ፈልግ

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሳንዘነጋ ለኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ውስጥ ሥፍራን እናዘጋጅ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 5/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ታኅሳስ 5/2012 ዓ. ም. በተጀመረው ሦስተኛ የስብከተ ገና እሑድ ላይ ባቀረቡት ስብከታቸው ምዕመናን በሙሉ በተለያዩ ቁሳዊ ነገሮች ሳይታለሉ ደስታውን ሊጋራን የሚመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ለመቀበል መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕይወት ለውጥ እና ድነት፣

በዕለቱ ከተነበቡት ንባባት መካከል ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 35 በተወሰደው የመጀመሪያ ምንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን ጥርጣሬ እና ተስፋ መቁረጥ ትተው አዲስ ሕይወት የሚሰጥ የእግዚአብሔር ምህረት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።     

ዘወትር እሑድ እንደሚያደርጉት ሁሉ ቅዱስነታቸው ሳምንታዊውን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በቅዱስ አደባባይ ላይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ከማድረሳቸው በፊት የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ታኅሳስ 5/2012 ዓ. ም. የዋለው የስብከተ ገና ሦስተኛ እሑድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ ወደ መካከላችን መምጣቱ ለታላቅ ደስታ የሚጋብዘን መሆኑን ገልጸዋል። በሕይወታችን ለውጥ እንድናመጣ ተጠርተናል በማለት ስብከታቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሠረታዊ የሕይወት ለውጥ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ለአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ የስብከት አገልግሎት በር ከፍቶላቸዋል ብለዋል። ለአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ እንደተገለጸለት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ትሑት እና መሐሪ ፊቱ ለእኛም ሊገለጥልን ያስፈልጋል ብለዋል።

የስብከተ ገና ሰሞን የጸጋ ወቅት ነው፣

የስብከተ ገና ሰሞን ጸጋን የምናገኝበት ወቅት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ የጸጋ ወቅት፣ ማመን ብቻውን እንደማይበቃ ነገር ግን እምነታችንን በየቀኑ ሊያጋጥሙት ከሚችሉ የተለያዩ እንቅፋቶች ነጻ እንድናደርግ ያሳስበናል ብለዋል። በመሆኑም ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ስንዘጋጅ የእርሱ መምጣጥ በታሪክ ብቻ የሚነገር ሳይሆን በልባችን ውስጥ በማሰላሰል የሚያቀርብልንን ምርጫ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ የተስተናገደበትን ሥፍራ አስመልክተው በቅርቡ የጻፉትን ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በከብቶች ግርግም ውስጥ የተኛው ሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በችግር እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይመስላል ብለው የተለያዩ ችግሮችን ዘወትር የሚጋፈጡ ሰዎች እግዚአብሔር በመካከላችን መገኘቱን ከማንም በላይ እንዲያውቁ ጥበብ ተሰጥቶአቸዋል ብለዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል ባጠቃለሉበት ወቅት፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ስንቃረብ በውጫዊ ወይም ቁሳዊ ነገሮች ሳንታለል፣ ዘለዓለማዊ ደስታውን የሰጠን እና አሁንም ደግሞ ሊሰጠን፣ ከህመማችንም ሊፈውሰን እና የደስታው ተካፋዮች ሊያደርገን የሚመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ውስጥ ተቀብለን የምናስተናግድበትን ሥፍራ ማዘጋጀት እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን በማለት በጸሎታቸው ተማጽነው የዕለቱን ስብከታቸውን ደምድመዋል።        

16 December 2019, 18:14