ፈልግ

መሐመድ አብዱ አል-ሳላም፣ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ካርዲናል አዩሶ ጉዊጉሶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሐመድ አብዱ አል-ሳላም፣ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ካርዲናል አዩሶ ጉዊጉሶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 

እ.አ.አ በየካቲት 04 በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድማማችነት ቀን እንዲከበር ጥያቄ ቀረበ።

“እኛ አማኝ የሆንን ሰዎች እጅ ለእጅ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ፣ መሳሳም እና አብረን መጸለይ ካልቻልን፣ እምነታችን ተሸናፊ ይሆናል” በማለት ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 26/2011 ዓ.ም  “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በአቡ ዳቢ ተካሂዶ በነበረው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብስባ ላይ መካፈላቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ “በእግዚኣብሔር ላይ እያንዳንዳችን ያለን እምነት ኅበረት እንዲኖረን ያደርጋል እንጂ አይከፋፍለንም” በማለት በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በአቡ ዳቢ በነበራቸው ቆይታ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮቻቸው ጋር ቆይታ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም ደግሞ እርሳቸው “ወንድሜ እና ጓደኛዬ” በማለት ከሚጠሩዋቸው የግብፅ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ ጋር መገናኘታቸው እና በዓለም ዙሪያ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የሁለቱ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ማለትም የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ምዕመናን በወንድማማችነት መንፈስ በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ ይኖሩ ዘንድ የሚያስችላቸው የመግባቢያ የሰላም ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

በወቅቱ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል አርእስት የተሰጠው የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የግብፅ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ ጋር የተፈራረሙት የሰላም የመግባቢያ ሰንድ “ታሪካዊ” መሆኑን ገልጸው ይህ የሰላም መግባቢያ ሰነድ የተዘጋጀው “ከፍተኛ የሆነ አስተንትኖ እና ጸሎት ከተደረገ” በኋላ እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው “ይህ የሰላም መግባቢያ ሰነድ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ በመንጸባረቅ ላይ ያሉ አስከፊ የሆኑትን “ጦርነቶች፣ ውድመቶችን እና የእርስ በእርስ ጥላቻን” ለማስወገድ በማሰብ በጥንቃቄ የተዘጋጀ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“እኛ አማኝ የሆንን ሰዎች እጅ ለእጅ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ፣ መሳሳም እና አብረን መጸለይ ካልቻልን፣ እምነታችን ተሸናፊ ይሆናል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህም መሰረት ይህ እርሳቸው እና የግብፁ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም የሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ የተፈራረሙት የሰላም የመግባቢያ ሰነድ “የተወለደው የሁሉም አባት ከሆነውና የሰላም አባት ከሆነው በእግዚአብሔር ላይ ካለን እምነት ነው፣ እርሱም በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የአሸባሪዎች ጥቃት ከሆነው ከቃየን የሽብር ዘመቻ ጀምሮ ያሉትን ውድመቶች እና የአሸባሪዎች ጥቃት ያወግዛል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል አርእስት ይፋ የሆነው ሰነድ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሕዝቦች ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደርገውን ጥረት ለመደገፍ በማሰብ ይህን ሰነድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚቴ በቅርቡ በሁለቱ መንፈሳዊ አባቶች ማለትም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ፍራንቸስኮስ እና በግብፅ የአልዓዛር ታላቁ መስጊድ እና ዮኒቬርሲቲ ታላቁ ኢማም የሆኑት ሼክ አህመድ ሙሀመድ ኣል ታይብ በተሰጣቸው ውክልና መሰረት “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል አርእስት ይፋ በሆነው ሰነድ ውስጥ የተጠቀሱትን ዓላማዎች በተገቢው ሁኔታ ለማሳከት ይችላ ዘንድ በየዓመቱ እ.አ.አ በየካቲት 04 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድማማችነት ቀን እንዲከበር በኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ ለሆኑት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጥያቄ ማቅረባቸው ለቫቲካን ሬዲዮ ከደርሰው ዘገባ ለመረዳት ተመረዳት ተችሉዋል። በቀረበው ጥያቄ መሰረት “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የተሰኘ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማክበር ባሻጋር “ሰብዓዊ ወንድማማችነትን” በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሕዝቦች መካከል ለማስፈን ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉባሄ ይደረግ ዘንድ አክለው መጠየቃቸው ተገልጹዋል።

በካርዲናል አዩሶ ጉዊጉሶ እና የሕግ ባለሙያ በሆኑት መሐመድ አብዱ አል-ሳላም የሚመራው “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” አስመልክቶ በእዚህ ሰነድ ላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለማሳካት ይችላ ዘንድ በሁለቱም የእመነት ተቋማት ኃላፊነት የተሰጣቸው የኮሚቴ አባላት እንደ ሆኑ ተያይዞ ከደርሰን ዜና ለመረዳት የተቻለ ሲሆን የእዚህ ኮሚቴ አባላት በኒው ዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዚ ጋር በተገናኙበት ወቅት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና በግብፅ የታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ የተላከውን እና በየዓመቱ እ.አ.አ በየካቲት 04 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድማማችነት ቀን እንዲከበር ያቀረቡትን ጥያቄ ለዋናው ጸሐፊ ማቅረባቸው ተገልጹዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አድናቆት እና ትብብር

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው በግንኙነቱ ወቅት እንደ ገለጹት ለሰው ልጆች ሁሉ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊነት በመግለጽ ሁለቱ የእመት ተቋማት በእዚህ ረገድ እያደረጉት የሚገኘውን መልካም ተግባር እና ተነሳሽነት እንደ ሚያደንቁ ገልፀዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥላቻ ንግግር እና የዘር ማጥፋት ዘመቻን ለመከላከል ይቻል ዘንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በእዚህ አውድ የታቀዱትን ተግባራት ለመከታተል እና ከግብ ለማደርስ ይቻል ዘንድ በማሰብ ከእዚህ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የሚሰራ  በተባበሩት መንግስታት ድርጅ ልዩ አማካሪ እና ጸሐፊ በማደረግ  አዳም ዳንግ የተባሉትን ግለሰብ መሾማቸውን ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጨምረው ገልጸዋል።

ካርዲናል አዩሶ ጉዊጉሶ እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት መሐመድ አብዱ አል-ሳላም በሁለቱም የእምነት ተቋማት ኃላፊነት የተሰጣቸው የኮሚቴ አባላት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነችስኮስ እና የግብፅ ታላቁ የአልዓዛር መስጊድ እና ዩኒቬርሲቲ ኢማም ከሆኑት ሼክ አህመድ አል ጣይብ እ.አ.አ በየካቲት 04/2019 ዓ.ም በአቡ ዳቢ የተፈረመው “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል አርእስት ይፋ የሆነው ሰነድ ላይ የተመለከቱትን ዓላማዎች ለማሳካት ይቻል ዘንድ እ.አ.አ በነሐሴ 20/2019 ዓ.ም ላይ የተቋቋመ ኮሚቴ የበላይ ኃላፊዎች መሆናቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግብፅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደርጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የአልዓዛር ታላቁ መስጊድ እና ዮኒቬርሲቲ ታላቁ ኢማም ከሆኑት አህመድ ሙሀመድ ኣል ታይብ ጋር በተገናኙበት ወቅት የሚከተለውን ንግግር አድረገው ነበር “የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደመሆናችን መጠን ማነኛውንም ዓይነት ቅድስናን የሚያጎድፉ ብጥብጦችን እና ግጭቶችን፣ የኋጢኣት ሁሉ መንስሄ የሆነውን የራስ ወዳድነት መንፈስን በማውገዝ እውነተኛ የሆኑ የውይይት መድረኮችን መክፈት ይኖርብናል። በሰው ልጆች ክብር እና ሰብአዊ መብት ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለማውገዝ፣ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ጥላቻዎችን በመፍጠር፣ እነዚህን ጥላቻዎች በሐይማኖትና በእግዚኣብሔር  ስም እውነተኛ እንደሆኑ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደርጉትን ጥረቶች በሙሉ ለማጋለጥ እና እነዚህን ጉዳዮች የእውነተኛው አምላክ ፍላጎቶች ሳይሆኑ ነገር ግን የጣዖት አምላክ ፍላጎቶች መሆናቸውን በማሳወቅ፣ የእውነተኛው እግዚኣብሔር ስም ቅዱስ፣ እርሱ የሰላም አምላክ፣ እግዚኣብሔር ሰላም መሆኑን በድፍረት መመስከር ይኖርብናል። ስለዚህ የተቀደሰ ነገር የሚባለው ሰላም ብቻ ነው፣ ስለሆነም በእግዚአብሔር ስም ምንም ዓይነት ግፍ፣ ብጥብጥ፣ ግጭት ሊፈጸም አይችልም፣ ምክንያቱም በእግዚኣብሔር ስም የሚፈጸሙ ግፎች ቅዱሱን የእግዚኣብሔር ስም ያረክሱታልና” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

 

06 December 2019, 13:05