ፈልግ

አንድ የተፈተነ ክርስቲያን ሥቃይ ምን እንደሆነ ስለሚያውቅ የሌሎች ሰዎችን መከራ ይጋራል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 29/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደርገው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው  “ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንት ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነሣችሁና ይህ ጒዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር። አሁንም ቢሆን አይዟችሁ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና። በትላንትናዋ ሌሊት፣ የእርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣ ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ ” (የሐዋ. 27፡21-24) በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ ሲሆን “ «  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 29/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጨረሻው ክፍል ውስጥ ቅዱስ ወንጌል በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በባሕር ላይ ጭምር ያደርገውን ጉዞ የሚያመለክት ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስን ከቂሳርያ ወደ ሮም በመርከብ በመጓዝ (ሐዋ. 27 1-28) ከሙታን የተነሳው ጌታ  “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ » (የሐዋ. 1፡18) ብሎ የተናገረውን ቃል በተግባር ላይ ሲያውለው እንመለከታለን። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን አንብቡትና ቅዱስ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታግዞ ለሁሉም የሰው ልጅ እንዴት እንደ ሚዳረስ እና እንዴት ዓለማቀፋዊ እንደ ሚሆን ተመልከቱ።

በባሕር ላይ የሚደርገው ቀዘፋ ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ መጥፎ ሁኔታዎች አጋጥሞታል። ጉዞው አደገኛ በመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ በመርከብ መጓዛቸውን እንዳይቀጥሉ መክሮዋቸው የነበረ ሲሆን ነገር ግን የመቶ አለቃው ይህንን ምክር ከቁም ነገር ሳይቆጥር በመርከቡ ካፒቴን ላይ በመተማመን ጉዞውን እንዲቀጥል ያደርጋል። ጉዞው እንደቀጠለ ኃይለኛ ነፋስ ተነሳ፣ መርከበኞቹ መርከቧን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ ጉዞው አደገኛ ይሆናል።

ሞት እየቀረበ መምጣቱን ተመልክተው ተስፋ እየቆረጡ በነበረበት ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ጣልቃ ይገባል። ስለዚህ ቀድም ሲል ያዳመጥነውን ነገር በመናገር በትላንትናዋ ሌሊት፣ የእርሱ የሆኑትንና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣ ‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ” (የሐዋ 27፡23-24) ብሎ በመናገር ለባልደረባዎቹ ማረጋገጫ ሰጣቸው። በመከራ ጊዜም ቢሆን ሐዋርያው ጳውሎስ የሌሎችን ሕይወት መንከባከብ እና የእነርሱን ተስፋ ከማነቃቃት በጭራሽ ባዝኖ አያውቅም።

ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ሮም የሚያደርገው ጉዞ እቅድ የሚመራው፣ እርሱን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ሳይቀር የሚመራው፣ መርከቧን ከመስጠም አደጋ የሚታደገው የስብከተ ወንጌል አግልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርገውን አጠቃላይ የሆነ ምስል ሉቃስ ያሳየናል።

በመርከቧ ላይ ሊደርስ የነበረውን አደጋ ተከትሎ በማልታ ደሴት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ያድርጉላቸዋል። በማልታ ደሴት ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ጥሩ፣ ጨዋዎች፣ የዋሆች እና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ሰዎች ናቸው። የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩዋቸው፣ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላቸውንም ተቀበሉ። በውቅቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር መሆኑን ለመመስከር ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ይጨምር ነበር። በእዚያን ጊዜ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀችበት። የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር አደጋ ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጒዳት አልደረሰበትም። ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ ጳውሎስን ክፉ አድራጊ ሰው ከመቁጠር ይልቅ እንደ መለኮታዊ ሰው አድርገውት መቁጠር ጀመሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ ያ ጸጋ የተሰጠው ጳውሎስን በጉዞ ወቅት ሲረዳው ከነበረው ከጌታ ጸጋ የተሰጠው ሲሆን ከሙታን የተነሳው ጌታ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ” (ማር 16፡18) ብሎ ጌታ ከተናገረው ቃል የተነሳ የተከናወነ ነው።  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማልታ ምንም ዓይነት እፉኝት እንደሌለ ታሪክ ይናገራል - እነዚህ በጣም ጥሩ ሕዝቦች ላደርጉት የሞቀ አቀባበል እግዚአብሔር የሰጣቸው በረከት ነው።

በርግጥ በማልታ መቆየት ጳውሎስ ለሚያስተላልፈው ቃል “ሥጋን” ለመስጠት እና የታመሙትን ለመፈወስ የርህራሄ አገልግሎት ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሩዋል። እናም ይህ የወንጌል ህግ ነው - አንድ አማኝ መዳንን ሲያገኝ ፣ እሱ ያ መዳን የራሱ የግሉ ብቻ እንዲሆን አያደርግም ፣ ነገር ግን እንዲሰራጭ ያደርገዋል። “መልካም የሆነ ነገር ሁሉ ራሱን ለሌሎች ማጋራት ይጀምራል። እያንዳንዱ የእውነት እና የውበት ልምምድ ራሱን ለማስፋፋት ይፈልጋል፣ እናም ጥልቅ ነፃነትን ያገኘ ማንኛውም ሰው በሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች ፊት የላቀ የመተማመን ስሜት ያገኛል። አንድ የተፈተነ ክርስቲያን በእርግጥም ሥቃይ ምን እንደሆነ ስለሚያውቅ ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመተባበር ልቡን ክፍት ማደረግ ይችላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ፈተናዎቻችንን በሙሉ በክርስቶስ ላይ በመጫን እንድንኖር ያስተምረናል፣ “በሚታዩት ውድቀቶችም እንኳ ቢሆን “በማንኛውም ሁኔታ ሊፈፀም የሚችል በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት” ለማዳበር ለእግዚአብሄር እና ለፍቅር ራሱን የሚሰጥ በእርግጠኛነት ፍሬያማ እንደ ሚሆን ያስተምረናል። ፍቅር ሁል ጊዜ ፍሬያማ ነው፣ እግዚአብሔርን መውደድ ሁል ጊዜ ፍሬያማ ያደርጋል፣ እናም በጌታ እንድንወሰድ ለእርሱ ከፈቀድንለት የጌታን ስጦታዎች ለመቀበል እንችላለን፣ ዘወትር ለአምላክ ያለን ፍቅር የላቀ ይሆናል።

ዛሬ በእምነታችን ላይ የሚደርሰውን እያንዳንዱን ፈተና ተቋቁመን መኖር እንችል ዘንድ የጌታን እርዳታ እንማጸን፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ አደጋ ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ማሰብ እንድንችል፣ በየወደቦቻችን ላይ እጅግ በጣም ደክመው ለደረሱ ሰዎች ማሰብ እንችል ዘንድ፣ ከኢየሱስ ጋር በምንገናኝበት ወቅት በምናገኘው ፍቅር ተሞልተን ወንድሞቻችንን መቀበል እንችል ዘንድ በእርሱ ፍቅር እንወሰድ። ምክንያቱም እኛን ከቸልተኝነት እና ኢሰብአዊነት የሚያድነው ይህ ነውና።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
08 January 2020, 16:09