ፈልግ

በቅ. ጳውሎስ ባዚሊካ የቀረበ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ ሥርዓት፣ በቅ. ጳውሎስ ባዚሊካ የቀረበ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ ሥርዓት፣ 

“በክርስቲያኖች ሆነ በሌሎች እምነቶች መካከል የመልካም አቀባበል ባሕልን እናሳድግ”።

ለክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት በየዓመቱ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል። ዘንድሮ ከጥር 9/2012 ዓ. ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የቆየ የጸሎት ሥነ ሥርዓት በልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች ሲደረግ ቆይቷል። ዛሬ ጥር 16/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ በተዘጋጀው የጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት “በክርስቲያኖች እና በሌሎች እምነቶችም የመልካም አቀባበል ባሕል ሊያድግ ይገባል ማለታቸው ታውቋል። ክቡራት እና ክቡራን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“እስረኛውን ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮም በምታመጣው መርከብ ውስጥ ሦስት ዓይነት ተሳፋሪዎች ነበሩባት። ከእነዚህ ተሳፋሪዎች መካከል ሃይለኛው የወታደሮች ቡድን ነው። ሁለተኛው የመርከቧን ጉዞ የሚቆጣጠሩ እና በተለያዩ የመርከብ ውስጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ናቸው። ሶስተኛው፣ ምንም ኃይል ያልነበረው እና የታዘዘውን ሁሉ የሚፈጽም ቡድን የእስረኛው ቡድን ነበር። 

መርከቧ በማልታ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ባጋጠማት ማዕበል እና ዝናብ ምክንያት ጉዞዋን አቋርጣ ለበርካታ ቀናት ቆማ በቆየች በት ጊዜ ወታደሮች በመርከቧ ውስጥ የነበሩ እስረኞች ከማምለጣቸው አስቀድመው ሊገድሏቸው አሰቡ። ነገር ግን ጳውሎስ እንዳይገደል በሚለው በወታደሮች አዛዥ ትዕዛዝ ምክንያት ሃሳባቸው እንዲቀየር ተደረገ። በመርከቧ የተሳፈሩት በሙሉ ተስፋ በቆረጡበት ጊዜ፣ በድንጋጤ እና በፍርሃት በተጨነቁበት ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ የሆነው ጳውሎስ፣ ለተሳፋሪዎች በሙሉ አንድ አጽናኝ መልዕክት ተናገረ። ይህም ከመልአክ የተነገረለት መሆኑን በመግለጽ፥ “ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል” አለኝ። (የሐዋ. 27:24)

በጳውሎስ መልዕክት ብርታትን ያገኙት የመርከቧ ተሳፋሪዎች፣ አስፈሪው እና አስጨናቂው ጊዜ አልፎ፣ ከመርከቧ ወጥተው ወደ ማልታ በገቡ ጊዜ ከማልታ ደሴት ነዋሪዎች በኩል የተደረገላቸውን ትህትና የተሞላበት መልካም አቀባበል እና መስተንግዶን ተመልክተው ተደሰቱ። ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የሚፈጸመው የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት ሃሳብ መነሻውን ያገኘው ከዚህ ታሪክ ነው።  

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው ይህ ታሪክ የእግዚአብሔር ዕቅድ ስለ ሆነው ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ይናገራል። ይህ ታሪክ በመጀመሪያ ደረጃ የሚናገረን፣ ለሌሎች ለማካፈል ምንም ነገር የሌላቸው፣ ነገር ግን ተስፋቸውን፣ ሃብታቸውን እና መመኪያቸውን፣ ለሰው ልጅ በሙሉ አጽናኝ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ያደረጉ መኖራቸውን ያስረዳል። የተለያዩ የክርስቲያን ማሕበረሰብን፣ በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑትን፣ በዓለማዊ ዓይን ሲመለከቷቸው ምንም የማይጠቅሙ መስለው የሚታዩትን እንኳ ብናስብ፥ መንፈስ ቅዱስን ኃይላቸው ካደረጉ፣ ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራቸው ያለውን ፍቅር በተግባር የሚገልጹ ከሆነ፣ በእርግጥም እነዚህ ክርስቲያኖች መላውን የክርስቲያን ማሕበረሰብ ሊጠቅም የሚችል መልዕክት አላቸው። የቅዱስ ጳውሎስ የመርከብ ላይ ጉዞ ታሪክ እንደሚነግረን፣ የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል ለአህዛብ የሚመሰክሩት ድሆች እና አቅመ ደካሞች ናቸው። እግዚአብሔር የሚደሰተው ዓለም በኃያላን ጉልበት ሳይሆን በመስቀሉ ኃይል ድነትን ሲያገኝ ነው።                   

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ ምልዕክቱ በምዕ. 1:20-25 ላይ፥ ጠቢብ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገምን? ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል። መቼም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይበረታል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል። በዓለማዊ ነገሮች እንዳንታለል እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ይልቅስ ከድሆች እና አቅመ ደካሞች አንደበት የሚወጣውን ማዳመጥ ይገባል። ምክንያቱም እግዚአብሔር መልዕክቱ በእነዚህ ልጁን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በሚመስሉ አቅመ ደካሞች በኩል እንዲደርስ ይወዳልና። 

የሐዋ. ሥራ መጽሐፍ የሚያስታውሰውን ሌላው ሁለተኛው መልዕክት የእግዚአብሔር ቀዳሚ ዓላማ የሰው ልጅ በሙሉ ይድን ዘንድ ነው። መልአኩ በመርከቧ ውስጥ በሞት አፋፍ ውስጥ ለነበረው ጳውሎስ የተናገረውም እግዚአብሔር ማዳኑን እንደላከላቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞ. በላከው የመጀመሪያ ምልዕክ፣ ምዕ. 2:4 ላይ፥ “እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል” ይላል። ይህ መልዕክት ደግሞ ለአንድ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የክርስቲያን ማሕበረሰብ ማሰብ እንዳለብን፣ ለሰው ልጅ በሙሉ የሞተውን ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከት እንዳለብን ያሳስበናል። ይህን የምናደርግ ከሆነ በመካከላችን የሚታየውን ልዩነት ማስወገድ እንችላለን። ጳውሎስ በተሳፈረባት መርከብ የነበሩ የመርከቧ ሰራተኞች ከደረሰባቸው አደጋ ለመትረፍ፣ በውስጧ የነበሩትን ሌሎች ተሳፋሪዎችን ለማዳን የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ ነበር። በክርስቲያኖች መካከልም እያንዳንዱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ከእግዚአብሔር ባገኘው የጸጋ ስጦታ በመታገዝ ሌላውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማገዝ ያስፈልጋል።

ይዚህ ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት መሪ ሃሳብ በሦስተኛ መልዕክቱ፣ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋ. ሥራ መጽሐፍ፣ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ፣ የማልታ ደሴት ነዋሪዎች ያደረጉትን፣ ትህትና የተሞላበት መልካም አቀባበል እና መስተንግዶን ያስታውሰናል። በሐዋ. 28:2 ላይ “የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን” ይላል። የእሳቱ ሙቀት በሰዎች መካከል የተፈጠረው ኅብረት፣ አንድ የሚያደርጋቸውን የፍቅር አንድነት ያመለክታል። በተደረገላቸው መልካም መስተንጎዶ የተደሰቱት በሙሉ ከጳውሎስ ጋር ሆነው ወደ ጣሊያን ለመድረስ ጉዞ መቀጠላቸውን እናነባለን።

ከዚህ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት፣ የበለጠ እንግዳ ተቀባዮች መሆንን እንማራለን። ከሁሉ በፊት በክርስቲያኖች መካከል በእንግድነት መቀባበልን፣ ቀጥሎም ለሌሎች እምነቶች ተከታዮች መልካም አቀባበል ማድረግ እንደሚገባን እንማራለን። በእንግድነት መቀባበል የቆየ የክርስትና እምነት ባሕል ነው። የቀድሞ የእምነት አባቶቻችን ተቸግሮ የእኛን እርዳታ ለሚጠይቅ ሁሉ እገዛን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስተምረውናል። ይህን ክርስቲያናዊ ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንጂ እንዲጠፋ ማድረግ የለብንም።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ይህን ሃሳብ መሰረት በማድረግ ዛሬ በመካከላችን ለሚገኙት፣ የቁንስጥንጥኒያው የውህደት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ተወካይ ለሆኑት ለብጹዕ ወ ቅዱስ ጀናዲዎስ፣ በሮም የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳሳ ተወካይ ለሆኑት፣ ለብጹዕ አቡንነ ያን ኤርነስት እና ለልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ለክርስቲያን ማኅበረሰብ ተወካዮች በሙሉ ልባዊ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። እንደዚሁም በካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ያላቸውን እውቀት ለማሳደግ በሮም ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት የቦሰይ ክርስቲያኖች አንድነት ተቋም ተማሪዎች፣ ከምስራቃዊያን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ለተገኛችሁት እና በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን አንድነት ከሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ለተገኛችሁት በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ሙሉ አንድነትን ማግኘት የምንችልበትን ጸጋ እግዚአብሔር እንዲሰጠን፣ ሳንታክት ዘወትር በሕብረት ጸሎታችንን ወደ እርሱ ዘንድ እናቅርብ”።            

25 January 2020, 17:25