ፈልግ

“በቤተክርስቲያን ሕይወት ቅዱስ ቁርባን ቀዳሚ ሥፍራን ይዞ ይገኛል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ታኅሳስ 5/2012 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ካቀረቡ በኋላ በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በመቀጠልም በሥፍራው ለተገኙት በሙሉ፣ ከሮም ከተማ፣ በጣሊያን ከሚገኙት የተለያዩ ቁምስናዎች እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች ለመጡት ምዕምናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሀገር ጎብኚዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በርካታ ወጣቶች እና ሕጻናት ሰላምታቸውን አቅርበው የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃነ ልደት የሚያስታውሱ መንፈሳዊ ምስሎችን ለማስተዋሻ ወደ የቤታቸው ወስደው እንዲያስቀምጡ  አደራ ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት የሚያስታውሱ ምስሎችን ባርከዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ሕያው ቅዱስ ወንጌል ነው ያኡት ቅዱስነታቸው የብርሃነ ልደቱን ታሪክ በምናስታውስበት ወቅት በኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና መማረክ እንደሚያስፈልግ፣ እያንዳንዳችንን በግል ሊያገኘን ስጋን ለብሶ ወደ ዓለም መምጣቱን ማስታወስ እንደሚገባ አስረድተው፣ እርሱ እኛን እንደወደደን እኛም እርሱን ከልባችን ልንወደው ይገባል ብለዋል።

ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከመስከረም 13-20/2020 ዓ. ም. በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት 52ኛው ዓለም አቅፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ የሚካሄድ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ከዚህ በፊትም በዚህች አገር ከአንድ የቅዱስ ቁርባን ዓለም አቀፍ ጉባኤ መከናወናወኑ ገልጸው፣ ቅዱስ ቁርባን በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ማዕከላዊ ቦታን ይዞ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በመጽሐፈ መዝሙር ምዕ. 87፤7 ላይ “የሚያዜሙም መሣሪያ የሚጫወቱም፣ ምንጩ ሁሉ በአንቺ ውስጥ ይገኛል” ተብሎ የተጻፈውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በክርስቲያን ማሕበረሰብ መካከል ለውጥን እንደሚያስገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበት ተመኝተው በሥፍራው የተገኙት ወጣቶች እና ሕጻናት የሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ወደ ቤታቸው በመውሰድ የብርሃነ ልደቱን በዓል በደስታ እንዲጠባበቁ አደራ ብለው በአደባባይ የተገኙ ምዕመናን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

16 December 2019, 18:19