ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአካል ጉዳተኞች ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአካል ጉዳተኞች ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለማችን የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ ክብር የሚያረጋግጥ ይሁን ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ህዳር 23/2012 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልክት መልዕክት አስተላልፈውል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በማቴ. 25:40 ላይ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁ ነው” ያለውን በመጥቀስ እንደተናገሩት የአካል ጉዳተኛ በሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በኩል የሚገለጠውን ኢየሱስ ተመልክተን፣ እምነታችንንም በማደስ በመካከላችን አነስተኛ ለሆኑት ፍቅራችንን መግለጥ ይኖርብናል ብለዋል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የአካል ጉዳተኞችን ማሕበራዊ ተሳትፎ መብት ማክበር አድልዎን ለመዋጋት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት ባህልን ለማሳደግ እና ጥራት ያለውን ኑሮ ለማመቻቸት ማዕከላዊ ሚና እንዳለው ማስታወስ እፈልጋለሁ ብለዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት እና ድጋፍ ከፍተኛ እድገትን እንዳሳየ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ሆኖን በዓለማችን በርካታ የአካል ጉዳተኞች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ እና ከማሕበረሰቡ መካከል እንዲገለሉ በሚያደርግ ባሕል የተጠቁ መሆናቸውን አስታውሰው በምንም ዓይነት ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አለመሳተፋቸው ለብቸኝነት ዳርጓቸዋል ብለዋል። እነዚህን ማሕበራዊ ችግር ለማስወገድ የአካል ጉዳተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ብቻ ሳይሆን የአካል ጉዳተኞችን በሰብዓዊ ሕሊና በመመልከት፣ በማሕበረሰብ መካከል ሙሉ ዜጋ እንዳይሆኑ የሚያግዱ እንቅፋቶችን በማስወገድ፣ ጥራት ያለውን ኑሮ እና መዋያ ሥፍራዎችን ማመቻቸት እና የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ደረጃ በሙሉ ከግምት ውስጥ ማስገባትን ይጠይቃል ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞች ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከመጠቀም አንስቶ ሊያገኟቸው እና ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ ቁሳቁሶችን በማቅረብ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን አስጠብቀው በማሕበራዊ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ይህን ማሟላት ለአንድ ማሕበረሰብ ከባድ ሆኑ ቢታይም ውጤቱን ስናየው ከምንም ሊስተካከል የማይችል የአንድ ሰው ሕይወት ክቡርነት ለመገንዘብ እና ለመረዳት ያግዛል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 29/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር እና እንደዚሁም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 12/2015 ዓ. ም. የውጭ አገር ዲፕሎማቶችን በቫቲካን ተቀብለው ባሰሙት ንግግር፣ “በየቤቶቻችን፣ በየዘመዶቻችን፣ በየማህበረሰቦቻችን ውስጥ ተደብቀው የሚገኙትን የአካል ጉዳተኛ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርሳት የለብንም” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል። በዕድሜ ከፍ ያሉትን የአካል ጉዳተኞች ያስታውሱት ቅዱስነታቸው እነዚህ የአካል ጉዳተኞች ራሳቸውን የማሕበረሰብ ሸክም አድርገው እንደሚቆጥሩ፣ ከዕለታት አንድ ቀን ሊዘነጉ እንደሚችሉ እና በማህበራዊ ዕድገትም ምንም አስተዋጽዖን የማያበረክቱ አድርገው ራሳቸውን የሚቆጥሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀላልም ሆነ በከባድ የአካል ጉዳተኛ የሕይወት ታሪክ አማካይነት ማሕበራዊ አንድነትን እና ጥቅምን በሚገባ ለመረዳት ተጠርተናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ለመረዳት ታዲያ በአምስቱ ሕዋሳት መመካት አያስፈልግም በማለት እንደ ጎርጎሮስውያኑ አቆጣጠር በሰኔ 11/2016 ዓ. ም. የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ በተዘጋጀ ስብሰባ ለተካፈሉት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መናገራቸው ይታወሳል። የአካል ጉዳተኞችን ማንነት እንድናውቅ የሚረዳን ቅዱስ ወንጌል መሆኑን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዎች መካከል ልዩነትን ፈጥሮ ደረጃን የሚሰጥ ባሕል ማሳደግ ማሕበራዊ ኃጢአት እንደሚያስከትል ገልጸዋል። በአንዳንድ አገሮች ዘንድ የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብት እኩል እንዳልተከበረላቸው፣ ዛሬም ቢሆን ልዩነት እንደሚደረግባቸው የገልጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚህ የአካል ጉዳተኞች ወንድሞቻችን ኣና እህቶቻችን መሆናቸውን የሚመሰክር ድምጽ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞችን የሚደግፍ ሕጎችን ማጽደቅ መልካም ቢሆንም በቂ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሁኑ ጊዜ በሕብረተሰብ መካከል ተስፋፍቶ የሚገኘውን እና በሰዎች መካከል ልዩነትን እየፈጠረ የሚገኘውን ባሕል፣ የአካል ጉዳተኞች በማሕበራዊ እድገት እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ባሕልን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ ተሳትፎን የሚያጠናክሩ አንዳንድ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህም ቢሆን በቂ እንዳይደሉ ገልጸው የአካል ጉዳተኞች ካለባቸው ችግር በተጨማሪ የትምህርት እና የሥራ ዕድል የማይሰጣቸው መሆኑን ገልጸው አንድ የአካል ጉዳተኛ ስብዕናውን የሚያረጋግጠው በሕይወት በመኖሩ ብቻ ሳይሆን በማሕበረሰብ መካከል እኩል መብት ኖሮት አባልነቱን ሲያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ህዳር 23/2012 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልክት ያስተላለፉትን መልዕክት ከማጠቃለላቸው በፊት አንድን አገር እድገት በሚያረጋግጥ የአካል ጉዳተኞች አገልግሎት ላይ ለተሰማሩት በሙሉ ብርታትን ተመኝተው፣ እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔርን ታላቅነት ራሱን ተመልክቶ መረዳት እንዲችል፣ ሙሉ ክብሩን እና ሕይወቱ ዋጋ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዲችል እጸልያለሁ ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 December 2019, 16:49