ፈልግ

የብርሃነ ልደቱን በዓል መልካም ምኞት በገለጹበት ወቅት፣ የብርሃነ ልደቱን በዓል መልካም ምኞት በገለጹበት ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጹ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በመቀጠል በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰው፣ ዛሬ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ክብረ በዓል ለማክበር የተዘጋጁ የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠርን ለሚከተሉ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፣ የመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ብርሃንን እና ሰላምን እንዲያበዛላቸው ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ዛሬ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሕጻናት የወንጌል ተልዕኮ ቀንን ባስታወሱት ንግግራቸው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች፣ በችግር ውስጥ ለወደቁት እኩዮቻቸው በሚያበረክቱት የቸርነት እና የጸሎት ድጋፍ አማካይነት የተጠሩበትን የቅድስና ሕይወት በተግባር ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ከሮም እና አካባቢዋ፣ ከሌሎች የጣሊያን ሀገረ ስብከቶች፣ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ከእነዚህም መካከል ከደቡብ ኮርያ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ በኒው ዮርክ ከተማ የሴና ቅዱስ ፍራንችስኮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች እና በጣሊያን ውስጥ ከፈራራ ከተማ ለመጡት የወንጌል ልኡካን ማሕበር አባላት ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት በሕዝቡ ባሕል ውስጥ በየጊዜው የሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት ክርስቲያናዊ ይዘታቸውን እና ትርጉማቸውን ጠብቀው መከበራቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣በፖላንድ፣ በስፔን፣ በደቡብ አሜሪካ እና በጀርመን ውስጥ በሚገኙ በርካታ ከተሞች እና መንደሮች፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት ሥነ ሥርዓትን በድምቀት ላከበሩት ምዕመናን በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው በመመኘት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ካሉ በኋላ መልካም ዕለተ ሰንበትን በመመኘት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

06 January 2020, 16:45