ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

የሕይወት ፈተና ለማሸነፍ “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” ይኖርብናል

የጎርጎስሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ-ክርክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል በታኅሳስ 15/2012 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከተከበረበት የገና በዓል በመቀጠል ባለው እለት የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ሰማዕት ተብሎ የሚጠራው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል እንደ ሚከበር ይታወቃል። የእዚህ  የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም. በተከበረበት ወቅት በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ባሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መጋፈጥ እንድንችል “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን የቅዱስ እስጢፋኖስን ዓመታዊ በዓል አስመልክተው ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ዛሬ ይከበራል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምዕራፍ (6-7) ውስጥ ስለሱ የሚያወሳ ሲሆን እናም በዛሬው የስረዓተ አምልኮ በእርሱ ማለትም በቅዱስ እስጢፋኖስ በሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የገጠመውን ስቃይ እና መወገር ለእኛ ገልጦልናል (የሐዋ. 6,12; 7,54- 60 ይመልከቱ)። በገና በዓል አስደሳች ወቅት ለእምነቱ የተገደለው የመጀመሪያው ክርስቲያን መታሰቢያ በዓል ብቅ ማለቱ ያለቦታው የተከሰተ በዓል ሊመስል ይችል ይሆናል። ሆኖም በትክክል በእምነት እይታ፣ የዛሬው በዓል ከገና ትክክለኛ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነው። በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት፣ በእውነቱ አመጽ በፍቅር ፣ በሞት በህይወት መሸነፉን ያሳያል፣ እርሱ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እምነቱን በመሰከረበት ወቅት የተከፈተ ሰማይ ይመለከታል፣ ለአሳዳጆቹም ይቅርታ ያደርግላቸዋል።

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ይህ ወጣት የወንጌል አገልጋይ ኢየሱስን በቃላት እና ከሁሉም በላይ በሕይወቱ ውስጥ ለመተረክ ችሏል። የእርሱን ሕይወት ስንመለከት “በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና” (ማቴ 10፡19-20)  በማለት ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም እናያለን።  በሕይወትም ሆነ በሞቱ ውስጥ ከጌታው ጋር በተመሳሰለ የቅዱስ እስጢፋኖስ አስተምህሮ ውስጥ፣ እኛም በአብ የታመነ እውነተኛ የኢየሱስ ምስክርነት ላይ ማተኮር እንደ ሚገባን እንማራለን። ለዘለአለም ህይወት እና ለሰማይ ክብር የሚያበቃን ሀብት እና ስልጣን ሳይሆን ነገር ግን ፍቅር እና ራስን በመስጠት እንደ ሆነ እንማራለን።

በእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚያግጥሙን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች በተገቢው ሁኔታ ለመጋፈጥ እና በተስፋ የተሞላ ምላሽ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ ትኩረታችንን “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” (ዕብ 12፡2) ይገባናል።  ለእኛ ክርስቲያኖች ፣ ሰማይ ከእንግዲህ ወዲህ ከምድር እጅግ የተለየ ሩቅ አይደለም፣ በኢየሱስ አማካይነት ሰማይ ወደ ምድር ወረደ። ለእርሱ ምስጋና ይግባውና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መላውን የሰው ልጅ መገናኘት እና ወደ መንግስተ ሰማይ መምራት እንችላለን። የመጀመሪያው ምስክርነት ትክክለኛ ሰው የመሆን ባሕሪይ ሲሆን በኢየሱስ መሠረቱን ያደረገ የአኗኗር ዘይቤ የሆኑትን ገርነት እና ብርታት፣ ትሑት እና ክቡር ፣ ዓመፀኛ ያልሆነ ነገር ግን ጠንካራ ባሕሪይ መላበስ ይኖርብናል።

እስጢፋኖስ ከቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዲያቆናት መካከል አንዱ ነበር (ሐዋ. 6: 1-6)። እርሱ በወንድማማችነት መንፈስ እና በቅዱስ ወንጌል የተቀባ ፍቅር አማካይነት ክርስቶስን እንድናውጅ አስተምሮናል። የእርሱ ምስክርነት በሰማዕትነት የሚጠናቅቅ ሲሆን፣ ለእኛ የክርስቲያን ማህበረሰባች እድሳት የመነሻ ምንጭ ነው። እነሱ የበለጠ የወንጌል ተልዕኮ እንዲያፋፍሙ የተጠሩ ሲሆን ሁሉም ቅዱስ ወንጌልን ለማብሰር የሚጥሩ በየተኛውም የመልካምድር አቀማመጥ ውስጥ ለሚገኙትን ሰዎች ቅዱስ ወንጌልን ለማዳረስ እና የመዳን ጥማት ያላቸውን ሰዎች ጥም ለማርካት ተጠርተዋል። ዓለማዊ አመክንዮን የማይከተሉ ማህበረሰቦች ራሳቸውን ማዕከል ያላደረጉ፣ የራሳቸውን ምስል የማይከተሉ ሲሆን ነገር ግን ለየት ባለ መልኩ የእግዚአብሔር ክብር እና የሰዎችን መልካምነት፣ በተለይም አቅመ ደካማ እና ድሃ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት ይሰጣሉ።

የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ትናንት እና ዛሬ ያሉትን ሰማዕታት ሁሉ እንድናስታውስ ፣ ከእነሱ ጋር ህብረት እንዳለን እንዲሰማን፣ በልባችን እና በከንፈሮቻችን የኢየሱስን ስም በማኖር እንድንኖር ኣና እንድንሞት ጸጋ እንዲያሰጡን ልንማጸናቸው የገባል። የአዳኙ እናት የሆነቺው ማርያም እይታችንን በኢየሱስ ላይ በማደረግ በየቀኑ ከእርሱ ጋር የተመሳሰለ ሕይወት በዚህ የገና ወቅት እንድንኖር እንድትረዳን ልንማጸናት የገባል።

 

26 December 2019, 13:35