ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የታኅሳስ ወር የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ አደረጉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን በያሉበት ሆነው በጸሎታቸው እንዲተባበሯቸው በማለት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በያዝነው የታኅሳስ ወር ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ የዓለም መንግሥታት በሙሉ የእያንዳንዱን ወጣት እና ሕጻን የወደ ፊት ሕይወት የተሻለ እንዲሆን ቅድሚያን በመስጠት በርትተው እንዲሰሩ በጸሎታችን እናግዛቸው ብለዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት አስተማማኝ ያልሆነ ኑሮ እየኖሩ መሆናቸውን በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክታቸው አስታውሰዋል። በማሕበረሰብ መካከል የተናቀ፣ የተገለለ፣ የተጨቆነ፣ የትምህርት ዕድል እና በቂ የጤና አገልግሎት የተነፈገ ሕጻን ጩሄት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ይቀርባል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት አቤቱታ የዓለም መንግሥታት በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቆም የመኩላቸውን እርምጃ እንዲውስዱ የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል። ሕጻናት የሚገኙበትን ሁኔታ የሚገልጽ የጎርጎሮሳውያኑ 2016/17 ዓ. ም. ሪፖርት፣ ሁለት ዶላር የቀን ገቢ ካለው 900 ሚሊዮን የዓለማች ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን አስታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2019 ዓ. ም. ይፋ የሆነው ሪፖርት ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው ሕጻናት ያልተስተካከለ የእድገት ደርጃን የሚያሳዩ መሆናቸውን አስታውቋል። በየዓመቱ ለትምህርት የሚመዘገቡ ሕጻናት ቁጥር እድገት  ቢያሳይም ከ175 ሚሊዮን በላይ ወንድ እና ሴት ሕጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል አያገኙም። ይህን ችግር ከሚያባብሱ ምክንያቶች አንዱ በብዙ አካባቢዎች ተቀስቅሶ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ አመጾች እና ጦርነቶች መሆንቸው ታውቋል። ወደ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት ጦርነቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች በሚታዩበት ወቅት እና ጦርነትም በሚካሄድበት ወቅት ለተስተካከለ እድገት እንቅፋት በመሆን የብዙ ሕጻናት ሕይወት እንዲጨልም ያደርጋል።     

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው የቅዱስነታቸውን የጸሎት ጥሪ መሰረት በማድረግ ባቀረቡት ግብዣ እያንዳንዱ አገር የወጣቶችን እና የሕጻን የወደ ፊት ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ቅድሚያን ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ በየቀኑ በርትተው ከሠሩ፣ ትንሽ መስሎ ቢታይም ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን ያህል ካበረከተ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት ይቻላል ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለወላጆች ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው “ሕጻናት ያለ ተንከባካቢ ሲቀሩ ኢፍትሕዊ ብቻ ሳይሆን የማሕበረሰብን ውድቀት ያመለክታል” ብለዋል።

በመሆኑም እያንዳንዱ አገር ሕጻናትን በመንከባከብ እና ለወደ ፊት ሕይወታቸው በተለይ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ቅድሚያን በመስጠት መልካም ዕድሎችን ማዘጋጀት እንዲችሉ በጸሎት እናግዛቸው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታኅሳስ ወር የላኩት የጸሎት ሃሳብ መላውን ምዕመናን የሚጋብዝ መሆኑን ክቡር አባ ፍሬደሪክ አስታውሰዋል።

10 December 2019, 19:02