ፈልግ

“ሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የተከተለ የፍቅር እና የአገልግሎት ሕይወት ይሁን”።

 የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በኅዳር 28/2012 ዓ.ም. የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በሙሉ በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖን በማድረግ ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ወቅት በሕይወታች ሁሉ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው መልስ የይሁንታ ሊሆን ይገባል ብለው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የተከተለ የፍቅር እና የአገልግሎት ሕይወት ይኑረን ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራት አድማጮቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ትርጉም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ እግዚአብሔር አምላካችን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም ለመላክ የገባልን ቃል እስኪፈጸም በምንጠባበቅበት በስብከተ ገና ሰሞን የሚውለውን የጽንሰታ ማርያም ክብረ በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። ይህን በዓል በምናከብርበት እለት በእመቤታችን ማርያም ላይ አስቀድሞ አንድ ነገር መከናወኑ ተነግሮናል። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የታየው አስደናቂ ነገር ጌታችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ከመውለዷ በፊት ነው። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መጸነስ ወይም ጽንሰታ ማርያም በማለት የምናከብረው በዓል የሚያስታውሰን፣ ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማሕጸን ውስጥ ከመጸነሷ አስቀድሞ፣ እርሷ የተጸነሰችበት ማሕጸን ከሰው ልጅ ኃጢአት ነጻ በሆነ እና በእግዚአብሔር ፍቅር በተሞላ ቅዱስ ሥፍራ መሆኑን ያስታውሰናል።

ዛሬ የሰማነው የቅዱስ ወንጌል ንባብ፣ በሉቃ. 1፡28 የእግዚአብሔር መልአክ፣ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ማርያም ባቀረበላት ሰላምታው “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” ማለቱን ያስታውሰናል። እግዚአብሔር ማርያምን በጸጋ የተሞላች፣ ታላቅ ሥራው በእርሷ በኩል እንዲገለጥ የመረጣት እና ያዘጋጃት መሆኑን ዘወትር በፍቅሩ በመሙላት ገልጾላታል። በእግዚብሔር ፍቅር ለመሞላት፣ እመቤታችን ቅድስት ማርያም እንዳደረገችው ሁሉ የእግዚአብሔር ጸጋ የሚያርፍበት ነጻ የሆነ ሥፍራ ሊኖር ይገባል። ማርያም የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ፣ ሙሉ በሙሉ ራሷን ለእርሱ በማስገዛት፣ በእርሷ ላይ የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም በማለት ራሷ አዘጋጅታለች። በዚህም የእግዚአብሔር ቃል በእርሷ ውስጥ በመግባት ስጋን ለበሰ። ይህ ሊሆን የቻለው የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብላ በውስጧ ለማኖር ፈቃደኛ በመሆኗ ምክንያት ነው። መልአኩ ገብርኤልም ማርያም የኢየሱስ እናት ለመሆን ያላትን ፈቃደኛነት ለማረጋገጥ ፈልጎ በጠየቃት ጊዜ በሉቃ. 1.38 ላይ እንደተገለጸው “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለችው።

ማርያም ይህን መልስ በመልአኩ ገብርኤል በኩል ለእግዚአብሔር በሰጠች ጊዜ ያለ ምንም ማንገራገር፣ ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥማትም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ የምታሸንፈው መሆኑን በማመን ነበር። በመሆኑም በሁለመናዋ እና በማንነቷ ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲገለጥ አደረገች። በዚህም ምክንያት ማርያም የእግዚአብሔር እቅድ በተግባር የሚፈጸምባት ያማረች እና የተቀደሰች ሥፍራ ሆና ተገኘች። እመቤታችን ማርያም ይህን ስታደርግ ፍጹም ትሑት፣ ከሁሉ ዝቅተኛ እና ደሃ ሆና ቀረበች። ይህም በመሆኗ የእግዚአብሔር ውበት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር ጸጋ የሚገለጥባት ሆና ተገኘች።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ስታቀርብ የተናገረችውን ቃል ማስታወስ እፈልጋለሁ። “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ” በማለት መለሰችለት። ማርያም ይህን ስትናገር ከመጀመሪያ አንስቶ ራሷን ለአገልግሎት ማዘጋጀቷን፣ የእርሷ ድጋፍ እና የእርሷ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ ለማገልገል መዘጋጀቷን በልበ ሙሉነት አስታውቃለች። ይህን ዝግጁነቷን ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ብስራት ወይም ሰላምታ በኋላ ሳትዘገይ ቶሎ ብላ ኤልሳቤጥን በመጎበኘቷ በተግባር አስመስክራለች። ለእግዚአብሔር ጥሪ የምንሰጠው በጎ ምላሽ የሚታወቀው ሌሎችን ለማገልገል ያለንን ዝግጁነት ስንገልጽ ነው። አገልግሎታችንን የምናበረክተው ከፍተኛ የሆነ የክብር ቦታን በመፈለግ፣ ስልጣንን በመፈለግ፣ ራስን በአደባባይ በማስተዋወቅ አይደለም። የቸርነት አገልግሎታችን እና የምሕረት ተግባራችን ለሌሎች እንዲታይ ብለን ወደ አደባባይ መውጣት አያስፈልገውም። የምሕረት ተገባራችን በጸጥታ እና በስውር መከናወን አለበት። በምንኖርበት ማሕበረሰባችን ውስጥም የምናከናውነው በጎ ተግባር የእመቤታችን ማርያምን ምሳሌ የተከተለ መሆን አለበት።

ዛሬ ያከበርነው የጽንስታ ማርያም ክብረ በዓል፣ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ የምናስገዛበት፣ ለእርሱ ክብርን እና ውዳሴን በማቅረብ ለጥያቄው መልካም ምላሽ የምንሰጥበት እና ዘወትር በፍቅር እርሱን እንድናገለግል ያግዘን”።    

09 December 2019, 17:11