ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን ከፊንላንድ ሉተራን ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮች ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን ከፊንላንድ ሉተራን ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮች ጋር  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቲያኖች አንዱ የሌላውን ሽክም የመሸከም ልምድ ማዳበር ይኖርባቸዋል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 08/2012 ዓ.ም በቫቲካን ከፊንላንድ ሉተራን ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮች ጋር ተገናኝተው በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው ግንኙነት መወያየታቸውን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደርጉትን ንግግር የጀመሩት “ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ሮም 1፡7) በሚለው በቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ቃል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “ክርስቲያኖች አንዱ የሌላውን ሸክም የመሸከም ልምድ ማዳበር ይኖርባቸዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ብዙ አለመግባባቶች በሚታዩባት በዛሬው ዓለማችን እኛ የሁለቱ ማለትም የካቶሊክ እና የሉቴራን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ተገናኝተን ለመወያየት በመቻላችን ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው አንዳችን ሌላውን ለማበረታታት እና የክርስቶስ ደቀመዝሙር እንደ መሆናችን መጠን ሁላችንም በእመንት መንገድ ላይ በጋራ ተያይዘን መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል።

ባለፈው እሑድ የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል አክብረነው ነበር (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በጥር 03/2012 ዓ.ም የተከበረውን የጥምቀት በዓል ማለታቸው ነው) በወቅቱ እኛ የተጠመቅንበትን እለት አስታውሰን ነበር በማለት ንግግራችውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች በጥምቀት ላገኙት ጸጋ እግዚኣብሔርን ማመስገን ይኖርባቸዋል ብለዋል። በእዚህም ምክንያት እግዚኣብሔር በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት ለሰጠን ጸጋ ምስጋና በምናቀርብበት ወቅት የተጠመቁ ክርስቲያኖች በሙሉ በክርስቶስ አንድ መሆናቸውን ያመለክታል በማለት ንግግራችውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ “ለኃጢያት ሥርዬት በሚፈጸመው ጥምቀት አምናለሁ” ብለን እምነታችንን መግለጻችን በራሱ ምስጢረ ጥምቀት ወደ ቅድስና የሚመራን መንገድ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ጽድቅ በቤተክርስቲያን እይታ በሚል አርእስት የካቶሊክ እና የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት ካደረጉት ውይይት በመቀጠል ይፋ በሆነው ሪፖርት ውስጥ “የተጠመቁ ሰዎች ከሌሎች ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር በመሆን ወደ ቅድስና በሚወስደው መንገድ ላይ የመጓዝ እድላቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ፣ ምክንያቱም የተጠመቁ ሰዎችን በሙሉ አንድ የሚያደርገው ክርስቶስ በመሆኑ የተነሳ ነው” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው በእዚህም የተነሳ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች በሙሉ በአንድነት መጓዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ክርስቲያኖች አንዱ የሌላውን ሽከም የመሸከም ልምድ ማዳበር እንደ ሚገባቸው በመጥቀስ ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቶስ መላውን ዓለም ሊቤዥ እንደ መጣ ሁሉ፣ ቤተክርስቲያን እና እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የምስራቹን ቃል በመስበክ የክርስቶስን ተልዕኮ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

“የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በእለት ተዕለት ሕይወታችን የእምነት ምስክርነታችን አካል ነው። ነገ (ጥር 09/2012 ዓ.ም) የሚጀመረው ለክርስቲያኖች ሕብረት ጸሎት የሚደረግበት ሳምንት ይህን ታላቅ ሥነ ምግባር ያሳየናል፣ እናም በእውነት ላይ ቆመን እንድንጓዝ ይመክራል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሐዋሪያው ጳውሎስ እና ከእርሱ ጋር የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመርከብ መሰበር አደጋ ባጋጠማቸው ወቅት (ሐዋ. 28፡ 2) በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እነርሱን ለማገልገል የተቀበሏቸውን የማልታ ደሴት ነዋሪዎችን በመጥቀስ “ያልተለመደ ደግነት አሳይተውናል” ብሎ መናግሩን በንግግራቸው አስታውሰዋል።

“የተጠመቅን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ክርስቶስን በቀጥታ ወይንም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሊገናኘን እንደሚፈልግ እናምናለን” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሰዎች ሀብታም እንጂ ድሃ አይሆኑም፣ የሚሰጥ ሁሉ በምላሹ ይቀበላል፣ ለሌሎች የምናሳየው ሰብአዊነት ስጋን ለብሶ ሰው በሆነው በእግዚአብሔር በጎነት ውስጥ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ እንድንካፈል ያደርገናል” ብለዋል።

“ውድ የፊንላንድ ተወካዮች፣ የቅዱስ ወንጌል አብሳሪዎች እንደ መሆናችን መጠን የእግዚአብሔርን መልካምነት እንቀበላለን፣ ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበሉ ማህበረሰቦች ውስጥ አብረን እየተጓዝን እንገኛለን” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ለተቀበሉት ምስጢረ ጥምቀት ምስጋና ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ብለዋል። ይህ የአመስጋኝነት ባሕሪይ ልባችንን እንደ ሚያስፋ እና ለባልንጀሮቻችን ልባችን ክፍት እንዲሆን እንደ ሚያደርግ በመግለጽ ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ ክርስቲያኖች በሙሉ በላቀ ሁኔታ “በአንድነት መቆም” ይኖርባቸዋል ብለዋል።

መንፈሳዊ የሆነ ሕብረት እና ሥነ-ምግባራዊ ምልከታን በተመለከተ የሚደረጉ ውይይቶች ይህንን “አንድ ላይ መቆም” ለማጠናከር ያገለግላሉ በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ለሁላችንም እግዚኣብሔር  የተትረፈረፈ ጸጋውን እና በረከቱን እንዲሰጥ እፀልያለሁ፣ እናንተም ለእኔ እንድትጸልዩ እጠይቃችኋለሁ፣ አመሰግናለሁ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 January 2020, 14:17