ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “እንደ ሰብዓ ሰገል ፣ ሕይወታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ለውጥን ሊያገኝ ይችላል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰብዓ ሰገል ሕጻኑ ኢየሱስን የጎበኙበትን፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር ሆነው ማስታወሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ዕለቱን በማስታወስ በአደባባዩ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ስብከታቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ በማቴ. 2: 1-12 ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸው “እንደ ሰብዓ ሰገል ሕይወታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ለውጥን ያገኛል” ብለዋል። ክቡራት እና የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ከዚህ በታች፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው አርቅርበንላችኋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣

በዛሬው ዕለት ጠቢባን ከምሥራቅ ተነስተው፣ ኮከብ የሚያሳያቸውን አቅጣጫ ተከትለው፣ በቤተልሔም የሚገኘውን፣ ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ የጎበኙበትን ሁኔታ እናስታውሳለን። ወንጌላዊው ማቴዎስ በጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በምዕ. 2: 1-12 ላይ የተገለጸውን ስንመለከት፣ ወንጌላዊው ማቴ. በቁ. 12 “እግዚአብሔርም ከምሥራቅ ጠቢባን ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ” የሚለውን እናገኛለን። መንገድ አሳብረው ወይም መንገድ ቀይረው የሚለውን እናገኛለን።

ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማግኘት፣ እርሱን ለማወቅ ከሩቅ አገር ረጅም መንገድ ተጉዘው ወደ ቤተልሔም የመጡት ጠቢባን በእርግጥም እጅግ ደክሟቸው እንደነበር እንገምታለን። ወደ ቤተልሔም ደርሰው ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ባገኙት ጊዜ በፊቱ ቀርበው ሰገዱለት፣ የከበረ ስጦታንም፣ ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። ቀጥለውም ብዙም ሳይቆዩ ወደ መጡበት አገር ለመመለስ ተነሱ። ከሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደረጉት ቆይታ እና ከእርሱ ጋር ያደረጉት ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል።

ከኢየሱስ ጋር መገናኘታቸው እዚያው ከእርሱ ጋር እንዲቆዩ ሳይሆን፣ ያዩትን ሁሉ፣ የተሰማቸውን ታላቅ ውስጣዊ ደስታን ቶሎ ብለው ወደ አገራቸው ሄደው ለሕዝባቸው እንዲናገሩ ቀሰቀሳቸው። በዚህ ክስተት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በዘመናት ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን ለሕዝቡ ለመግለጥ ያደረገበትን መንገድ እናገኛለን። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነጻ ያደርገናል እንጂ በምንም እንድንሰናከል አያደርገንም። በነጻነት መንገድ እንድንጓዝ ያደርገናል እንጂ አስሮን አይዘንም። ወደ ተለመደው፣ ወደ ምናውቀው፣ ከስጋት እና ከፍራቻ ነጻ ወደ ምንሆንበት መኖሪያ ሥፍራችን ይመልሰናል። በምንኖርበት አካባቢ ምንም ለውጥ አይኖርም ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንገናኝ፣ ከቀድሞ ማንነታችን ተለውጠን እንገኛለን። ከኢየሱስ ጋር የምናደርገው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ይለውጠናል። ወንጌላዊው ማቴዎስም፣ በምዕ. 2:12 ላይ፣ ኢየሱስን ያገኙት ጠቢባን ወደ አገራቸው ሲመለሱ መንገድ አሳብረው፣ መንገድ ቀይረው ሄዱ በማለት ይገልጸዋል። እነዚያ ጠቢባን፣ መለኩ እንደነገራቸው ወደ ሄሮድስ እና ወደ ስልጣኑ የሚወስዳቸውን መንገድ ትተው በሌላ መንገድ መጓዝን መረጡ።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምናደረገው ማንኛውም ግንኙነት፣ ቀድሞ ከምንጓዝበት ወጥተን በተለየ መንገድ እንድንጓዝ ያደርገናል። ምክንያቱም ከኢየሱስ በኩል ልብን የሚፈውስ፣ ከፋትን የሚያስወግድ መልካም ኃይል እናገኛለንና።

ከምሥራቅ በኩል ተነስተው ወደ ቤተልሔም የተጓዙት ጠቢባን ያደረጉትን የጉዞ ሂደት ስንመለከት ሁለት ነገሮችን እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሲሆን ሁለተኛው ደግም ወደ አገራቸው ለመመለስ ሌላ አዲስ መንገድ መውሰዳቸውን እናያለን። ከዚህ ሁኔታ መረዳት የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ከነበርንበት ያልተስተካከለ ሕይወት ለመውጣት የሚያስችለን ቁርጥ ውሳኔ የሚመጣው ከራሳችን እንደሆነ፣ በዙሪያችን ባለው እውነታ ላይ ለመፍረድ በሚያስችሉ መስፈርቶች ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝበናል። በእውነተኛ እግዚአብሔር እና ገንዘብን ፣ ሥልጣንን ፣ እና ታዋቂነትን በመሳሰሉ አታላይ ጣኦቶች መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። የማይሆን ተስፋን የሚሰጡ፣ ቃል የሚገቡ ጣኦቶች፣ ጠንቋዮች እና አስማተኞችም ብዙዎች ናቸው። እነዚህ ጣኦቶች ታዲያ ዘወትር በውስጣችን ተዘግተን፣ በራሳችን ተወስነን እንድንኖር ያደርጉናል። እኛም በእነርሱ በመሸነፍ እጅ እንሰጣለን። በእውነት የምናመልከው እግዚአብሔር አምላካችን ነጻነት ሰጥቶን፤ በነጻነት የምንጓዝበትን መንገድ ያዘጋጅልናል። ምክንያቱም እርሱ ዘወትር ከእኛ ጋር በመሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናድግ ያደርገናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈስዊ ግኑኙነት የምትፈጥር ከሆነ፣ ይህን አስተውል፥ ቀድሞ ወደ ነበርክበት ቦታ መመለስ ይኖርብሃል። ወደ ቀድሞ ቦታ ለመመለስ የሚወስደው መንገድ ግን ቀድሞ ከምትረማመድበት መንገድ የተለየ፣ የሕይወት አካሄድም ሙሉ በሙሉ የተለየ መሆን አለበት። ልባችንን በመለወጥ፣ ወደዚህ መንገድ የሚመራን፣ አዲስ ሕይወት የሚሰጠን፣ መንፈስ ቅዱስ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።      

በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ተለውጠን፣ በአዲስ ሕይወት የእርሱ ምስክሮች ለመሆን እንድንበቃ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን”።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
07 January 2020, 15:58