ፈልግ

በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተ በርሃማነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተ በርሃማነት፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተካፋዮች መልዕክት አስተላለፉ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት እየተካሄደ ለሚገኝ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በላኩት መልእክት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለው ያለንን ዕድል በሙሉ መጠቀም እንደሚያስፈልግ በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በአየር ንብረት ላይ የደረሰውን ለውጥ ለማስተካከል በፓሪስ ከተማ  በመንግሥታቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማሳየቱን ገልጸዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ መንግሥታት ተወካዮች በጋራ ሆነው ሊወሰድ በሚገባው እርምጃ ላይ ተስማምተው የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከጉዳት መከላከል የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል። ከአራት ዓመት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ተግባራዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል ባለመፈጸማቸው አሁንም ዓለማችን በአደጋ ላይ የምትገኝ መሆኗን አስረድተዋል።

ግንዛቤን መስጠት ቢቀጥልም ተግባራዊነቱ ትንሽ ነው፣

እስካሁን የተደረጉት ጥናቶች በአየር ንብረት ላይ የደረሰውን ለውጥ ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎች በጣም ጥቂት መሆናቸውን ያመለክታል ያሉት ቅዱስነታቸው እስካሁን ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉትን የእድገት ሞዴሎች ላይ ለውጥ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም ከዚህም በተጨማሪ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስምምነት እና ሕብረት አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

የአመለካከት ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው፣

ፖለቲካዊ ፍላጎት እና ቅንነት መኖር አስፈላጊ ነው በማለት መልእክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል ተብሎ በሚደረጉ ኤኮኖሚያዊ ጥረቶችም ላይም አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ በጋራ በምንኖርባት ምድራችን ፍጥረታትን ከአደጋ ማዳን እና ለዛሬውም ሆነ ለነገው ትውልድ የተሻለ የመኖሪያ ሥፍራን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለወጣቶች ተስፋን መስጠት ያስፈልጋል፣

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ. ም. እየተካሄደ ለሚገኝ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ላይ የደረሱት ጥፋቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ ለአዲሱ ትውልድ በቂ ግንዛቤ እንዲሰጥ ጠይቀው፣ አዲሱ ትውልድ በመተባበር ለጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን ጥበቃን እና እንክብካቤብ በማድረግ የተሻለ ዓለምን መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረው የተባበሩት መንግሥታት ተባብረው በአየር ንብረት ላይ የታየውን ለውጥ ለማስተካከል የሚያደርጉት ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 December 2019, 16:44