ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቅዱስ ወንጌል፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀልን ዕቅድ የተገለጠበት” ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ክብረ በዓል ሁለተኛ እሁድ በማስመልከት፣ ትናንት እሑድ ታኅሳስ 26/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ስብከታቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት “የቅዱስ ወንጌል ታሪክ ተረት ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀልን ዕቅድ የተገለጠበት” ነው በማለት አስረድተዋል። ክቡራት እና የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ከዚህ በታች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው አርቅርበንላችኋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በተከበረ በሁለተኛ እሑድ የቀረቡት የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት፣ አመለካከታችንን ሰፋ በማድረግ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ትርጉም በሚገባ እንድንገነዘብ ያግዙናል። ቅዱስ ዮሐንስ የጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በምዕ. 1:14 ላይ በአስደናቂ ሁኔታ፣ ዘለዓለማዊው ቃል ሥጋን በመልበስ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጡን ያሳየናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሕዝቦች መካከል መኖር ብቻ ሳይሆን ከእኛ መካከል አንዱ ሆኗል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ሕይወታችን የሚመራው በሕግ ብቻ ሳይሆን መለኮታዊ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሕይወታችን መከተል ያለበትን አቅጣጫ በማመልከት፣ እርሱ አስቀድሞ ባዘጋጀልን መንገድ እንድንራመድ ኢየሱስ አግዞናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክቱ፣ በምዕ. 1:3-6 እና 15-18 ላይ “በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፣ በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን”፤ በማለት እግዚአብሔርን ያመሰግናል። በዚህ የእግዚአብሔር ዕቅድ ውይም ዓላማ በመታገዝ እያንዳንዳችን የተጠራንበት መንገድ የቱ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስም፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን የለበሰው እኛም የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ለማድረግ ነው። በዚህም ዘለዓለማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ ከእግዚአብሔር ጋር አስተዋወቀን።

ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃነ ልደት ስናስታውስ፣ በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ታሪክ የአሉ ባልታ ወሬ ወይም ተረት ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለዓለም ሕዝቦች ያዘጋጀው ዕቅድ በሙላት የተገለጠበት ነው። ነገር ግን ይህ የእግዚአብሔር ዕቅድ በእያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ አንድ ጥያቄን እንድናነሳ ይገፋፋናል። ጥያቄውም “እግዚአብሔር አብ የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በየዓመቱ እንድናስታውስ ሲያደርገን፣ ለእኛ ምን ዕቅድ ወይም ዓላማ ቢኖረው ነው”? የሚል ነው። 

ለዚህ ጥያቄ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክቱ፣ በምዕ. 1:4 ላይ ቅዱሳን እና በፊቱ ነቀፋ የሌለብን ሆነን በፊቱ እንድንገኝ፣ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ መረጠን በማለት ይመልሳ። የመድኃኒታችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ትርግምም ይህ ነው። እግዚአብሔር በየጊዜው በእኛ መካከል መገኘትን ከቀጠለ፣ በቃሉም የሚመግበን ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር በመታገዝ እና በመመራት ለቅድስና የማንበቃበት ምክንያት አይኖርም። ቅድስና የእግዚአብሔር መሆናችንን የምናረጋግጥበት፣ ከእርሱ ጋር ያለንን አንድነት የምናጸናበት እና የእርሱ ዘለዓለማዊ ፈቃድ በግልጽ የሚገለጥበት መንገድ ነው። ቅድስና እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን ስጦታ ስለ ሆነ አጥብቀን ልንይዘው ይገባል። ቅድስና ማለትም ይህ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን ቅድስና በልቡ የሚይዝ በሙሉ በዕለታዊ ሕይወቱ መካከል በተግባር ላይ ሊያውል ይችላል። ይህ ከእግዚአብሔር የተቀበልኩት የቅድስና ስጦታ ወይም ጸጋ እውን እንዲሆን የማደረገው፣ በእለታዊ ሕይወት ወስጥ በተግባር በመግለጽ፣ ከሌሎች ወንድሞቼ እና እህቶቼ ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት መሆን አለበት። ለሌሎች የማበረክተው የቸርነት እና የምሕረት ተግባር፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በገሃድ የሚገለጥበት መንገድ ነው። በዚህ ሁኔታ የበደሉንን ይቅር በማለት፣ በየቀኑ ልባችንን ንጹሕ እንድናደርግ ያግዘናል። ንጹሕ ስንል ከእድፍ ነጻ መሆን ማለት ሳይሆን የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ተቀብለን በልባችን ውስጥ በመያዝ ለሌሎች ማካፈል ማለት ነው።

እግዚአብሔር አብ፣ ልጁን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም በመላክ የገለጠልንን ዘለዓለማዊ ፍቅር በደስታ ተቀብለን እንድናመሰግነው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 January 2020, 16:31