ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮችን በቫቲካን በተቀበሉበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮችን በቫቲካን በተቀበሉበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የሰለጠነ የሰው ሃይል ማዘጋጀት የቤተክርስቲያን ተግባር ነው”።

አራተኛ ዙር ዓለም አቀፍ ጉባኤያቸውን ያካሄዱ የልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ቅዳሜ ኅዳር 27/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት የሰለጠነ የሰው ሃይል ማዘጋጀት የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታወቁ። በጉባኤው ላይ ለተገኙት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የቅድስት መንበር ተወካዮችን እና ለካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መሪዎች ቅዱስነታቸው ሰላምታቸውን አቅርበው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር በመምጣት ከመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን አንድነት በመግለጻቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በአራተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤን የተሳተፉት የልዩ ልዩ አገራት ካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መሪዎች፣ በቅድስት መንበር የልዩ ልዩ ሐዋርያዊ መማክርት ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች ተባብረው ልምዶቻቸውን ለመጋራት እና አንድነታቸውን ለመግለጽ መምጣታቸውን በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበው በዓለማችን ውስጥ የደሄዩት እና ከማሕበረሰብ መካከል የተገለሉትን ወደ ማሕበራዊ ሕይወት በመመለስ ዓለማችን የጋራ መኖሪያ ለማድረግ መፈለጋቸውን ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የጉባኤው ተካፋዮች ይህን ማድረግ የሚችሉት ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ አቅጣጫን በማጤን ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጉባኤውን የተካፈሉት በርካታ እንግዶች፣ ሰብዓዊ መብቶችን፣ ማሕበራዊ ሕይወትን፣ ባሕልን፣ ትምህርትን፣ እድገትን እና ማሕበራዊ ችግሮችን አስመልክተው በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ለመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ይህን መንገድ በመከተል፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ እንደሚገልጸው ቤተክርስቲያን በሕዝቦች መካከል መኖሯዋን በተግባር ትገልጻለች ብለው ቤተክርስቲያን በእነዚህ ማሕበራዊ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መሳተፏ የተጣለባትን የአገልግሎት አደራ በትጋት እንድታከናውን ያደርጋታል ብለዋል። በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ስለሚገባ ሕብረት አስመልክቶ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ያስቀመጣቸውን ገንቢ ሃሳቦች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለሰላም ግንባታ እና በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን አገሮች በማገዝ፣ ማሕበራዊ አገልግሎቶች ፍሬያማ ውጤት እንዲያስገኙ ለማስቻል በቂ ስልጠናዎችን በማስተባበር ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው እነዚህን አገልግሎቶች በብቃት ለማበርከት የጋራ ውይይቶችንም ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ አሁን ለምንገኝበት ዘመንም ጠቃሚ መንገዶችን የሚጠቁም መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከጉባኤው ሰነድ ጋር በተያያዘ ሦስት አበይት ነጥቦችን ጠቅሰው፣ የመጀመሪያው በማሕበራዊ ዕርዳታ አቅርቦት ተግባር ላይ የሚሰማራ የሰው ሃይል ማዘጋጀት፣ ሁለተኛ ማሕበራዊ የእርዳታ አገልግሎትን ለማበርከት የሚያግዙ መሣሪያዎችን ማሟላት፣ ሦስተኛ ተነሳሽነት ያላቸውን የቡድን ሥራ ማስተባበር እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

በማሕበራዊ ዕርዳታ አቅርቦት ተግባር ላይ የሚሰማራ የሰው ሃይል ዝግጅትን በማስመልከት፣ ከፍተኛ ማሕበራዊ ቀውስ ባጋጠመው ዓለማችን ውስጥ የሕይወት ምስክርነት ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቁ የጋራ ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የሕይወት ምስክርነት በእምነት ላይ እርግጠኛ መሆንን እና የእግዚአብሔር የእርዳታ ማስፈጸሚያ መሣሪያ መሆንን ይጠይቃል ብለው፣ ሁለተኛው አገልግሎትን በክርስቲያናዊ መንገድ ለማበርከት በሚያግዙ ሳይንሳዊ  ጥበብ ራስን ማዘጋጀት ነው ብለዋል። ይህን ማሟላት እንዲቻል የቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ በደንብ የሚያዘጋጅ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተምህሮን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው በማሕበራዊ የአገልግሎት እቅዶች ውስጥ በተግባር መተረጎም ያስፈልጋል ብለዋል። የዘመናችንን ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ወደሚፈለገው አቅጣጫ መምራት የሚችሉ ሰዎችን በትምህርት እና በስልጠና ማዘጋጀት ዛሬ ለቤተክርስቲያን ቀዳሚ የሥራ ድርሻ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ሰላምን ለማስከበር፣ ፍትህን ለማስፈን፣ በሕዝቦች መካከል መቻቻል እንዲኖር ለማድረግ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት በመመራት በጋራ ለምንኖርባት ምድራችን አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ጥበቃን ለማድረግ የሰለጠነ የሰው ሃይል ያስፈልጋል በማለት ዓለም አቀፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለው ከጊዜ ወደ ጊዜ በእውቀት በማደግ ክርስቲያናዊ ማንነትንም ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ማሕበራዊ አገልግሎትን በክርስቲያናዊ መንገድ ለማበርከት በሚያግዝ ሳይንሳዊ ጥበብ ራስን ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥበብ ማስፈለጉ የማይካድ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ እጥረት ሲያጋጥም ወደሚፈለገው ግብ ሳንደርስ እንቀራለን ብለዋል። ይህ ሲያጋጥም ተስፋን መቁረጥ እንደማያስፈልግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያን በቂ የሰው ሃይል ባልነበራትም ጊዜ ቢሆን ታላላቅ ሥራዎችን ለማበርከት ችላለች ብለዋል። እነዚያ ጥቂት ሰዎች ያላቸውን እውቀት በሙሉ የተጠቀሙ ቢሆንም ሃይል እና ጥበብ የእኛ ሳይሆን የእግዚአብሔር ነው ብለው ቤተክርስቲያን የምትመካበት ትልቁ ሃብት የሚገኘው በእግዚአብሔር ዘንድ ነው ብለው፣ ሐዋ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 9፡8 ላይ “ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል”፤ ማለቱን አስታውሰዋል።      

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ንግግራቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት ለጉባኤው ተካፋዮች እንደተናገሩት ለአገልግሎት ያላችውን ተነሳሽነት አንድ ላይ ማስተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው ከእምነታችን በምናገኘው ልምድ በኩል እግዚአብሔር በጸጋው የጠራን መሆናችንን በማወቅ በሕብረት የምናከናውነው ተግባር በግልጽ ሊታይ ይችላል ብለዋል። በአንድ ዓላማ ሥር ሆነን በሕብረት ስንጓዝ የቤተክርስቲያንን ማንነት እንገልጻለን ያሉት ቅዱስነታቸው የቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አገልግሎት ለማበርከት በሚወጠኑ እቅዶች ላይ ከልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር መተጋገዝ፣ ከቤተክርስቲያን አባቶች እና ከቅድስት መንበር ጋር መተባበር እንደሚያስፈል አስረድተዋል። የምንገኝበት ዘመን የጋራ ውይይቶችን እንድናካሂድ የሚጠይቀን በመሆኑ የውይይት ባሕሎችን በማሳደግ የእግዚአብሔርን ጥበባዊ እቅድ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፣ መላዋ ቤተክርስቲያን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሕይወት ምስክርነትን እና ፍሬያማ ሥራን ለዓለሙ ማሕበረሰብ በገሃድ እንዲያሳዩ ይጠይቃሉ ብለው የጉባኤው ተካፋዮች ተስፋን በመሰነቅ በድፍረት ወደ ፊት እንዲጓዙ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

07 December 2019, 15:28