 30/2012 ዓ. ም. በመላው ዓለም መከናወኑ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሶርያ የሚካሄድ ጦርነት እንዲያበቃ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 1/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸው አቅርበው በስፍራው ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው  የእግዚአብሔር መልአክ ጸሎት ካደረሱ በኋላ በሶርያ የሚካሄድ ጦርነት እንዲያበቃ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክትም በሶርያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ከባድ ጦርነት ምክንያት የብዙዎች ሕይወት አደጋ ውስጥ መውደቁን የተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች ይናገራሉ ብለው፣ በተለይም እናቶች እና ሕጻናት በስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ይህ አሰቃቂ ጦርነት ያበቃ ዘንድ፣ የጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት በሙሉ ወደ ጋራ ውይይት ተመልሰው እርቅን እና ሰላምን እንዲያወርዱ በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በመድገም፣ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት በከንቱ እንዳይጠፋ እና የሰብዓዊ መብት ሕጎችም እንዲከበሩ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው በጦርነት እና በአመጽ ውስጥ የሚገኘውን የሶርያ ሕዝብ በጸሎት እናስታውስ በማለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው ቅዱስነታቸው የጋራ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ አድርሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም የሕሙማንን አደራ እንድትቀበል በጸሎት ተማጸኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 3/2012 ዓ. ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ ተከብሮ የዋለውን የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ጸሎታቸው ቅድስት እመቤታችን ማርያም የሕሙማንን አደራ እንድትቀበል፣ ፈውስንም እንድታስገኚላቸው ተማጽነዋል። ለሕሙማን ሊደረግ የሚግባ ትክክለኛ የእንክብካቤ ዓይነትን አስመልከተው በጻፉት መልዕክታቸው፣ ፈውስ እና እንክብካቤ የሚያሻቸው ሕሙማን ብቻ ሳይሆኑ ከስጋዊ ሕመም እንዲፈወሱ አስፈላጊውን የሕክምና አገልጎት በመስጠት ላይ የሚገኙት እና ዕለታዊ እንክብካቤን በማድረግ ላይ የሚገኙትን ወላጅ ቤተሰብ ከፈጣሪ የተቀበሉትን የፍቅር አገልግሎት ጥሪያቸውን በታማኝነት እንዲያበረክቱ፣ መለኮታዊ ትዕዛዝን መሠረት በማድረግ፣ ቅዱስ ለሆነው ለሰው ልጅ ነፍስ ሊሰጥ ገሚገባውን ክብር እንዳያጓድሉባቸው አደራ ብለዋል። የሕክምና አገልግሎት በጥልቀት ማሰብንና ጥንቃቄን ይጠይቃል ያሉት ቅዱስነታቸው የሕክምና አገልግሎት ታካሚውን፣ የታካሚውን ቤተሰብ እና ሐኪሙንም ትልቅ ጥንቃቄን ይጠይቃል ብለው “ኤውታናሲያ”እና ነፍስን ከስጋ የመለየት የሕክምና ዘዴ ተቀባይነት የለውም ብለው ሕሙማን ከበሽታቸው የመፈወስ ዕድል የመነመነ ቢሆን እንኳ የሐኪሞች ዋና ተልዕኮ አንድ ሕሙማን ሕይወቱ እስከምታልፍ ድረስ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ሳያጓድሉ፣ ፍቅር በታከለበት አኳኋን እርዳታን መስጠት ነው ብለዋል። ለ28ኛ ጊዜ ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ድሆች እና አቅመ ደካሞች በቂ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው እንዲከበርላቸው፣ ማሕበራዊ ፍትህን እንዲያረጋግጡላቸው መንግሥታትን እና ማሕበራዊ ተቋማትን አደራ ብለው በተለይም በሕክምና አሰጣጥ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ለሕሙማን ፍቅርን እና ርህራሄን በመግለጽ፣ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌነታቸውን እንዲያሳዩ አደራ ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 February 2020, 16:56