ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ዛሬ ምሽት የእግዚኣብሔር የፍቅር ብርሃን ተገልጾልናል” አሉ።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እየተከበረ እንደ ሚገኝ ይታወቃል። የእዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመሩት እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ በታኅሳስ 14/2012 ዓ.ም መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “ዛሬ ምሽት የእግዚኣብሔር የፍቅር ብርሃን ተገልጾልናል” ማለታቸው ተዘግቡዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

“ነገር ግን ተጨንቀው የነበሩ ከእንግዲህ ተስፋ ቢስ አይሆኑም!” (ኢሳያስ 9:1)። ይህ በመጀመሪያው ንባብ ውስጥ የሰማነው ትንቢት በወንጌ ውስጥ ፍጻሜውን አግኝቱዋል - እረኞች በሌሊት መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ፣ “የእግዚአብሔር ክብር በዙሪያቸው አበራ” (ሉቃስ 2፡9)። በምድራዊ ጨለማ ውስጥ ፣ ከሰማይ ብርሃን ተገለጠ ፡፡ በጨለማ ውስጥ የሚያበራ የዚህ ብርሃን ትርጉም ምንድን ነው? ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ” ሲል ይናገራል።  ለሁሉም “ድነትን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ጸጋ (ቲቶ 2፡ 11) ፣ በዚህ ምሽት በአለማችን ላይ ብቅ ብሏል።

ነገር ግን ይህ ጸጋ ምንድነው? ህይወትን የሚቀይር ፣ ታሪክን የሚያድስ ፣ ከክፉ ነገር ነፃ የሚያወጣ፣ መለኮታዊ ፍቅር ነው፣ በሰላምና በደስታ ይሞላናል። በዛሬ ምሽት የእግዚአብሔር ፍቅር ተገለጠልን እርሱም ኢየሱስ ነው።  በጣም ታላቅ እና ልዑል የነበረው ኢየሱስ እንወደው ዘንድ ራሱን ትንሽ እጅግ ትንሽ አድርጎ አቀረበ። ነገር ግን አሁንም እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን - ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ወደ ዓለም የመጣበትን ሁኔታ ሲገልጽ “ጸጋ” በማለት የገለፀው ለምንድነው? ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑን ለእኛ ለመናገር አስቦ ነው። በምድር ላይ ሁሉም ነገር የሚገኘው በመስጠት ሲሆን ነገር ግን እግዚአብሔር በነጻ ወደ እኛ ይወርዳል። ፍቅሩ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም፣ እኛም ለእርሱ የሚገባውን ነገር አላደረግንም ውለታውን ሙሉ በሙሉ ለመክፈል በጭራሽ አንችልም።

የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ ፡፡ ዛሬ እኛ ይህንን የእግዚኣብሔር ጸጋ መለካት ባቃተን ጊዜ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ትንሽ ሆኖ እንደ መጣ እንገነዘባለን፣ እኛ ወደራሳችን ሥራ በምንሄድበት በአሁኑ ጊዜ እርሱ በመኃላችን ገባ። የገና በዓል እግዚኣብሔር ሁላችንንም መውደዱን እንደሚቀጥል ያስታውሰናል። ለእኔ፣ ለሁላችንም፣ ለእያንዳንዳችን ሳይቀር ዛሬ “እወድሃለሁ፣ ሁሌም ቢሆን እወድሃለው፣ አንተ በዐይኔ እይታ ውስጥ ውድ ነህና” በማለት ይናገራል።

እግዚኣብሔር የሚወድህ በትክክለኛ ሁኔታ ስላስብክ እና በትክክለኛው መንገድ ላይ ስልተጓዝክ አይደለም። እርሱ ይወድሃል፣ ይህም ግልፅ እና ቀላል ነገር ነው። ፍቅሩ በመስፈሮች ላይ የተመሰረተ አይደለም፣ የሚወድህ በአንተ ስለተመካም አይደለም። የተሳሳቱ ሀሳቦች ሊኖሩህ ይችሉ ይሆናል ፣ ብዙ ስህተቶችን የሰራህ ሰው ልትሆን ትችል ይሆናል፣ ነገር ግን ጌታ አንተን መውደዱን ይቀጥላል። እኛ ጥሩ ሰው በምንሆንበት ወቅት እግዚኣብሔር ለእኛ መልካም፣ መጥፎ ሰዎች ስንሆን ደግሞ እግዚኣብሔር እንደ ሚቀጣን ሆኖ የሚሰማን ምን ያህል ጊዜ ነው? ነገር ግን እሱ እንደዚያ አይደለም ። ከነኃጢያታችን ሁሉ እርሱ እኛን መውደዱን ይቀጥላል። ፍቅሩ አይለወጥም። እሱ ተለዋዋጭ አይደለም; ታማኝ ነው፣ ታጋሽ ነው። በገና በዓል ላይ የምናገኘው ስጦታ ይህ ነው። ጌታ በነጻ የሚሰጠን ፍጹማዊ በሆነ ፍቅር የሚወደን መሆኑን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ እንረዳለን።  የእርሱ ክብር አያሸብረንም የእርሱ ከእኛ ጋር መሆን አያስፈራንም። በጣም አስቸጋሪ በሆነ ድህነት ውስጥ የተወለደው በከፈተኛ ፍቅር ልባችንን ለማሸነፍ ነው።

የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ። ጸጋ የውበት ተመሳሳይ ቃል ነው። ዛሬ ማታ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ እኛ የራሳችንን ውበት እንመለከታለን፣ ምክንያቱም እኛ በእግዚአብሔር የተወደድን በመሆናችን የተነሳ። በመልካም ወይም በክፉ፣ በበሽታ እና በጤና፣ በደስታ ሆነ በሐዘን፣ በእሱ ፊት ቆንጆዎች ነን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት እኛ በሰራነው መልካም ነገር ሳይሆን፣ እኛ የእርሱ በመሆናችን የተነሳ ነው። በውስጣችን ጥልቅ ፣ የማይታይ እና የማይዳሰስ ውበት፣ ልናልመው ከምንችለው በላይ የሆነ ውበት አለ፣ ይህም የእኛነታችን ዋና አካል ነው ፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ይህንን ያስታውሰናል ፡፡ እሱ በፍቅር ተነሳስተን ሰብአዊነታችንን እራሱን ወስዶ የእሱ እንዲሆን ያደርገዋል ፣ እናም ለዘላለም የእርሱ ያደርገዋል።

ዛሬ ማታ ለእረኞቹ የተነገረው “ታላቅ ደስታ” “ለመላው ህዝብ የተነገረ ነው። እኛ ሁላችንም ከነድክመቶቻችን እና ከእነውድቀቶቻችን ሁሉ በእውነቱ ቅዱሳን ካልነበሩ ከእረኞች መካከል እንመደባለን። እግዚአብሔር እረኞችን እንደጠራ ሁሉ እርሱ እኛን ሰለሚወደን እኛንም ይጠራናል። እርሱ ይወደናልና። በጨለማ ውስጥ በነበሩበት ሕይወት እረኞቹን “አትፍሩ!” (ሉቃ 2 10) ብሎ እንደ ተናገረው ሁሉ እኛንም አትፍሩ ይለናል። አይዞህ፣ በርታ፣ ተስፋ አትቁረጥ ፣ መውደድ ጊዜ ማባከን ማለት አይደለም ይለናል። ዛሬ ማታ ፍቅር ፍርሃትን አሸንፉል ፣ አዲስ ተስፋም ፍንጥቋል፣ የእግዚአብሔር ደግ ብርሃን በእብሪት የተሞላውን የሰውን ጨለማ አሸንፉዋል። የሰው ልጅ ሆይ!፣ እግዚአብሔር ይወድሃል! በአንተ ምክንያት ሰው የሆነው እርሱ ይወድሃል። ከእንግዲህ ብቸኛ አይደለህም!

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ይህንን ጸጋ ምን እናድርግ? አንድ ነገር ብቻ ማድረግ ይጠበቅብናል፣ ይህም ይህንን የጸጋ ስጦታ መቀበል ነው። እግዚአብሔርን ለመፈለግ ከመሄዳችን በፊት እርሱ እንዲፈልገን እራሳችንን ለእርሱ እናስገዛ። በራሳችን ችሎታዎች አንጀምር ፣ ነገር ግን በእርሱ ጸጋ ፣ እርሱ ኢየሱስ እርሱ አዳኝ ነውና። በልጁ ላይ እናሰላስል እና በእርሱ ኃይለኛ ፍቅር እንያዝ። ያኔ እራሱ በእርሱ እንዳንወደድ ላለመፍቀድ ምንም ተጨማሪ ሰበብ አይኖረንም። በሕይወታችን ውስጥ ስሕተት ያለ ከሆነ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ችግሮች የሚታዩ ከሆነ፣ በዓለም ላይ የትኛውም ችግር ቢኖር፣ እንደ ሰበብ ከእንግዲህ አያገለግልም። ከኢየሱስ ድንገተኛ ፍቅር ፣ የየዋህነት እና የጠበቀ ቅርበት ፍቅር ጋር እነዚህ ነገሮች ፊት ለፊት ሲታዩ ሁለተኛ ነገር ይሆናሉ፣ ስለዚህ ሰበብ የለንም። በገና በዓል ላይ ጥያቄው “እግዚአብሔር እንዲወደኝ እፈቅድለታለሁ ወይ? እኔን ለማዳን በመጣው ፍቅር እታመናለሁ ወይ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል።

ስለዚህ ለእዚህ ታላቅ ስጦታ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል። ይህንን ጸጋ መቀበል ማለት በምላሹ ለማመስገን ዝግጁ መሆን ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ህይወታችንን በእንደዚህ ባልይ ትናንሽ ምስጋና በማቅረብ መኖር ይኖርብናል። ወደ ማደሪያው ድንኳን ወደ ከብቶች በረት ወደ ግርግሙ ለመቅረብ እና ለማመስገን ዛሬ ትክክለኛ ቀን ነው። ስጦታ የሆነውን ኢየሱስን እንቀበል፣ እንደ ኢየሱስ ሆነን እንኖር ዘንድ ኢየሱስ የሆነውን ስጦታ እንቀበል ፡፡ ስጦታ መሆን ለሕይወት ትርጉም መስጠት ማለት ነው። እናም ዓለምን ለመለወጥ ምርጡ መንገድ ነው ፣ እኛ እንቀየራለን ፣ ቤተ-ክርስቲያን ትለወጣለች ፣ ታሪክ ይለወጣል ፣ ሌሎችን ለመለወጥ ከመሞከር ይልቅ በቅድሚያ ራሳችንን ብንለውጥ ራሳችንን እና ሕይወታችንን ስጦታ አድርገን እናቀርባለን ማለት ነው።

ዛሬ ማታ ኢየሱስ ይህንን ያሳያል። እሱ በህይወቱ ስጦታ ሆኖ መጣ እንጂ ማንንም በማስገደድ እና ብዙ ቃላትን በመናገር አለወጠም። እርሱ እኛን ከመወደዱ በፊት ጥሩ እስክንሆን ድረስ አልጠበቀንም፣ ነገር ግን እራሱን ለእኛ ሰጠን። ጎረቤቶቻችን መልካም እስኪሆኑ ድረስ ጠብቀን ለእነርሱ መልካም ማደረግ የለብንም፣ ቤተክርስቲያንን ለመወደድ የግድ ቤተክርስቲያን ፍጹም እስክትሆን ድረስ መጠበቅ የለብንም፣ ሌልቾ ሰዎች እስኪያከብሩን ድረስ ጠብቀን እነርሱን መውደድ የለብንም። በመጀመሪያ በራሳችን እንጀምር ፡፡ የፀጋ ስጦታን በነፃነት መቀበል ማለት ይህ ነው ፡፡ ቅድስና ይህንን ነፃነት ከመጠበቅ የበለጠ የተሻለ ትርጉም የለውም።

አስደሳች በሆነ መልኩ የኢየሱስ ልደት ታሪክ የተነገራቸው እረኞች ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይዘው ወደ ከብቶች በረት ግርግም በፍጥነት ሮጠው ሄዱ። እያንዳንዳቸው ያለቸውን አመጡ; ጥቂቶች የጉልበታቸውን ፍሬ፣ ሌሎቹ ደግሞ ጥቂት ውድ ነገሮችን አመጡ ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ስጦታቸውን ያቀረቡት በጣም ብዙ ነገር አላቸው ተብለው የማይታሰቡት እረኞች ነበሩ። እነርሱ በጣም ድሃ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን እነርሱ የነበራቸውን ነገር ለመስጠት በመሽቀዳደም ላይ በነበሩበት ወቅት አንድ ምንም መስጠት የማይችል ሰው ከእነሩስ ጋር ነበር። እርሱም በሁኔታው እጅግ አፍሮ ነበር፣ ጉዳዩም ተስምቶት ነበር። በአንድ ወቅት ቅዱስ ዮሴፌ እና እመቤታችን ማርያም የመጣላቸውን ስጦታ ለመቀበል እስከሚያዳግታቸው ድረስ ከባድ ሆኖባቸው ነበር።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እጆቻችሁ ባዶ ሆኖው የሚሰማችሁ ከሆነ፣ ልባችሁ ፍቅር የሚጎለው መስሎ የሚሰማችሁ ከሆነ፣ በእዚህ ምሽት የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችሁ ውስጥ እንዲገለጥ፣ ይህንን ብርሃን ተቀበሉ፣ የገና በዓል ብርሃን በውስጣችሁ ያበራልና።

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የገና ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት
24 December 2019, 19:00