ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ለኮንጎ ካቶሊካዊ ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ለኮንጎ ካቶሊካዊ ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “በቁሳዊ ነገሮች ላይ መመካት እምነትን ሊጎዳ ይችላል”።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሁድ ህዳር 21/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሆነው በቫቲካን በሚገኝ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማድረሳቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሚሼል ራቪያት የላከችልን ዜና አመልክቷል። የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት የቀረበው፣ የኮንጎ ካቶሊካዊ ምዕመናን አንድነት በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ የተዋቀረበትን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመሩት እና በኮንጎ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  ስርዓተ አምልኮ በመታገዝ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ሮምን ጨምሮ ከሌሎች የጣሊያን ከተሞች የመጡ ምዕመናን የተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ ትናንት ህዳር 21/2012 ዓ. ም. የተጀመረውን የስብከተ ገና ሳምንት የመጀመሪያ ንባብ፣ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 2,1-5 የተጻፈውን  መሠረት በማድረግ ባቀረቡት ስብከታቸው  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ጊዜ ለማስታወስ በተስፋ የምንጠባበቅበት ወቅት መሆኑን ገልጸው ወቅቱ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኝ ዓለም እግዚአብሔር መጽናናቱን የላከው በቃል ሳይሆን በስጋ በመገለጥ መሆኑን እርግጠኞች የሆንንበት ነው ብለዋል።

የእግዚአብሔር ግብዣ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 2. 1-5 ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ ባደረጉት አስተንትኖ እንደገለጹት ነብዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ የተናገረው የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም እንደሚመጣ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች በአንድነት ሆነው ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንደሚመጣ በትንቢቱ መግለጹን አስረድተዋል። ነብዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ወደ ቤቱ እንድንመጣ ከእግዚአብሔር በኩል የቀረበልን ግብዣ እንዳለ መናገሩን አስታውሰው “እግዚአብሔር በቤቱ ለሁሉም የሚበቃ ሥፍራን አዘጋጅቶ እንደሚጠብቀን፣ በልቡም ለአንድ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዳችን የሚበቃ ሥፍራን አዘጋጅቶ የሚጠብቅ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ለእግዚአብሔር እንግዶች አይደለንም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ምዕመናን ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ ካቶሊካዊ ምዕመናኑ አገራቸውን እና ቤተሰባቸውን ትተው ከሩቅ አገር የመጡ መሆናቸውን እና ከፍተኛ ችግሮችን ያሳለፉ መሆናቸውን አስታውሰው ቢሆንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን እና ለእርሱም እንግዶች አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

የእግዚአብሔርን ግብዣ ቸል አለ ማለት፣

እግዚአብሔር ወደ ዓለም መምጣቱን እና ወደ እርሱ እንድንቀርብ መጋበዙን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእግዚአብሔርን ግብዣ የማይቀበሉ መኖራቸውን አስረድተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ የእርሱን ግብዣ ቸል እንዳንል ማሳሰቡን እና በኖሕ ዘመን የሆነው እንዳይደገም ማስጠንቀቁን ተናግረው በዘመኑ የሰዎች ጭንቀት ለመብላቸው እና ለመጠጣቸው ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም ሕይወታቸውን ለምግብ፣ ለመጠጥ እና ለስጋዊ ደስታ ያስገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዕለታዊ ፍጆታቸው መመካት እምነትን ይጎዳል፣

በዕለታዊ ፍጆታ ብቻ መመካት እምነትን ሊጎዳ እንደሚችል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰው ልጅ መመኪያውን በምድራዊ ሃብት ላይ ካደረገ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ሊቀንስ ይችላል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማያያዝም የሰውን ልጅ ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መምጣቱን በመዘንጋት በቁሳዊ ፍላጎት እና በምድራዊ ሃብት ላይ ብቻ መመካት በእምነት ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።

ምድራዊ ሃብት ገደብ የለውም፣

የአንዳንድ ሰዎች ቤት በምድራዊ ሃብት የበለጸገ ነገር ግን ሕጻናት የሌሉበት መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በርካታ ሰዎች ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ስዎች ቦታን የማይሰጡ መሆናቸውን፣ ይህም በሕዝቦች መካከል ቁጣን እና ጥላቻን የሚቀሰቅስ መሆኑን አስረድተዋል። በዓለማችን የጦር መሣሪያ መበራከቱን እና ይህም ለርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ መልኩ የሰው ልብም በቁጣን እየተሞላ መምጣቱን ዘንግተናል ብለዋል።

ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ነቅተን እንድንጠብቅ ይመክረናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ነቅተን እንድንጠብቅ በተስፋ ልንኖር ይገባል ብለው ዛሬ የጨለመ ቢሆንም ነገ ብርሃን መውጣቱ አይቀርም ብለዋል። በምድራዊ ሃብት ብቻ እንድንመካ የሚያደርገንን ፈተና መቋቋም ያስፈልጋል በማለት ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር የሚተሉ ሕዝቦች በተጀመረው ወር ውስጥ የሚያከብሩትን የብርሃነ ልደቱን በዓል አስታውሰው ለዚህ በዓል ሲባል የሚወጣውን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ አስታውሰው፣ ሕዝቡ እውነተኛ ሃብት የሆኑት የጸሎት እና የልግስና ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

የሰላም ስጦታ፣

ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ልባችንን ስንከፍት ምድራዊ ሃብትን የሚበልጥ ውድ ስጦታን እናገኛለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነብዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደገለጸው፣ ይህ ውድ ስጦታ ሰላም ነው ብለዋል። በሰላም ማጣት የተነሳ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ምሥራቃዊ ክፍለ ሀገር በእርስ በእርስ ግጭቶች እና አመጾች ውስጥ እንደሚገኝ እና በርካታ ሰዎች እንደሚሞቱ፣ እንደሚፈናቀሉ እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን አስታውሰው በዚህች አገር ሰላም እንዲወርድ በጸሎት መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል። አመጽን የሚያካሂዱ የአመጽ መሣሪያዎቻቸውን እንዲያስቀምጡ፣ በመካከላቸው እርቅን እና ሰላምን አውርደው በፍቅር እንዲኖሩ፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላም የሚበልጥ መሆኑን እንዲገነዘቡ የምሕረት ምሳሌ የሆነችውን የማሪ ክለሜንቲን አማላጅነት በጸሎት እንጠይቅ በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

02 December 2019, 16:53