ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ለአህዛብ ሁሉ መመስከር ያስፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበበው በቅዱስ ማቴ. 4:12-23 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት ስብከታቸው “የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት ፈለግ በመከተል የእግዚብሔርን ፍቅር ለአህዛብ ሁሉ መመስከር ያስፈልጋል” ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ከዚህ በታች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከማቴ. 4፡12-23 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ንባብ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎት ተልዕኮ መጀመሪያን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን የጀመረበት የገሊላ ክፍለ ሀገር እንደ ኢየሩሳሌም ሳይሆን አይሁዳዊያን እና አረማዊያን በአንድነት የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደገበት የናዝሬት ከተማ የሚገኝበት ክፍለ ሀገር ነው። በዚህ አካባቢ ነው እንግዲህ ኢየሱስም የማስተማር አገልግሎቱን የጀመረው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ የትምህርቱ ቀዳሚ ዓላማ፣ በማቴ. 4፡17 ላይ እንደሚናገረን፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች እና ንሥሐ ግቡ በማለት ማሳሰብ ነበር። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቢያ ጨለማን እንደሚያበራ፣ በብርሃነ ልደቱ ምሽት የሚነበበውን የነብዩ ኢሳያስ ትንቢት የሚያስታስ ነው። በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤  በሞት ጥላ ምድር ለኖሩትም  ብርሃን ወጣላቸው (ኢሳ. 9:1)። ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ ወደ ዓለም መምጣቱ፣ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለውን ቅርበት እና ወዳጅነትን የገለጸበት ነው። የእግዚአብሔርን ነጻ ስጦታዎች ለመቀበል በእውነት የተገባን ሆነን ሳይሆን እጅግ አድርጎ ስለሚወደን በመሆኑ ስጦታዎቹን መጠበቅ እና መንከባከብ ይኖርብናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለገሊላ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች ያቀረበው የመለወጥ ጥሪ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የቀረበ ጥሪ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደ ዓለም መምጣቱን፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ላስታወስን ሰዎች ሁሉ የቀረበ ጥሪ ነው። ከተሳሳተ የሕይወት አካሄድ፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከክፋት፣  ከኃጢአት ሕይወት ወጥቶ ለውጥን ማሳየት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በሕይወታችን ሥር ነቀል ለውጥን ለማምጣት፣ በራሳችን ኃይል ብቻ ምንም ማድረግ እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል። በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በማሳነስ በግል ችሎታ ብቻ መተማመን የለብንም። በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በማሳነስ፣ በራሳችን አቅም ብቻ መተማመን በራሱ ኃጢአት እንደሆነ አምናለሁ። እምነትን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ መልካም ነው። ዓለምን እና የሰዎችን ልብ የሚቀይር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና ቅዱስ ወንጌልን ልባችንን ከፍተን መቀበል ያስፈልጋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመታመን፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመቀበል እና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለውጥን ለማግኘት ተጠርተናል።

ለውጥን ለማምጣት የምናደርገው እውነተኛ ጉዞ የሚጀምረው ከዚህ ነው። የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርትን እንዳጋጠማቸው ሁሉ፣ ከመለኮታዊ መምህር ጋር ያደረጉት ግንኙነ፣ ከቃሉ የቀሰሙት እውቀት እርሱን እንዲከተሉት እና ሕይወታቸውን ቀይሮት ለእግዚአብሔር መንግሥት አገልግሎት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ወይም እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል።

ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደረጉት አስደናቂ እና ቆራጥ ግንኙነት ሕይወታቸውን እና ማንነታቸውን ሙሉ በሙሉ ቀይሮት፣ ከኢየሱስ የተማሩትን ትምህርቶች ለሌሎች እንዲያካፍሉ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች እንዲሆኑ እና የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሕዝቡ ሁሉ መመስከር እንዲችሉ የመጀመሪያ ድጋፍ ሆኖላቸዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት ፈለግ በመከተል፣ ዘለዓለማዊ ቃሉን ለመስማት እጅግ ለተጠሙት መልካም ዜናን ማብሰር እንድንችል እያንዳንዳችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ የምንጓዝ መሆን አለብን።  

በዛሬው ዕለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረብነው ጸሎት አማካይነት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነን የእርሱን መልካም ዜና የምናበስርበትን ኃይል እና ጸጋ እንድታስገኝልን፣ የእርሷን እናታዊ አማላጅነት በጸሎት እንጠይቃለን”።         

27 January 2020, 14:45