ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” ከሚያጠና ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካፋዮች ጋር፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” ከሚያጠና ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካፋዮች ጋር፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን በነጻነት ወደ ፊት መጓዝ አለባት ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ህዳር 30/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው “የወንጌል ደስታ አብሳሪዎች” ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር፣ ነጻ እና በአገልጋይነት ደረጃ የምትገኝ ቤተክርስቲያን የምታስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት  ከስድስት ዓመት በፊት እርሳቸው ይፋ ባደረጉት “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” በተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ ለመወያየት ከመላው ዓለም ለመጡት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም የምዕመናን ወገን መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር “ከወንጌል የሚፈልቅ ደስታ የሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲገናኙ ብቻ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለተገኙት በሙሉ ቅዱስነታቸው ባሰሙት ንግግር ተመቻችታ የተቀመጠች ሳትሆን የእግዚአብሔርን ሕዝብ በትህትና ለማገልገል የተዘጋጀች ነጻ ቤተክርስቲያን ታስፈልገናለች ብለዋል።    

የወንጌልን መልካም ዜና ማብሰር ቀዳሚ አገልግሎት ነው፣

“የወንጌል መልካም ዜና ማብሰር የምንችለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲንገናኝ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወንጌልን የማብሰር አስፈላጊነት እና ጥሪ በአእምሮአችን ውስጥ በድንገት ይመጣል ብለዋል። የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮ አመጣጡ በዚህ መንገድ ነው በማለት ያስረዱት ቅዱስነታቸው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ዕለት ጠዋት የሆነውን ታሪክ አስታውሰ፣ መቅደላዊት ማርያም ለሐዋርያት መልካም ዜናን ያበሰረችው ከሞት የተነሳውን ሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘች በኋላ ነው ብለዋል። ዛሬ ላይ የብዙ ሰዎች ልምድ ከመቅደላዊት ማርያም ልምድ የተለየ እንዳይደለ አስረድተው በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የእውነተኛ እና ዘለዓለማዊ እግዚአብሔር ፍቅር ይገኛል ብለዋል። የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፍቅር ዘወትር መሻት ያስፈልጋል ብለው ፍቅሩ በዘላቂነት በልባችን ውስጥ ካለ “ከግድ የለሽነት ስሜት ወጥተን ለሎችን ማገልገል እንጀምራለን፣ በቁሳዊ ነገርም አንታለልም” ብለው “የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር ቆርጠው የተነሱት በሙሉ ነፍሳትን ለማዳን በልው በየጎዳናው ላይ እና በየመንደሩ ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል።

አዲስ ጎዳናን መጓዝ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኤውን ለተካፈሉት በሙሉ ባሰሙት ንግግር ስህተትን መሥራት መፍራት የለብንም ብለው ከስህተት መንገድም ወጥተን በአዲስ ጎዳና ላይ መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ድህነቶቻችን እንቅፋት ሊሆኑብን አይገባም ብለው ይልቅስ የእግዚአብሔር ፍቅራዊ ጸጋ በድካማችን ላይ እንዲገለጥ ያደርጋሉ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” በተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ ለመወያየት ከመላው ዓለም ለመጡት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ምዕመናን ያደረጉትን ንግግር ከመፈጸማቸው በፊት እንደተናገሩት ስቃይ መከራ እና ሞት የደረሰባቸው የጥንት ክርስቲያኖች ምሳሌዎቻችን ሆነው ሊመሩን ይገባል ብለዋል። ነገሮች በትክክለኛው መንገድ ሳይሄዱ ሲቀር እና አለመግባባት ሲፈጠር ማዘን የለብንም ብለው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢራዊ እውቀት ሲፈተሹ ከምንም የሚቆጠሩ አይደሉም ብለዋል።   

ሁሉም ነገር በተሳሳተ መንገድ እንደሚሄድ በማሰብ ራሳቸውን ለሽንፈት አሳልፈው እንደሚሰጡ ሰዎች መሆን የለብንም ብለው “ሕይወታችንን በእግዚአብሔር ዘንድ በማኖር የመልካም ታሪክ ባለቤት ለሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ አደራ እንስጥ” በማለት ምክራቸውን አካፍለዋል።             

30 November 2019, 18:17