ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከፖላንድ የሠራተኛ ማህበራት ሕብረት ተወካዮች ጋር፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከፖላንድ የሠራተኛ ማህበራት ሕብረት ተወካዮች ጋር፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ማኅበራዊ ደህንነትና ፍትህ ለማምጣት የእግዚአብሔርን እገዛ መለመን ያስፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ህዳር 24/2012 ዓ. ም. ለፖላንድ ልኡካን ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት ለማህበራዊ ጥቅም እና ፍትህ በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ የእግዚአብሔርን መሪነት መለመን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ዘወትር ረቡዕ ዕለት የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከመጀመራቸው በፊት ባደረጉት ንግግር በማሕበራዊ ተቋማት መካከል መልካም ለውጦችን ለማምጣት ከተፈለገ በቅድሚያ የሰዎችን አስተሳሰብ ወደ መልካም መንገድ መምራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለዚህም ወጣቱን ትውልድ በስነ ምግባር ማነጽ እና ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዚህ መልኩ ቅድመ ዝግጅት ካልተደረገ ሕዝብን ለማገልገል የሚመሠረቱ ማህበራዊ ተቋማት የተወሰኑ ክፍሎችን ወይም ግለሰቦችን ብቻ ከማገልገልም በላይ ሙስናን በማስፋፋት ውጤት አልባ ሆነው የሚቀሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ርቡዕ ህዳር 24/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከመጀመራቸው በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1980 ዎቹ መገባደጃ ላይ በፖላንድ የኮሚኒስት ሥርዓት መውደቅ ውሳኝ ሚናን ለተጫወተው የሕዝባዊ አንድነት መምሪያ ምክር ቤት ንግግር ማሰማታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሚኬሌ ራቪያርት የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

ከፖላንድ አገር ውጭ ምን እየሆነ ነበር፣

በወቅቱ የፖላንድ ሕዝባዊ አንድነት መምሪያ ምክር ቤት ተጠሪ የነበሩት ሌክ ዋሌሳ ከአገራቸው ፖላንድ አልፎ ከሌሎች አገሮች ጋርም መልካም ሃሳባቸውን ይጋሩ እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በፖላንድ ውስጥ ለማህበራዊ ጥቅም እና ፍትህ የበኩላቸውን አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ የሚገኙትን የሠራተኛ ማህበራት ተወካዮችን አመስግነዋቸውል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው እንደገለጹት ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የፖላንድ ከተማ በሆነች ቫርሳቪያ ለሚገኙ የሕዝባዊ ማህበራት ተወካዮች መልዕክት ይልኩ እንደነበር አስታውሰው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በመልዕክታቸው የእግዚአብሔርን እገዛ እና የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ ይመኙ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለተገኙት የፖላንድ ሠራተኛ ማህበራት ልኡካን ባሰሙት ንግግር ለማህበራዊ ጥቅም እና ፍትህ በሚቀርቡ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ የእግዚአብሔርን መሪነት መለመን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።         

መብታቸውን የተነፈጉትን መርዳት ያስፈልጋል፣

መብታቸውን ከተነፈጉት ጋር መቆም የመንፈስ ቅዱስ እገዛ እና የእግዚአብሔርን መሪነት ለማግኘት ራስን ክፍት የማድረግ ምልክት ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማሕበራዊ ሕይወት፣ በሥራ መስክ፣ በሳይንሳዊ ምርምር፣ ማሕበራዊ ዘርፍ በሆኑት ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችም መብታቸውን ከተነፈጉት ጋር በመቆም እገዛን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ለሕዝቦች እነዚህን አሟልቶ መገኘት መብታቸውን የተነፈጉት ወንድሞቻችን እና ህቶቻችን ራሳቸውን የሚችሉበትን፣ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ተሻለ ሕይወት ማብቃት የሚችሉበትን፣ ሥራን እና በቂ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል ለማመቻቸት ያግዛል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

05 December 2019, 16:54