ፈልግ

ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ2019 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ክንውኖች መካከል ጥቂቶቹ።

ማክሰኞ ታኅሳስ 21/2012 ዓ. ም. የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር ለሚከተሉት ሕዝቦች የዓመቱ መገባደጃ ዕለት ነው። የ2019 ዓ. ም. መገባደጃ ማለት ነው። በዚህ ዝግጅታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2019 ዓ. ም. ውስጥ የፈጸሟቸውን አበይት ክንውኖች፣ ከእነዚህም መካከል ከተለያዩ ሰዎች ጋር ያደረጓቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን፣ ያስተላለፏቸውን ሐዋርያዊ መልዕክቶች እና ወደ ተለያዩ አገሮች ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን የምንዳስስበት ይሆናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዘወትር አስተምህሮአቸው ከሁሉ አውቀድሞ የወንጌልን መልካም ዜና ለዓለም ማብሠር ቅድሚያ የሚሰጠው እና አስፈላጊ አገልግሎት እንደሆነ ይመክሩናል። በመገባደድ ላይ ባለው የአውሮፓውያኑ 2019 ዓ. ም. በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ጸሎት እና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ በማስተንተን ያቀረቡት 41 ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ይህን ያመለክታል። እንደዚሁም 56 በየእሑዱ የሚያቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እና የሰማይ ንግሥት ጸሎት፣ ከ60 በላይ ስብከቶች፣ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቧቸው 44 የቅዱሳት ንባባት አስተንትኖ እና ስብከቶችን ስንመለከታቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወንጌል ማብሰር አገልግሎት ቅድሚያ መስጠታቸውን ያመለከታል። እነዚህ በሙሉ የቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌል በአማቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የጻፏቸውን ሐዋርያዊ መልዕክቶች፣ ከልዩ ልዩ ከፍተኛ የመንግሥታት እና የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር የተፈራረሙትን ሰነዶች፣ ከዜና ማሰራጫ ተቋማት እና ጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልሶችን፣ በሮም እና ከሮም ውጭ ባደረጓቸው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት ያደረጓቸውን 260 ንግግሮችን ሳያካትት መሆኑ ተመልክቷል።

በእርግጠኝነት መጓዝ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. ያስተላለፉት የመጽናኛ መልዕክቶች አማካይነት እግዚአብሔር በእርግጥም እንደሚወደን፣  አንዲያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ እንዳፈቀረን አስታውሰውናል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወንጌል የሚገኝ ደስታ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ የተጠቀሰው መልዕክትም የወንጌል ተልዕኮአቸውን ቀዳሚነት ያረጋግጣል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው አማካይነት ከእናቶቻችን እና ከአባቶቻችን በወረስናት በትንሿ እምነታችን ሃይልን በማግኘት እስካሁን መጓዛችንን እና በመጓዝ ላይ መሆናችንን አስታውሰውናል። ይህ እምነታችን ምንም እንኳን በአደባባይ ጎልቶ የሚታይ ባይሆንም ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመገንባት እገዛን በማድረግ ላይ ይገኛል። ምክንያቱን እምነታችን የተመሠረተው በቅዱስ ወንጌል ላይ ነውና።

በእውነተኛ እምነት መኖር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለማዊነት እየተጠናወተው ባለ ማሕበረሰብ ውስጥ የምንገኝ በሙሉ ፊታችንን  ወደ እውነተኛው እግዚአብሔር እንድንመለከት ብርታትን የሰጡበት ዓመት ነበር 2019  ዓመት። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በዚህ ዓመት ውስጥ ባቀረቡት አንድ ስብከተ ወንጌላቸው ጣኦትን ማምለክ ማለት ወደ ጣኦት ቤት መሄድ፣ ለምስሎች መምበርከክ እና ማምለክ ሳይሆን ልባዊ ምኞቶችን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል። የተለያዩ ጣኦቶች ስማቸውን ቀይረው ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን አሁን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ከምን ጊዜም ገንነው የወጡበት ሁኔታ ይታያል ብለዋል። ገንዘብ፣ ዝና፣ ዕውቀት ፣ ራስን መቻል ፣ ከመጠን ያለፈ ደስታ እነዚህ በሙሉ ደስታን የሚሰጡ እየመሰሉ ነገር ግን መጨረሻቸው ሲታይ ወደ ሐዘን፣ ተስፋን ወደ መቁረጥ እና ወድ ባርነት በመዳረግ ወደ ጥፋት የሚመሩ ሆነው ተገኝተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ አስተምህሮአቸው ጣኦት መልካም ሕይወት እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም ሕይወትን ከመቀማት በቀር ሌላ ምንም ነገር የማይሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን በእውነት የምናመልከው እውነተኛው እግዚአብሔር ሕይወትን አሟልቶ የሚሰጠን መሆኑን መስክረዋል።

ራስን መገሰጽ ያስፈልጋል፣

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌን በመከተል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በአስተምህሮአቸው በኩል ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ አድርገው ለሚቆጥሩት ማስጠንቀቂያዎችን ከመስጠት አልተቆጠቡም። ይህም ራሳቸውን ካቶሊኮች ነን ብለው የሚያስቡት ነገር ግን ክርስቲያን እና ሰው መሆናቸውን የዘነጉ መሆናቸውን አስታውሰዋል። እነዚህ ታዲያ እግዚአብሔርን ከልብ ማምለክ የሚታወቀው ለጎረቤት በምናሳየው ፍቅር የሚገለጽ መሆኑን  የዘነጉ ናቸው በማለት አስረድተዋል። ከሌላው እሻላለሁ የሚል የፈሪሳዊነት አስተሳሰብ እንዳያጠቃን ያስጠነቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት እራሳችንን እንድናርም እና በትህትና እንድንኖር ያደርገናል ብለዋል።

ገርነት እንጂ ወግ አጥባቂነት አያስፈልግም፣

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት እርሱን በሚያምኑት እና የበለጠ ልባቸውን አደንድነው ወግ አጥባቂነት የተለወጡ ሰዎችን እንደፈጠ ሁሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሥር ነቀል የለውጥ አስተምህሮም በቤተክርስቲያን ውስጥ ልዩነቶችን እንደፈጠረ፣ ከወግ አጥባቂነት በስተጀርባ የወንጌል ቅድስና የማይታይበት መሆኑን ወደ አፍሪቃ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝትን ፈጽመው ሲመለሱ መግለጻቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ክፋትን በጎን በማድረግ እንድናሸንፍ ብዙን ጊዜ መክረውናል። በጎነታችንም በገርነት የታጀበ እንዲሆን አሳስበው፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለረጅም ዘመናት በምትከተለው አስተምህሮቸዋ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልተካሄደበት፣ ውዳሴዎችዋም ቀጣይነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀው ምዕመናኖቿ በሙሉ የአንድነትን እና የምሕረትን መንገድ እንዲጓዙ አበረታትተው ምዕመናን በሚተባበሩበት ጊዜ የቤተክርስቲያን አስተምህሮም ጥንካሬን የሚያገኝ መሆኑን እና እውነተኛውን የቤተክርስቲያን የአምልኮ ባሕልን መከተል የሚቻል መሆኑን በማስረዳት ብርታትን የሰጡበት ዓመት ነበር የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም.።

በነገር ሁሉ ኢየሱስን ማስቀደም፣

ባለፈው ጥቅምት ወር በተካሄደው የላቲን አሜሪካ አማዞን አካባቢ አገሮች ብጹኣን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈሳዊ ለውጥን ስለማሳየት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል። በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ፍጻሜ ላይ ይፋ የተደረገው ሰነድም ይህን የሚያረጋግጥ ሆኖ ተገኝቷል። በእርግጥም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በላቲን አሜሪካ በሚገኙ የአማዞን አካባቢ አገሮች መካከል መንፈሳዊ እድገቶች እንዲመጡ የሚጠቁሙ ሃሳቦችን ማንሳቱ ሲታወስ ከእነዚህም መካከል ሲኖዶሳዊ አንድነት፣ ይህም  የብጹዓን ጳጳሳት አንድነት እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸውን አንድነት በማጠናከር የቤተክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተመለከተው ርዕሠ ጉዳይ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በፍሬያማነት የምትፈጽምበት የተለያዩ ባሕሎች ግንዛቤ ሊኖራት ይገባል የሚል ነው። ሌላው ለሥነ ምሕዳር ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግ ይገባል የሚል ሲሆን ባሁኑ ጊዜ በላቲን አሜሪካ አማዞን አካባቢ የሚታየው ሃላፊነት የጎደለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ከሁሉ አስቀድሞ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን አደጋ ላይ መጣሉ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስጋት ላይ የጣለ መሆኑ ተመልክቷል። ሌላው የላቲን አሜሪካ አማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተመለከተው ርዕሠ ጉዳይ በአካባቢው አገሮች የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲሆን ይህን በተመለከተ ለአካባቢው አገሮች ሕዝቦች የወንጌልን መልካም ዜና ማብሰር እና ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ እጅግ አስቸኳይ መሆኑ ተመልክቷል። ለእነዚህ አራት ርዕሠ ጉዳዮች ትኩረትን በመስጠት በርትቶ መሥራት በቅዱስ ወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ትልቅ ለውጥን እና እድገትርን ማሳየት፣ ይህ ማለት ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ መታደስ ማለት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አበክረው አስረድተዋል። ከዚህ ጋር በማያያዝ ይህን ሁሉ ለማከናወን በራስ ከመተማመን ይልቅ የሥራውን ባለ ቤት ኢየሱስ ክርስቶስ በማድረግ፣ መንፈስ ቅዱስን የሕይወታችን ቀዳሚ ተዋናይ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

በካርዲናሎች መማክርት የተደረጉ ማሻሻያዎች፣

በመገባደድ ላይ ያለው የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የካርዲናሎች መማክርት ውስጥ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ዓመ መሆኑም ይታወሳል። ይህም መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተጣለባትን የሐዋርያዊ ተልዕኮ አደራዋን በፍሬያማነት እንድታከናውን የሚያደርጋት መሆኑ ስለታመነበት ነው ተብሏል። ይህን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማደረግ የሚያግዝ ሐዋርያዊ ሕገ መንግሥት፣ “ስብከተ ወንጌል” የሚል ስያሜን በማግኘት በድጋሚ በመረቀቅ ላይ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ፣ የካርዲናሎች መማክርት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ሶዳኖ፣ ከጎርጎሮሳውያኑ 2005 ዓ. ም. ያበረከቱትን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን መፈጸማቸው ይታወሳል። የተሰጣቸውን የግል ውሳኔ መብትን በመጠቅም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካርዲናሎች መማክርት ዋና ተጠሪነት በአምስት አመት እንዲገደብ፣ አስፈላጊ ከሆነ ገደቡ የሚሻሻል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውቀዋል።

የቃለ እግዚአብሔር እሑድን ማጽደቅ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስከረም 19/2012 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ከታላላቅ የቤተክርስቲያን በዓላት በኋላ የሚከበረው ሦስተኛ እሑድ፣ ይህም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀተ በኋላ የሚውለው ሦስተኛ እሑድ ልዩ የቃለ እግዚአብሔርን እሑድ እንዲሆን ብለው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ ሦስተኛው ዕለተ ሰንበት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጥልቅ አንተንትኖን በማድረግ አብረው የሚያጠኑበት፣ ወደ ሌሎችም ዘንድ ለማድረስ የሚነሳሱበት እንዲሆን በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግል ተነሳሽነት በማጽደቅ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ርዕሥ በላቲን ቋንቋ “Aperuit illis” የሚል ሲሆን በግርድፉ ሲተረጎም “ግልጽ ሆነላቸው” የሚል ሲሆን ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በመታየት ቅዱሳት መጻሕፍትን መረዳት የሚችሉበትን አእምሮ እንደከፈተላቸው የሚገልጽ ክፍል መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል(ሉቃ. 24.45) ። በቤተክርስቲያን ሕይወት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ እና መረዳት አስፈላጊነት አስመልክቶ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግል ተነሳሽነት በወሰዱት ሐዋርያዊ ውሳኔያቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ምዕመናን ላቀረቡት ጥያቄ መልስ መሆኑን አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የእግዚአብሔርም ቃል እንደሚያሳስበን ሁሉ፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ከሚከተሉት እና ከሚያዳምጡት የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ያለንን እውነተኛ አንድነት ለማጠንከር ትልቅ መንፈሳዊ ሃይል የሚጨምር መሆኑን አስታውቀዋል።     

ለወጣቶች ብርታት ሆነዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በጣሊያን ውስጥ ባደረጉርት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል በሎረቶ ከተማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ያደረጉት ጉብኝት የሚጠቀስ ሲሆን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማም ከአካባቢው ምዕመናን ጋር በሕብረት ለመጸለይ እንደነበር ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ጉብኝታቸው ከጣሊያ ክፍላተ ሀገራት ከመጡ ወደ 800 ከሚጠጉ ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው ሲታወስ ወጣቶቹ በየዓመቱ ወደ ሎሬቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ድረስ ያደረጉትን መንፈሳዊ ጉዞ መካፈላቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለወጣቶች በሙሉ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዘንድሮ በቫቲካን ከተማ ወጣቶችን አስመልክቶ ካደረገው 15ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ያወጣውን “ክርስቶስ ሕያው ነው” የሚል የድህረ ሲኖዶስ ሰነድ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል።

ቤተክርስቲያን ዘወትር ታብባለች፣ 

ከብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እምነትን በተግባር የሚኖሩበት፣ ከተለያዩ ችግሮች ወጥተን በወንድማማችነት መንፈስ በአንድነት የምንጓዝበትን መንገድ ማበጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ስለዚህ ወጣቶች ማኅበራዊ አንድነትን እንዲያሳድጉ፣ ለጋራ ጥቅም እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ የቸርነትን ተግባር እንዲያበረክቱ፣ ከድሆች ጎን ቆመው እንዲያገለግሏቸው፣ የግለኝነት እና ከሚያስፈልገው በላይ የመሸመት ስሜት እንዳያጠቃቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል።          

ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን አድርገዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገባደደው የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. ብቻ ሰባት ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ሲታወስ በእነዚህ ሰባት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በአራት አህጉራት ውስጥ ወደ አስራ አንድ ሃገራት በመሄድ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው፣ በሰባት የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ውስጥ ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ዓመት መሆኑ ታውቋል። ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በፓናማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የጀመሩት ቅዱስነታቸው በመቀጠልም

በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡዳቢ ከተማ ላይ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ዶ.ር አህመድ አል ጣይብ ጋር የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስድቀው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በሞሮርኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሐይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት በማሳደግ፣ ቀጥለውም በቡልጋሪያ፣ መቄዶኒያ እና ሮማኒያ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላቸውን አንድነት ማሳደጋቸው ይታወሳል። ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ ባደረጉት የአፍሪቃ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት አቅመ ደካማ ለሆኑት የማሕበረሰብ ክፍሎች ከለላ ሊደረግላቸው እንደሚገባ፣ ለተፈጥሮም አስፈላጊው ጥበቃ እና እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ በመልዕክታቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። የሩቅ ምስራቅ እስያ አግሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በታይላንድ የሕጻናት እና የሴቶች መብት እንዲከበር አሳስበው፣ በጃፓንም ባሰሙት የሰላም ጥሪ መልዕክታቸው አውዳሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች መጠቀም ኢ-ሰብዓዊ መሆኑን ማሳሰባቸው ይታወሳል።  

በጣሊያን ውስጥ ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል በካሜሪኖ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዱትን አጽናንተው መመለሳቸው ሲታወስ፣ በሎሬቶ ባደረጉትም ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በወጣቶች ጉዳይ ላይ የተሰበሰበው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ ሰነድ አጽድቀው ይፋ ማረጋቸው ይታወሳል። ቀጥለውም በግሬቾ ከተማ ውስጥ የአሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የከብቶች ግርግም የሚያሳይ ትዕይንት መጎብኘታቸው ይታወሳል።   

ቅዱሳንን እና ብጹዓንን ይፋ አድርገዋል፣  

የጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅዱሳን እና ብጹዓን ይፋ የተደረጉበት ዓመት እንደሆነም ይታወቃል። በስፔን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙ ምዕመናን መገደላቸው፣ ከእነዚህም መካከል በእምነታቸው ላይ በተነሳው ጥላቻ ምክንያት የተገደሉ እና ለሰማዕትነት የበቁ መኖራቸው ታውቋል። በሌሎች አገሮችም እንደዚሁ፣ በሮማኒያ ውስጥ ሰባት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በኮሚኒስት ስርዓት አገዛዝ መገደላቸው ይታወሳል። አርጀንቲናዊ ጳጳስ አቡአነ ሄንሪቅ አንጀለሊ ከአበሮቻቸው ጋር በአምባገነናዊ መንግሥት እጅ መገደላቸው ይታወሳል። በስዊዘርላንድ ከምዕመናን ወገን የሆኑትም ለቅድስና መብቃታቸው ይታወሳል። ለቅድስና ከበቁት መካከል የአንግሊካን ቤተክርስቲያን አባል የነበሩት በኋላ ወደ ካቶሊክ እምነት የመጡት ካርዲናል ጆን ሄንሪ ኒውማን ይገኙበታል።

50 ዓመት የክህነት ሕይወት።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የክህነት ሕይወት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ያከበሩበት በጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። በሰላሳ ሦስት ዓመት ዕድሜአቸው የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ራሳቸውን ያዘጋጁት የኑዛዜ ምስጢርን ከፈጸሙ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባገኙት ምሕረት እና ቆራጥ ውሳኔ መሆኑ ታውቋል። የክህነት ሕይወት መለኮታዊ ምሕረት የተገለጠበት መሆኑን የተናገሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካህናት በምእመናን መካከል ምሕረትን እና ርህራሄን የሚያደርግ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ይዘው እንደሚገኙ አስረድተው ያለንበት ዘመን የምሕረት ዘመን እንደሆነ ተናግረዋል።

 

31 December 2019, 19:49