ፈልግ

እውነተኛ ወንጌላዊ የሆነ ሰው በሁሉም ተግባሩ የሚመሰክረው ስለራሱ ሳይሆን ስለክርስቶስ ነው!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 01/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 01/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ ስምንት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 26፡28 ላይ በተጠቀሰው አግሪጳ የሚባል አንድ ሰው ጳውሎስን፣ “እንዲህ በቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን?” ብሎ ባነሳለት ጥያቄ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን  “እውነተኛ ወንጌላዊ የሆነ ሰው በሁሉም ተግባሩ የሚመሰክረው ስለራሱ ሳይሆን ስለክርስቶስ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል። 

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 01/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የቅዱስ ወንጌል ጉዞ በዓለም ውስጥ የሚያደርገውን ጉዞ የቀጠለ ሲሆን፣ በስቃይ ማኅተም የታተመው የቅዱስ ጳውሎስ ምስክርነት ሁልጊዜም እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳያል። ጳውሎስ በወኔ የተመላ የቅዱስ ወንጌል ሰባኪ ብቻ አልንበረም፣ ለአዳዲስ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ሕይወት የሚሰጥ ከሙታን የተነሳውን የክርስቶስ ስቃይ የመሰከረ ወንጌላዊ ነበር።

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 21 ውስጥ የተገለፀው ሐዋርያው ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ በእርሱ ላይ ከባድ የሆነ ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል። የኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች በኢየሱስ ላይ አድርገውት እንደ ነበረው ዓይነት እርሱንም እንዲሁ እንደ ጠላት አድረገው ነበር የቆጠሩት። ወደ ቤተመቅደስ ከሄደ በኋላ ሕዝቡ እርሱ መሆኑን አወቁ፣ ሕዝቡም ከቤተመቅደስ አውጥተው ሊገሉት ወሰዱት፣ ነገር ግን በስፍራው የነበሩ የሮማውያን ወታደሮች ታደጉት። በሕጋቸው እና በቤተ መቅደሱ ላይ የጥላች ንግግር አድርጓል የሚል ክስ ቀረበበት፣ በእዚህም ጉዳይ ተከሰሰ፣ ከዚያም የእርሱ የእስር ቤት የቆይታ ጊዜ ጀመረ፣ በቅድሚያ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቀረበ፣ ከእዚያም በቂሳሪያ በሚገኘው የሮማዊያን ገዢ ፊት ቀረበ፣ በመጨረሻ ደግሞ ጳውሎስ በንጉስ አግሪጳ ፊት ቀረበ። ወንጌላዊ ሉቃስ በጳውሎስ እና በኢየሱስ ላይ የተፈጸመውን ተመሳሳይ ተግባር በንጽጽር በማቅረብ፣ ሁለቱም በጠላቶቻቸው መጠላታቸውን፣ በሕዝቡ በይፋ መከሰሳቸውን እና በንጉሰ ነገስቱ እና በባለሥልጣናቱ ዘንድ ግን ምንም ጥፋት እንደ ሌለባቸው መገለጹን በማሳየት ጳውሎስ የጌታው ስቃይ ተካፋይ መሆኑን በመግለጽ በሁለቱ ላይ የተፈጸመውን ተግባር ያብራራል፣ የእርሱም ስቃይ ሕያው ወንጌል ይሆናል።

ጳውሎስ የተከሰሰባቸውን ክሶች እንዲከላከል ተጋበዘ ፣ በመጨረሻም ፣ በንጉሥ አግሪጳ ዳግማዊ ፊት ፣ ቀርቦ ውጤታማ የሆነ የእምነት ምስክርነት ካደረገ በኋላ ይቅርታ ተደረገለት (ሐዋ. 26፣1-23 ይመልከቱ)። ስለራሱ በሚናገርበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ጳውሎስ ጌታውን መመስከር እና ማስተዋወቅ አልታከተም ነበር።  እውነተኛ ሚስዮናዊ የሆነ ሰው እርሱ በራሱ ላይ እጅግ ያተኮረ ሰው አይሆንም፣  ነገር ግን ሁሉንም የሁሉም ነገር ማዕከል ወደሆነው ወደ ጌታው ይመራል። ጳውሎስ ለንጉሱ በተናገረው ንግግር፣ ከእስራኤል ጋር ያለውን የጠበቀ ቁርኝት አጠናክሮ እንደ ሚቀጥል ያሳያል። ከፈሪሳውያንም ጋር የትንሳኤን ተስፋ ይካፈላል፣ ክርስቲያኖች ጋር ደግሞ የሙታን ትንሳኤ በክርስቶስ አማካይነት መፈጸሙን ይናገራል።

ከዚያን በመቀጠል ጳውሎስ እርሱ መነፈሳዊ ለውጥ ያመጣበትን ሁኔታ ይናገራል፡ ክርስቶስ ራሱ ክርስቲያን እንዲሆን እንዳደርገው እና በአሕዛብ መካከል ልያደርግ የሚገባውን ተልእኮ በአደራ እንደሰጠው “ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ” (የሐዋ 26፡ 18) በማለት ክርስቶስ እንደ ነገረው ይገልጻል። ጳውሎስ ይህንን ኃላፊነት ተቀብሎ ለአግልግሎቱ ታዛዥ የነበረ ሲሆን ነብያት እና ሙሴ አስቀድመው የተነበዩትን በድጋሚ በማወጅ “ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብ » (የሐዋ 26፡23) ያውጃል።

የጳውሎስ በስሜት የተሞላ ምስክርነት የንጉሱን አግሪጳን ልብ ይነካል፣ “እንዲሁ ብቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን!” (የሐዋ 26፡28) በማለት የመጨረሻ ውሳኔ ብቻ የቀረው ንግግር እንዲናገር አድርጎታል። ጳውሎስ ነፃ መሆኑ ተነገረው፣ ነገር ግን ለቄሳር ይግባኝ በማለቱ ሊፈታ አልቻለም። ስለዚህ ማንም ሰው ሊቋቋመው እና ሊያስረው የማይችለው የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሮም የሚያደርገውን ጉዞ በእርሱ አማካይነት ይቀጥላል።

ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ በጳውሎስ ላይ የተፈጸመው ተግባር (እስረኛ ሆኖ በእጁ ላይ ሰሰለት የተደርገበት ሁኔታ ማለት ነው) እርሱ ለቅዱስ ወንጌል ያለውን ታማኝነት እና ከሙታን ለተነሳው ኢየሱስ የሚሰጠው ታማኝ ምስክርነት ምልክት ሆኖ ቀጥሉዋል።

ሰንሰለቶቹ በርግጥም በዓለም እይታ እንደ “ወንጀለኛ” ሆኖ ስለሚታይ ለሐዋርያቱ አዋራጅ የሆነ ፈተና ናቸው። ነገር ግን ለክርስቶስ ያለው ፍቅር ጠንካራ በመሆኑ እነዚህ ሰንሰለቶች እንኳን በእምነት ዐይን እንዲታዩ ይደረጋሉ፣ ለሐዋርያው ጳውሎስ እምነት ማለት “እግዚኣብሔርን እና ዓለምን የሚመለከት ጽንሰ-ሐሳብ ወይም አመለካከት ማለት ሳይሆን” ነገር ግን እምነት ማለት “የእግዚአብሔር ፍቅር በልቡ ላይ የሚያሳደረው ተጽዕኖ ፣ […] ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ፍቅር” ማለት ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ጳውሎስ በፈተና ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ሁሉ በጽናት እና በእምነት ሁሉንም ነገር የመመልከት ችሎታ አስተምሮናል። ዛሬ እምነታችንን እንዲያንሰራር እና ሚስዮናዊ ደቀመዛሙር በመሆን ለተሰጠን ኃላፊነት እስከመጨረሻው ድረስ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንችል ዘንድ እንዲረዳን የሐዋርያው ጳውሎስን አማላጅነት እንማጸን።

 

 

11 December 2019, 16:34