ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አምባሳደሮችን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አምባሳደሮችን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣  

ዲፕሎማቶች፣ “የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ተግባር ለበርካታ ሕዝቦች ተስፋን የሚሰጥ ነው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ታኅሳስ 30/2012 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተወካይ የሆኑት፣ የቆጵሮስ አምባሳደር ክቡር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ ዲፕሎማቶችን በመወከል ለር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት የምስጋና ንግግር፣ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚያበረክቱት በርካታ ሐዋርያዊ ተግባራት፣ ከእነዚህም መካከል ለጋራ ውይይት፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሥነ ምሕዳር መጠበቅ እና ለሰብዓዊ ወንድማማችነት ጥረት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአንድ ዓመት በፊት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ ብዝሃንነት ባላቸው የዲፕሎማሲ እሴቶች መተማመን አስፈላጊ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል። በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተወካይ የሆኑት፣ የቆጵሮስ አምባሳደር ክቡር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ በንግግራቸው በዘመናችን የሚንጸባረቁ የብሔርተኝነት ስሜት፣ የግጭት እና የጦረነት መግለጫዎች እና አዋጆች ስለ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” እንድናወራ አድርገውናል ብለዋል። ባለፉት ዘመናት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የጋራ ወይይቶች ማጣት የተነሳ በዓለማችን ውስጥ ጦርነቶች መቀስቀሳቸውን አስታውሰው፣ ዛሬ ግን ያለፉ ስሕተቶች እንዳይደገሙ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ዓመት ጥረቶች፣

ባለው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ያስታወሱት የቆጵሮስ ክቡር አምባሳደር  አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ ቅዱስነታቸው በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ከግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር ያደረጉትን  የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ጠቅሰው፣ ወደ ሞሮኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውም፣ አንድነት እና የጋራ ውይይት ባሕል የሚታይበትን ማሕበረሰብ   መገንባት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ክቡር አምባሳደር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ በማከልም ቅዱስነታቸው በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አንድት በማሳደግ ወንድማማችነት እና ፍቅርን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በሮማኒያ፣ በቡልጋሪያ እና በሰሜን መቄዶኒያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

በእስያ እና በአፍሪካ አህጉራት ቅዱስነታቸው ያሰሙት የአንድነት እና የሰላም ጥሪዎች፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ እስያ አህጉር ያደረጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታ ያስታወሱት ክቡር አምባሳደር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት ዓለም አቀፍ ሥነ ምግባር የታከለበት የአንድነት እና የመተጋገዝ ባሕል ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል። በታይላንድ ባደረጉት ጉብኝታቸው፣ ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አስታውሰው፣ በጃፓን ጉብኝታቸው ኒዩክሌር የጦር መሣሪያ አስከፊነት እና ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት በመግለጽ አጥብቀው መቃወማቸውን አስታውሰ፣ ፍርሃትን በማስወገድ በጋራ ሰላምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አፍሪካ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ክቡር አምባሳደር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ ቅዱስነታቸው በሚያደርጉት ጥረት አማካይነት የሰላም እና የእርቅ ምልክቶች መታየታቸውን ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው በሞዛምቦክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ ተኝተው፣ የእነዚህ አገሮች ሕዝቦች ለሰላም እና ለወዳጅነት ያላቸው ቅን ፍላጎት ማሳደግ እንዳለባቸው ያበረታቱ መሆኑን አስታውሰዋል።

በትውልድ መካከል የጋራ ውይይት እና ትምህርት እንዲዳብር ማድረግ፣

በትውልድ መካከል የጋራ ውይይትን እና ትምህርትን ማዳበር አስፈላጊነት አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ማሳሰባቸውን ያስታወሱት ክቡር አምባሳደር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ፣ በግንቦት 6/2012 ሊደረግ የታቀደውን እና ከወጣቶች ለወጣቶች የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የመማማር እና የጋራ ውይይት ጉባኤ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ለሰው ልጅ የሚሰጥ ፍቅር ማሳደግ፣

በቅድስት መንበር የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተወካይ የሆኑት፣ የቆጵሮስ አምባሳደር ክቡር አቶ ጆርጆ ፑሊደስ በንግግራቸው መጨረሻ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጥረቶች በሙሉ፣ በዲፕሎማቶቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ዲፕሎማቶቹ በሙሉ የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጥረት ለበርካታ ሕዝቦች ተስፋን የሚሰጥ በመሆኑ፣  ይህ ጥረታቸው ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ተልቅ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን በፍቅር የሚያዩት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 January 2020, 16:04