ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዩክሬን ሰላም እና ፍትህ እንዲሰፍን ተመኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትናንት ኅዳር 28/2012 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ካቀረቡ በኋላ በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው ከጸሎታቸው በመቀጠል ንግግር ማድረጋቸው ሲታወቅ በንግግራቸውም በላቲን አሜሪካ አገር በሆነች ጓቴማላ ውስጥ፣ እውቴናንጎ በተባለ አካባቢ የሚገኝ የክርስቲያን ትምህርት ቤት ወንድሞች ማሕበር አባል የሆነው የወንድም ያዕቆብ ሚሌር ብጽዕና መታወጁን አብስረዋል። ወጣቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1982 ዓ. ም. በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በክርስትና እምነት ጠላቶች እጀ የተገደለ መሆኑን አስታውቀዋል። በማስተማር አገልግሎቱ የሚታወቅ ወንድም ያዕቆብ በጓቴማላ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ ሕይወቱን በመሰዋት ለሰማዕትነት የበቃው ሕዝቡን በፍቅር እና በቆራጥነት በማገልገል እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው የእርሱ ሰማዕትነት በጓቴማላ ውስጥ ፍትህ፣ ሰላም እና አንድነት እንዲወርድ ትልቅ አስተዋጽዖን ማድረጉን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ዛሬ ህዳር 29/2012 ዓ. ም. በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ የዩክሬን፣ የሩሲያ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን ቻንስሌር ተገናኘተው በዩክሬን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የእርስ በእርስ ጦርነት አብቅቶ ሰላም በሚወርድበት መንገድ ላይ የሚወያዩ መሆናቸውን ገልጸው በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ ጸሎታቸው የሚያግዙ መሆኑን ገልጸው ምዕመናኑም በጸሎት እንድዲተባበሩ አደራ ብለዋል። በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ የተጀመረው የጋራ ውይይትም መልካም የመፍትሄ ሃሳቦችን ይዞ እንደሚወጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው በአካባቢው ሕዝብ መካከል ሰላም እና ፍትህ እንዲወርድ በማለት መልካሙን ሁሉ ተመኝተውላቸዋል።

በዕለቱ የተከበረውን ጽንሰታ ማርያም ክብረ በዓልን በማስታወስ ባሰሙት ንግግርም በጣሊያን በሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች የተዋቀሩ ካቶሊካዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ብርታትን በማግኘት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራስን በእውቀት በማሳደግ ፍሬያማ ውጤት እንዲያሳዩ እና በአገልግሎታቸው መልካም ምስክርነትን የሚያበረክቱ እንዲሆኑ በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ከጣሊያን ውስጥ የተለያዩ ከተሞች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ ለወጣት ማሕበራት አባላት፣ ሀገር ጎብኝዎች እና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ “እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ” አደራ ብለው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት መሰናበታቸውን ከሥፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 December 2019, 17:18