ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቅድስት መንበር ሠራተኞች የብርሃነ ልደቱን መልካም ምኞታቸውን ገለጹ።

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ታኅሳስ 15/2012 ዓ. ም. የሚከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ቅዳሜ ታኅሳስ 11/2012 ዓ. ም. መልካም ምኞታቸውን ተለዋውጠዋል። በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት በሙሉ ለሚያበረክቱት ውጤታማ ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከህዳር 9-16 ቀን 2012 ዓ. ም. የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች ወደ ሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን ያደረጉትን 32ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማስታወስ ንግግር ያደረጉት ቅዱስነታቸው፣ በጉብኝታቸው ወቅት የታይላንድ ሕዝብ ያሳየውን ፈገግታ እና ትህትና አስታውሰው፣ ሰብዓዊ ፍቅራቸውን የገለጹበት እና የማይረሳ ትዝታ በልባቸው ውስጥ መቅረቱን አስረድተዋል።

“ፈገግታ” በሚለው ቃል ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው፣ አዲስ የተወለዱ ሕጻናት እኛ የምናሳያቸውን ፈገግታ በመመልከት የተሰማቸውን ደስታ በፈገግታ የሚገልጹ መሆኑን አስረድተው፣ ፈገግታቸውም ከልብ እና እንደ ምንጭ ውሃ የጠራ ነው ብለዋል። ፈገግታ ቅዱስ ቤተሰብ በሆኑት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በቅዱስ የሴፍ እና በሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከልም በተለየ መልኩ መገለጹን የተናገሩት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ ለሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅራቸውን በገለጡበት ጊዜ ልባቸው በሰማያዊ ደስታ መሞላቱን አስታውሰዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ደስታ እና ፈቃዱንም ሊያሳየን ወደ ዓለም መምጣቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ በቅድሚያ የተመለከቱት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ መሆናቸውን ተናግረው፣ በልባቸው ውስጥ ጠብቀው በያዙት ታላቅ እምነት በመታገዝ፣ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም የመጣው፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመጠባበቅ ላይ ነበሩት በሙሉ መሆኑን አስረድተዋል። የኢየሱስ ክርስቶን ብርሃነ ልደት በመመልከት እኛም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ ዮሴፍን ደስታ እንጋራለን ብለው፣ ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ በመመልከት እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ፣ የእርሱን ምሕረት በተስፋ ለሚጠባበቁት፣ ከአመጽ እና ከጦርነት ነጻ የሆነውን ዓለም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚመጣውን ክብር ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

በቫቲካን ውስጥ በሚገኙ የቅድስት መንበር ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶችም ከሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነው ደስታ ዛሬም በድጋሚ እንዲገለጥ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሥራችን እና በአገልግሎታችን ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲገለጥ ያስፈልጋል ብለው ይህን ካደረግን መልካም ሥራዎቻችንን እንዳናከናውን እቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች ሁሉ ከልባችን ውስጥ ማስወገድ እንችላለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሥራ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ለመልካም ውጤት የምንበቃባቸው ጊዜያት እና የሥራ ዘርፎች አሉ ብለው ፍሬያማነት ያለው ሥራ የሚለካው ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እና የአኗኗር ዜይቤ ነው ብለው ይህ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቤተክስቲያንን በማገልገል ላይ የሚገኙትን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል።

አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች የደስታ ፊትን ማሳየት ከባድ ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ በሚሆንበት ጊዜ በእግዚአብሔር ደስታ የሚሞላን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን አስረድተው መዳኛችንም እርሱ ብቻ ነው ብለዋል። በደስታም የምንሞላባቸው ጊዜያት አሉ ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህ ጊዜ በሐዘን ውስጥ የሚገኙ መኖራቸውን በማስታወስ በምንም ሳንመካ እውነተኛውን የእግዚአብሔር ደስታ በመለመን ከሐሰተኛ እርግጠኝነት በመራቅ፣ ራስን ዝቅ በማድረግ የትህትናን ሕይወት መኖር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙት ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ለሚሰሩት እና ለቤተሰቦቻቸው በሙሉ ያቀረቡትን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት እንዳስረዱት፣ ብርሃነ ልደቱን በሚያስታውሱን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እና ሌሎችንም የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች ከልብ በመሳተፍ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጠልንን የእግዚአብሔር እውነተኛ ደስታ ልናስታውስ ይገባል ብለው፣ የብርሃነ ልደቱ መልካም ምኞታቸውን ለተቀሩት ቤተሰቦቻቸው፣ በተለይም በሕመም ላይ ለሚገኙት እና አቅመ ደካማ ለሆኑት እንዲያደርሱላቸው አደራ ካሉ በኋላ በጸሎት እንተባበር ብለው መልካም የብርሃነ ልደት በዓልን በመመኘት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

  

21 December 2019, 15:29