ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጳጳሳዊ መኖሪያቸው ከሕጻናት ጋር የልደታቸውን ዕለት ሲያከብሩ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጳጳሳዊ መኖሪያቸው ከሕጻናት ጋር የልደታቸውን ዕለት ሲያከብሩ፣ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 83ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን አከበሩ።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 83ኛ ዓመት የልደት በዓል በማስመልከት ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች እየደረሱ መሆናቸውን እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን በጸሎት ማስታወሳቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ቸቺሊያ ሴፒያ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሳስ ወር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዩ መታሰቢያ ወር መሆኑን የገለጸው የቫቲካን ዜና አገልግሎት፣ ቅዱስነታቸው ያለፈው ታኅሳስ 3/2012 ዓ. ም. የክህነታቸውን 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓላቸውን አክብረው ማለፋቸውን አስታውሶ ቅዱስነታቸው የወንጌል አገልግሎታቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ገልጿል። መላው ዓለም በዛሬው ዕለት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ ጋር ሆኖ 83ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን አክብሮ መዋሉ ታውቋል። በሺዎች ከሚቆጠሩ ምዕመናን በኢሜይል አድራሻቸው በኩል የደስታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች የደረሷቸው መሆኑ ታውቋል። በዚህ አድራሻቸው አማካይነት ከሕጻናትም በርካታ መልዕክቶች የደረሷቸው መሆኑ ሲታወቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢስታግራም ማሕበራዊ ሚዲያ በኩል “ፍራንቺስኩስ” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምስል ሥር መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። ከሃያላን መንግሥታት መሪዎች፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛም የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት መድረሳቸው ታውቋል። ለልደት በዓላቸው ከደረሳቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ እና ትልቁ በእርሳቸው ጥያቄ መሠረት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ምዕመናን የቀረበላቸው ጸሎት ሲሆን ባለፈው ዓመትም በቅድስት መንበር ከካርዲናሎች መማክርት ጋር ሆነው ያቀረቡት የምስጋና እና የደስታ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መሆኑ ይታወሳል።

የመንፈስ ቅዱስ ዕቅድ ነው፣

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1969 ዓ. ም. የክህነት ማዕረግን የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የትውልድ አገራቸው በሆነው አርጀንቲና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1973 ዓ. ም. እርሳቸው ለሚገኙበት የኢየሱሳውያን ማሕበር የበላይ አለቃ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1992 ዓ. ም. በሚኖሩበት አገር አርጀንቲና ማዕረገ ጵጵስና የተቀበሉ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የካቲት 21/2001 ዓ. ም. ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እጅ የካርዲናልነትን ማዕረግ መቀበላቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትፍራንችስኮስ በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም. 266ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸው ሲታወስ በዚህም ከላቲን አሜሪካ የመጀመሪያው፣ ከሚገኙበት የኢየሱሳውያን ማኅበርም የመጀመሪያው እና በአሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስም ሲሰየሙም የመጀመሪያ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸው ታውቋል። የድኾች አባት በመባል የሚታወቀው እና የፍራንችስካዊያን ማሕበር መስራች የነበረው ቅዱስ ፍራንችስኮስ፣ በሕይወቱ ዘመን ለድኾች ባሳየው ትህትና፣ ክብር፣ ፍቅር እና ልገሳ የተማረኩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርሳቸውም የቅዱስ ፍራንችስኮስን አብነት በመከተል በጵጵስና ዘመናቸው ለድኾች፣ ለስደተኞች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ እኩልነት እና ፍታሃዊነት እንዲኖር በማሰብ የቅዱስ ፍራንችስኮስን ስም የጵጵስናቸው ዘመን መጠሪያ ስማቸው እንዲሆን መምረጣቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው በተመረጡ ባለፉት 7 ዓመታት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ዘመናቸው በተለይ ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ የሆነ ተግባሯን አጠናክራ እንድትቀጥል እና ለሁሉም የሰው ልጆች በቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ደስታ እንድትመሰክር፣ በማንኛውም የቅዱስ ወንጌል የማብሰር ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ በመፍቀድ ማከናውን እንደሚገባ አበክረው መንገራቸው እና አሁንም ቤተክርስቲያን በዚሁ መንገድ እንድትቀጥል ማሳሰባቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 December 2019, 16:24