ፈልግ

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን፣ ሂሮሺማ የሰላም ምልክት ብርሃን ሲያበሩ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን፣ ሂሮሺማ የሰላም ምልክት ብርሃን ሲያበሩ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “የሰላም ተስፋ ምንጭ ኢየሱስ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 22/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን 53ኛ ዓለም አለም የሰላም ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። የጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት የገባበት ታኅሳስ 22/2012 ዓ. ም. የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል የተከበረበት ዕለት መሆኑም ታውቋል። ቅዱስነታቸው ዘንድሮ ባስተላለፉት ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክት ከዚህ በፊት ያስተላለፉቸውን ዓመታዊ የሰላም መልዕክታቸውን አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ ዓመታት ባስተላለፏቸው የሰላም መልዕክቶች በኩል የዘመናችን ተግዳሮቶች፣ ከእነዚህም መካከል ለሰላም ማጣት መፍትሄው የሰላም ተስፋ ምንጭ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

1.  ሰላም እንቅፋቶችን የምናልፍበት የተስፋ ጉዞ ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዘንድሮ የሰላም መልዕክታቸው አማካይነት ሰላም ለሰው ልጆች በሙሉ ውድ የተስፋ ምንጭ መሆኑንም አስረድተዋል። ከተለያዩ ችግሮች ለመላቀቅ የሚያስችል የሰላም ጥረት ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም መልካም ውጤት የሚገኝበት ብቸኛው ግባችን ይህ ከሆነ ጥረታችን ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል። ተስፋ ሁል ጊዜ የማንወጣው መስሎ የሚታየንን ችግር በአሸናፊነት እንድንጨርስ የሚገፋፋን ኃይል ነው ብለዋል። በዘመናችን ውስጥ የተካሄዱት አመጾች እና አስከፊ ጦርነቶች፣ በተለይም አቅም በሌላቸው እና ደሃ በሆነው ማሕበረሰብ መካከል መጥፎ ትዝታን ጥሏል ያሉት ቅዱስነታቸው ጥላቻን እና አመጽን ከሚቀሰቅሱ የጭቆና እና የምዝበራ አገዛዝ መላቀቅ ለበርካታ አገሮች አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ዛሬም ቢሆን በበርካታ አገሮች ውስጥ ሰብዓዊ ክብር መጣሱን አስታውሰው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ወንዶች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ማኅበራዊ አንድነትን፣ የእምነት ነጻነትን እና የመልካም ሕይወት ተስፋን ተነፍገው ለሐዘን፣ ለፍትህ ማጣት እና ለጥቃት የተጋለጡ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ላይ የሚገኙ የጭካኔ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በመምጣት በሰው ልጆች ሕይወት እና ስጋ ላይ አሳዛኝ ውጤቶችን በማስከተል ላይ እንደሚገኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ እያንዳንዱ ጦርነት ሕዝቦች በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን ቤተሰባዊ ፍቅር ጣረት የሚያፈርስ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። ብዙን ጊዜ የጦርነት ዋና ምክንያት በሕዝቦች መካከል ያሉ ልዩነቶች አለመቀበል እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህም የበላይነትን፣ የጥላቻን፣ የስግብግብነትን እና የንቀትን መንፈስ በማሳደግ ወደ ሞት አደጋ ያደርሳል ብለዋል። ጦርነት የሚነሳው በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ ራስን ከሌሎች የበላይ ለማደርግ ሲሞከር፣ ስልጣንን በአግባቡ አለመጠቀም፣ ፍራቻን እና ልዩነቶችን በማሳደግ መሆኑን አስረድተዋል።

ወደ ሩቅ ምስራቅ እስያ አገር ወደ ሆነው ጃፓን ያደረጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለማችን ለሰላም እና ጸጥታ የሚደረጉ ጥረቶችን በማደናቀፍ፣ በሕዝቦች መካከል ፍርሃት እና ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ ለጋራ ውይይቶች እንቅፋት መሆኑን አስታውሰዋል። በፍርሃት እና በእርስ በእርስ ጥቃት ሰላምን እና ዓለም አቀፍ መረጋጋትን ማምጣት እንደማይቻል ያስረዱት ቅዱስነታቸው ሰላምን እና መረጋጋትን ማምጣት የሚቻለው ትክክለኛ መንገድን በተከተለ ዓለም አቀፍ ትብብር፣ ለዛሬው እና ለነገው ማሕበረሰብ ሃላፊነት የሚሰማው አካል ሲኖር እንደሆነ አስረድተዋል።

የሰላምን ጥረት የሚያደናቅፍ ተግባር ሁሉ በሰዎች መካከል ጥርጣሬን በማስከተል ስጋትን ይፈጥራል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥርጣሬ እና ፍርሃት ማሕበራዊ ግንኙነትን አዳክሞ ወደ አመጽ በመምራት ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይኖር ያደርጋል ብለው፣ የኑክሌር መሣሪያ እጥረት እንኳ ቢሆን የፀጥታ ስጋትን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

ፍርሃት በነገሠበት ዓለም እና በሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ሊያስከትል በሚችሉ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ላይ መተማመን በሚታይበት ዓለም የተረጋጋ ሰላምን ማምጣት እንደማይቻል የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖን በማስከተል የሰዎችን ሕይወት እና ተፈጥሮን ከአደጋ ከመከላከል ይልቅ ለጉዳት የሚዳርግ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ ከሆነ የሰላም እና የአንድነት ጉዞን እንዴት መጓዝ እንችላለን? ፍርሃትን እንዴት ማስወገድ እንችላለን? በሰዎች መካከል ያለውን አለመተማመን እንዴት ማስወገድ እንችላለን በማለት ቅዱስነታቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።  በማከልም መሠረቱን በእግዚአብሔር ላይ ባደረገ እውነተኛ የወንድማማችነት ስሜት በመታገዝ መተማመንን ሊያመጣ የሚችል የጋራ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ በልባችን ውስጥ የሚገኘውን የሰላም ምኞት እና ፍላጎት በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል ብለዋል።

2.  ሰላም፣ የመደማመጥ፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት ጉዞ ነው፣

በጃፓን ውስጥ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1945 ዓ. ም. ከተፈጸሙት የአቶሚክ ጦር መሣሪያ ጥቃት የተረፉት የሂባኩሻ ማሕበረሰብ፣ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ለደረሰው አሰቃቂ አደጋ እና ላስከተለው ጥፋት የእስካሁን ጊዜ ምስክር መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። ምስክርነታቸውም የአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ልብ በመቀስቀስ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ዓይነት ጥፋት እና የበላይነት ለመቃወም ያስችላል ብለው ትዝታው የዛሬውንም ሆነ የነገውን ትውልድ፣ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ሳይዘነጋው፣ ፍትሃዊ የሆነ የወንድማማችነት ሕይወት ለመገንባት ብርታትን ይሰጣል ብለዋል።

እንደ ሂባኩሻ ማሕበረሰብ፣ በዓለማችን ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች በርካታ ሕዝቦች፣ ያለፉት የአስከፊ ዘመናት ገጽታዎች በትውልድ መካከል እንዲታወሱ በማድረግ፣ ስሕተቶች ሁለተኛ እንዳይደገሙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ሆነ ነገ የሚደረጉ ውሳኔዎች ሰላምን ለማስፈን ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረቶችን በማድረጋ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።  ያለፉት ጊዜያት ትዝታዎቻችን ተስፋን እንድናደርግ ይረዱናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ብዙን ጊዜ አመጽ እና ጦርነት ባንዣበበት ዓለም ውስጥ የሚታይ ትንሽ የሰላም እና የአንድነት ጥረት ወደ መልካም ውሳኔዎች ለማድረግ ይረዱናል ብለው፣ በእያንዳንዱ ግለሰብ እና ማሕበረሰብ ልብ ውስጥ ብርታትን በመጨመር፣ አዲስ የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

ሰላምን ለመገንባት በሚደርግ ጉዞ ላይ በርካታ እንቅፋቶች ሊኖሩ እንደሚችል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእነዚህም መካከል የሰዎችን ግንኙነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉት ልዩ ልዩ የማሕበረሰብ እና የአገር  ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ከሁሉ አስቀድሞ የሰዎች የግል ስነ ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ምን እንደሚመስል መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ሰላም የሚመጣው ከሰዎች ልባዊ ፍላጎት እና ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው ይህ ፍላጎት እና ፈቃደኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመታደስ ዕርቅን እና ማሕበራዊ አንድተን ለማምጣት ዝግጁ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ዓለም ባዶ ቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የተገለጸ ምስክርነትን ማየት ይሻል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላምን ማምጣት የሚፈልጉት በሙሉ የልዩነት አስተሳሰብን ከልባቸው አስወግደው የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ ዝግጁዎች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። በሰዎች መካከል መግባባት የሚታይበት የጋራ ውይይት ሳይደረግ ወደ እውነተኛ ሰላም መድረስ ያስቸግራል በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፣ ሰላም ቀጣይነት ባለው የጋራ ውይይት መመራት እንዳለበት ገልጸው፣ በተጨማሪም ለጋራ ጥቅም በመቆም በሕግ እና በእውነት በሚመሩት ሰዎች የታገዘ መሆን ይኖርበታል ብለው፣ የእርስ በእርስ መደማመጥ ካለ ወደ መግባባት መድረስ እንደሚቻል አስረድተው በቅራኔ ውስጥ የሚገኙትንም ወደ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ፍቅር ሊመራ ይችላል ብለዋል።

በሕግ በሚመራ መንግሥት ውስጥ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን እና ሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር፣ ሰላምን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለይም በሕዝቦች መካከል ለተገለሉት እና ለደሄዩት ዘላቂ እና እውነተኛ ፍትሕን ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል። ይህም ዘላቂ በሆነ ማሕበራዊ ጥረት ውስጥ የግለሰብን፣ የአገርን እና የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብን አስተዋጾ የሚያስፈልገው መሆኑን አስረድተዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “የሕዝቦችን እኩልነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ እና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት ማሕበራዊ ሕይወትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለው፣ የማሕበራዊ ኑሮ እውቀት ከማሳደግ መብት በተጨማሪ የሌሎች ሰዎች ሕይወት ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የራስ ጥረት ምን መሆን እንደሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።  በሕዝቦች መካከል የሚፈጠር ክፍፍል፣ የኑሮ ልዩነቶች እና የሁለገብ ማሕበራዊ እድገት ችላ ማለት የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ነገር ግን እውነትን መሠረቷ ያደረች ትዕግስት ርህራሄን እና አንድነትን ልታስገኝ እንደምትችን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

የክርስትና ሕይወታችን የሚያስተምረን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠው በሰዎች መካከል እርቅን ለማምጣት መሆኑን ሳናቋርጥ ማስታወስ ይኖርብናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያንም በኅብረተሰብ መካከል ፍትህ እንዲኖር በማድረግ፣ ማኅበራዊ ጥቅምን በማስከበር እና ለሰላም ያላትን ተስፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ፣ ክርስቲያናዊ እሴቶችን እና ሞራላዊ አስተምህሮችን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ማሕበራዊ አገልግሎቶቿን ታከናውናለች ብለዋል።        

3.  ሰላም፣ የእርቅ እና የወንድማማችነት ጉዞ ነው፣

መጽሐፍ ቅዱሳችን፣ በነቢያት ትንቢት በኩል ራሳችንን ከሌሎች አብልጠን እንድንመለከት የሚያደርገንን ስሜት አስወግደን፣ ሰዎችን በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ልጆች በመመልከት፣ እርስ በእርሳችን እንደ ወንድም እና እንደ እህት መተያየት ያስፈልጋል በማለት መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎችን በንግግራቸው እና በሥራቸው ከመፈረጅ ይልቅ ነገር ግን ተሸክመው ለሚጓዙት የእግዚአብሔር አምሳያነት ዋጋን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። የበቀል ስሜትን አስወግደን የመከባበር መንገድን መያዝ የምንችለው በተስፋ ጎዳና ላይ መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ብለዋል።

በቅዱስ ወንጌል ቃል እንመራለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በማቴ. 18፡ 21-22 ላይ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ብሎ የመለሰውን አስታውሰው፣ ይህ የእርቅ መንገድ ልባችን ለወንድሞቻችንን እና ለእህቶቻችን ምሕረትን የማድረግ አቅም እንዳለው ያስረዳል ብለው ምሕረትን ማድረግ ስንማር የሰላም መሣሪያዎች ሆነን ማደግ እንችላለን ብለዋል።

በሥነ ማሕበራዊ አስተሳሰብ ለሰላም የሚሰጥ ትርጉም በፖለቲካው እና በኤኮኖሚው ዘርፍም ተመሳሳይ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሰላም በማኅበራዊ ዘርፎች በሙሉ እኩል የጋራ አቅጣጫ እንዳለው አስረድተዋል። ፍትሃዊ የሆነ ኤኮኖሚያዊ ሥርዓት ማሳደግ የሚቻለው በእውነተኛ የሰላም መንገድ ስንጓዝ ነው ብለዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዲክቶስ 16ኛ፣ ከአሥር ዓመት በፊት ይፋ ባደረጉት “በእውነተኛ ቸርነት” በተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ በቁጥር 39 ላይ ድህነትን ማስወገድ የሚቻለው ማሕበራዊ አገልግሎቶችን በማሳደግ፣ የህዝብን ደህንነት ለማሻሻል በሚደረግ የግብይት ልውውጦች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በዓለማችን ውስጥ ቀስ በቀስ ወቅቱን ጠብቀው በሚመጡ ሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

4.  ሰላም፣ የሥነ ምሕዳር ለውጥን ለማድረግ የሚደረግ ጉዞ ነው፣

በተፈጥሮ ላይ ጥፋት የሚደርሰው የተፈጥሮ ደንቦችን በትክክል ካለማወቅ የተነሳ፣ ተፈጥሮን በአግባቡ ካለበጠቀም፣ በጦርነት በመጠመድ፣ ኢፍትሃዊ መንገዶችን በመከተል፣ በአመጽ ተግባር ውስጥ በመግባት መሆኑን በመገንዘብ፣ ተፈጥሮን እንድንጠብቅ እና ከጉዳት እንድንከላከል ለተሰጠን አደራ ታማኞች ሆነን ባለመገኘታችን መሆኑን ርዕሠ  ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

በሌሎች ላይ ለተፈጸመው የጭካኔ ተግባር ዋጋን እየከፈልን እንገኛለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለጋራ መኖሪያ ለሆነው ምድራችን ክብርን ካለመስጠት ወይም የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ካለመጠቀም የተነሳ የደረሰብንን ችግር ለማወገድ ሥነ ምሕዳራዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በቅርቡ የተካሄደው የላቲን አሜርካ አማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች አሁን ከሚኖሩበትን ዘመን ጋር ራሳቸውን በማስታረቅ፣ ከአካባቢያቸው ጋር ጤናማ ግንኙነት በማበጀት፣ ያለፈውን ስህተት ወደ ፊት ከሚመጣው ተስፋ ጋር ማስታረቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል። በሥነ ምሕዳር ላይ የሚደረግ ለውጥ ጠቅላላ የተፈጥሮ ሕግጋትን ያገናዘበ መሆን አለበት ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዎች እና በሌሎች ፍጥረታት መካከል ያለው ግንኙነት የሕይወት ሁሉ ምንጭ ከሆነው ፈጣሪ ጋር ግንኙነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

5.  ተስፋ የምናደርግበትን ሁሉ ማግኘት እንችላለን፣

የእርቅ ጉዞ ትዕግስትን እና እርስ በእርስ መተማመንን ይጠይቃል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰላምን ለማግኘት ተስፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ከሁሉም በላይ ሰላም ማምጣት የሚቻል መሆኑን እና ሰላም ለግል ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እንደሚያስፈልግ ማመን ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ የእግዚአብሔር ፍቅር ለሁሉም እንደሆነ ገልጸው፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የማይደክም እና የማይሰለች፣ ነጻ የሚያወጣ የቸርነት ስጦታ መሆኑን አስረድተዋል።

ፍርሃት የአመጽ ውጤት መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍራሃትን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በእግዚአብሔር ጥበቃ ሥር የምንገኝ መሆናችንን በማወቅ፣ በሉቃ. 15፡ 11-24 እንደተገለጸው ምንም ብናጠፋ እና ብንሳሳትም ምሕረትን የሚያደርግልን ርህሩህ አባት እንዳለን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። የወንድማማችነትን ባሕል ማሳደግ አመጽን ያስወግዳል ያሉት ቅዱስነታቸው የወንድማማችነትን ባሕል ማሳደግ የእግዚአብሔርን የፍቅር ቸርነት እንድንረዳ ያግዛል ብለው፣ ከጠባብ አስተሳሰብ ተላቅቀን በወንድማማችነት መንፈስ በማሰባብሰብ የዘለዓለማዊ አባት ልጆች ያደርገናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚከተሉት ሁሉ የወንድማማችነት ጉዞ በምሕረት ጸጋ የሚታገዝ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ቤተክርስቲያን በቅዱሳት ምስጢራት የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሕይወት የሚታደስ መሆኑን አስረድተው፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም በምድር እና በሰማይ ሰላም እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

ከእግዚአብሔር በምናገኘው የፍቅር ጸጋ ምሕረትን ተቀብለናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሰላምን ማካፈል እንችላለን ብለው፣ መንፈስ ቅዱስ በዕለታዊ ሃሳባችን እና ንግግራችን የፍትህ እና የሰላም መሣሪያዎች እንድንሆን ያደርገናል ብለው፣ የእግዚአብሔር ሰላም ረዳታችን እንዲሆን፣ የሰላም ንጉሥ እናት፣ የዓለም ሕዝቦች እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የእርቅ መንገድን ለመጓዝ ትርዳን ብለው፣ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ የሰላም ሕይወት በመኖር በልባቸው ፍቅርን እንዲያሳድጉ በመመኘት የጎርጎሮሳውያኑን 2020 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕታቸውን አጠቃልለዋል።         

03 January 2020, 10:27