ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእግዚኣብሔር ቃል ኃይል ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሻገር ያደርገናል” አሉ!

የክርስቲያኑ ማኅበርሰብ እመነቱን ጠብቆ ይኖር ዘንድ ለማስቻል ይረዳው ዘንድ፣ ቤተ-ክርስቲያን በየወቅቱ የምዕመናኖቿን እምነት ማነቃቃት የሚችሉ ተግባራትን እና ዘዴዎችን በመጠቀም ምዕመናኖቿን በእምነት የማንቃት ተግባሯን አጠናክራ በመቀጠል ላይ እንደ ምትገኝ ይታወቃል። ከእነዚህም ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አነሳሽነት የጥር ወር ሦስተኛው ሳምንት ሰንበት “የእግዚኣብሔር ቃል እለተ ሰንበት” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ከወትሮ ለየት ባለ ሁኔታ ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልምዳቸውን ለማዳበር እና ሕይወት ሰጪ ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል ጋር ያላቸውን የሕይወት ትስስር ለማጎልበት እንዲረዳቸው በማሰብ በተለያዩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስናዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የሚነበብበት እና መጽሐፍ ቅዱስ ለምዕመናኑ የሚሰራጭበት እለት እንዲሆን በቅርቡ መወሰናቸው ይታወሳል። በእዚህም መሰረት “የእግዚኣብሔር ቃል እለተ ሰንበት” በመባል የሚጠራው የመጀምሪያው ሰንበት በጥር 17/2012 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ይህ “የእግዚኣብሔር ቃል እለተሰንበት” በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “የእግዚኣብሔር ቃል ኃይል ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሻገር ያደርገናል”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

“ኢየሱስ መስበክ ጀመረ” (ማቴ 4፡17)። በእነዚህ ቃላት ወንጌላዊው ማቴዎስ የኢየሱስን አገልግሎት ማስተዋወቅ ይጀምራል። የእግዚአብሔር ቃል የሆነው እርሱ በገዛ ቃሉ እና በራሱ ሕይወት ለእኛ ሊናገር መጣ። በዚህ የእግዚአብሔር ቃል ለየት ባለ ሁኔታ በሚከበርበት የመጀመሪያ እሑድ ወደ ኢየሱስ ስብከት ሥር መሰረት ወደ ሆነው ሕይወት ቃል ምንጭ እንሂድ። የዛሬ ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 4 ፡12-23) ኢየሱስ መስበክ የጀመረው እንዴት፣ የት እና ለማን እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል።

1.      እንዴት ተጀመረ? በጣም ቀላል በሆነ ሐረግ-“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴ 4፡17) በማለት ይጀምራል። መንግሥተ ሰማያት እንደ ቀረበች የሚነግረን ሁሉም የኢየሱስ ስብከቶች ዋና መልእክት ይህ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? መንግስተ ሰማያት ማለት የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት ነው፣ ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት በእኛ ላይ የሚንግሥበት ሁኔታ ማለት ነው። መንግሥተ ሰማያት እንደ ቀረበች፣ እግዚአብሔር ቅርብ መሆኑን ኢየሱስ ነግሮናል። ደስ የሚለው ነገር እና የመጀመሪያው መልእክት እነሆ! -እግዚአብሔር ከእኛ የራቀ አይደለም። በሰማይ የሚኖር እርሱ ወደ ምድር ወረደ፣ ሰው ሆነ። እሱ ግድግዳዎችን አፍርሷል እንዲሁም ርቀቶችን አጥብቧል። ምንም እንኳን እኛ ለእዚህ ጉዳይ የተገባን ባንሆንም እንኳን እርሱ እኛን ለመቀበል ወረደ። እግዚኣብሔር ለሕዝቡ ያሳየው ይህ ቅርበት እግዚኣብሔር ነገሮችን ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ያከናወነበትን መንገድ ያሳየናል። ለሕዝቡ እንዲህ አለ-“በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? እስቲ አስቡት-እኔ ቅርብ እንደሆንኩ አምላኩ ለእርሱ የሚቀርበው ብሔር የትኛው ነው?” (ዘዳግም 4፡ 7) በማለት ይናገራል። ይህ ቅርበት በኢየሱስ ውስጥ ሥጋ ሆነ።

እግዚአብሔር ሰው በመሆን በአካል ሊጎበኘን መምጣቱ ለእኛ አስደሳች የሆነ መልእክት ነው። እሱ የሰውንነታችንን ሁኔታ የተቀበለው በግዴታ ሳይሆን በፍቅር ነው። ለፍቅር ሲል እርሱ የእኛን ሰብዓዊ ተፈጥሮዋችንን ወሰደ። እግዚአብሔር ሰብዓዊ የሆነ ተፈጥሮአችንን የወሰደበት ምክንያት እርሱ ስለሚወደን እና ድህንነትን በነጻ ሊሰጠን ፈልጎ ነው። እርሱ ከእኛ ጋር ለመሆን እና የህይወትን ውበት ማጣጣም እንችል ዘንድ፣ የልብ ሰላም እንድናገኝ፣ ይቅር መባባል እንድንችል እና እንደተወደድን ሆኖ እንዲሰማን ይፈልጋል።

ኢየሱስ “ንስሐ” ግቡ ያለበትን ምክንያት በሌላ መንገድ ስንረዳው “ሕይወትህን ቀይር” የሚለውን ቀጥተኛ ጥርጉም እናገኛለን። አዲስ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ለመከትል ሕይወትህን ለውጥ ይለናል። ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እነዚህን ቃልት ለእኛ ይናገራል። ለራስህ የምትኖርበት ጊዜ አብቅቶ ከእግዚአብሄር እና ከሌሎች ጋር በፍቅር የምትኖርበት ጊዜ አሁን ነው ይለናል። ዛሬ ኢየሱስ እነዚያን ተመሳሳይ ቃላት ይናገራል “አይዞህ ፣ እኔ እዚህ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ባንተ ውስጥ እንድገባ ፍቀድልኝና ሕይወትህን ልለውጥ” ይለናል። ኢየሱስ በርህን ያንኳኳል። እርሱ ከጎንህ መሆኑን እንድታውቅ እሱ ልክ እንደ አንድ የፍቅር ደብዳቤ በሚመስል መልኩ መልእክቱን የሚጽፍልህ በእዚህ ምክንያት ነው። ቃሉ ያጽናናናል እናም ያበረታታናል። በተመሳሳይ ጊዜ ቃሉ እኛን ይገዳደረናል፣ ከራስ ወዳድነት እስራት ነፃ ያወጣናል፣ ለውጥ እንድናመጣም ይረዳናል፣ ቃሉ ሕይወታችንን የመለወጥ እና ከጨለማ ወደ ብርሃን እኛን የማውጣት ኃይል አለውና። ይህ የቃሉ ኃይል ነው።

2.      ኢየሱስ ስብከቱን የት እንደጀመረ ከተመለከትን፣ እርሱ በዚያን ጊዜ “በጨለማ ውስጥ ነበሩ” ብሎ ካሰባቸው ስፍራዎች እንደ ጀመረ እንመለከታለን። የመጀመሪያው ምንባብ (ኢሳያስ 8፡23-9:3) እና በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 4፡12-23) “በሞት ጥላ እና በጨለማ ውስጥ ስለተቀመጡ” ሰዎች ይናገራሉ። እነሱ “የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣ ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣ በጨለማ የሚኖር ሕዝብ፣ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ላለው፣ ብርሃን ወጣለት” (ማቴ 4፡15-16) በማለት ይናገራል። ኢየሱስ የስብከት አገልግሎቱን የጀመረበት የአህዛብ ገሊላ ተብሎ ስም የተሰጠው ስፍራ የተለያዩ አገር ሰዎች የሚኖሩበት፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች መነሻ ስፍራ ስለነበረ ነው። ስፍራው በእውነቱ "በባህር አጠገብ" የሚገኝ መተላለፊያ የነበረ ቦታ ነበር።  ዓሣ አጥማጆች ፣ ነጋዴዎችና የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ እዚያ ይኖሩ ነበር። የተመረጠው ህዝብ እና ሃይማኖታዊ ንፅህና የሚያገኝበት ቦታ በእርግጠኝነት አልነበረም። ሆኖም ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ስብከቱን ጀመረ እንጂ ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ዳርቻ አልጀመረም፣ ነገር ግን በተቃራኒው ከገጠራማ ስፍራ፣ ከአሕዛብ ገሊላ፣ ከድንበር ክልል አከባቢ በአጠቃላይ ስብከቱን የጀመረው ራቅ ካሉ ስፍራዎች ነበር።

 

እዚህ ጋር ለእኛ የሚሆን አንድ መልእክት አለ፣ የመዳን ቃል በመጀምሪያ የሚፈልገው ያልታወቁ ፣ ንጹህ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ቦታዎችን አይደለም። ይልቁኑ በሕይወታችን ውስጥ ወደ ውስብስብ እና ምስጢራዊ ስፍራዎች ይገባል። እንዲያውም እግዚአብሔር መቼም ቢሆን ወደ እዚያ አይሄድም ብለን ወደ ገመትናቸው ስፍራዎች እንደ ሚሄድ እንገነዘባለን። ሆኖም ግራ መጋባታችንን፣ ጨለማ ጎናችንን እና ድብቅ የሆነውን መንታ ማንነታችን እንዳይመለከት በሩን የምንዘጋው እኛ ነን። እውነቱን በልባችን ውስጥ ደብቀን እና ልባችንን ከውስጥ ቆልፈን እንዲያው ለይስሙላ አስለቺ የሆኑ ጸሎቶችን ይዘን ወደ ጌታ እንቀርባለን። ይህም ድብቅ የሆነ ግብዝነት ነው። ነገር ግን የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደሚናገረው “ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር” (ማቴ 4፡23) በማለት ይናገራል። ኢየሱስ ያንን የተለያዩ ሰዎች የሚኖሩበትን እና የተወሳሰበ ክልል አልፎበታል። በተመሳሳይ መንገድ ፣ የልባችንን ዳርቻ ለመዳሰስ እና በጣም አስቸጋሪ እና ውስብስብ ወደ ሆነ የህይወታችን ማዕዘኖች ለመግባት አልፈራም። የእርሱ ምህረት ብቻ እኛን ሊፈውስ እንደሚችል ያውቃል፣ የእርሱ መገኘት ብቻ ሊቀይረን እና ቃሉ ብቻውን ሊያድሰን ይችላል። ስለዚህ በልባችን ውስጥ ያለውን የማጥመጃ መንገዶችን እንከፍትለት፣ እኛ የማናያቸው ወይም እኛ የምንደብቃቸው - በውስጣችን የሚገኙትን ጉዶች እንዲጎበኝ  “ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ” ሕያው የሆነውን ፣ የሚሠራ ፣ የልቡን አሳብ መርምሮ የሚያውቀውን (የመፍቻ ቃል) የሆነውን ቃሉን በልባችን እንቀበል” (ዕብ. 4 12)።

3.      በመጨረሻም፣ ኢየሱስ መናገር የጀመረው ለማን ነው? ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ “ሁለት ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር። ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው” (ማቴ 4፡ 18-19)። የመጀመሪያው ጥሪ የደረሳቸው ሰዎች ዓሣ አጥማጆች ነበሩ እንጂ በሚያቀርቡት ምርጥ ጸሎት የተነሳ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚኖሩ በጥንቃቄ የተመረጡ ወይም ቀናተኛ የተባሉ ሰዎች ግን አልነበሩም፣ ነገር ግን ተራ የሆኑ ሰዎች ነበሩ።

 

እስቲ ኢየሱስ ምን እንዳላቸው እንመልከት፣ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ ይላቸዋል። እሱ የዓሳ አጥማጆች ሊረዱት በሚገባው ቋንቋ ይናገራቸዋል። ሕይወታቸው ቅጽበታዊ በሆነ ሁኔታ ይቀየራል። በተልእኮው ውስጥ ተካፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ በነበሩበት እና ባሉበት ሁኔታ ይጠራቸዋል። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት (ቁ. 20)። ለምንድነው እርሱ ወዲያውኑ የተከተሉት? በቀላሉ እንደተሳቡ ስለተሰማቸው ነው። ትእዛዝ ስላልተሰጣቸው እና የእርሱን ትእዛዝ ስለተቀበሉ ብቻ ቸኩለው አልተነሱም፣ ነገር ግን በፍቅሩ ስለተሳቡ ነው። ኢየሱስን ለመከተል መልካም ሥራዎች ብቻ በቂ አይደሉም፣ ጥሪውን በየቀኑ ማዳመጥ አለብን። እርሱን ለሰሙት ደቀ-መዛሙርት እንዳደረገው ሁሉ እኛን የሚያውቀን እና ሙሉ በሙሉ የሚወደን እርሱ ወደ ጥልቅ ሕይወት ውስጥ እንድንገባ ይመራናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሺዎች ከሚቆጠሩ ከሌሎች ቃላቶች መካከል የእርሱን ሕይወት ሰጪ የሆነ ድምጽ ለይተን መስማት እንችል ዘንድ እንዲረዳን ልንጠይቀው የገባል።

 

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ለእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን ስፍራ እንስጠው! በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናንብብ። በቅዱስ ወንጌል እንጀምር-በጠረጴዛችን ላይ ቅዱስ ወንጌሉን ክፍት አድርገን እናስቀምጠው፣ በኪሳችን ወይም በሻንጣችን ውስጥ እንያዘው፣ በሞባይል ስልካችን ላይ እንጫነው እና እናንብበው፣ በእየቀኑ ቃሉ እንዲያነቃቃን እንፍቀድለት። እግዚአብሄር ወደ እኛ ቅርብ መሆኑን ፣ ጨለማችንን የሚያስወግድ እና በታላቅ ፍቅር ህይወታችንን ወደ ጥልቅ ውሀዎች እንደሚወስድ እናውቃለን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

 

26 January 2020, 14:20