ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ድሆች ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስዱ መንገዶች ናቸው” አሉ!

“የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም” (መዝ 9፡18) በሚል መሪ ቃል ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በኅዳር 07/2012 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ በእርሳቸው መሪነት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ  ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ወደ መንግሥተ ሰማይ የምናደርገውን ጉዞ የሚያመቻቹት ድሆች ስለሆኑ የድሆችን ድምጽ እንስማ” ማለታቸው ተገልጹዋል። ድሆች የእኛን እገዛ ፈልገው የሚያሰሙትን ጩኸት ማዳመጥ ከራስ ወዳድ ስሜት እንድንወጣ ያደርገናል ያሉት ቅዱስነታቸው ካቶሊክ መሆን ወይም የክርስትና እምነት መለያ የሆነውን ክርስቶስን አምናለሁ ማለት በራሱ በቂ አይደለም ፣ ግብዝነት ባልታከለበት መልኩ ምጽዋዕት ለመስጠት መነሳሳት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሦስተኛውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በማስመልከት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጦሮስ ባዚሊካ ይህንን ቀን ለማክበር በርካታ ምዕመናን ተገኝተው እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “ድሆች የቤተ-ክርስቲያን ውድ ሀብት፣ በእግዚአብሔር ተወዳጅ፣ የሰማይ ደጃፍ” ናቸው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ድሆች በጀርባዎቻቸው ላይ የተለያዩ የህይወት ታሪኮችን የተሸከሙ እግዚኣብሔር ባዘጋጀው ማዕድ ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ የተጋበዙ መሆናቸውን ጨምረው ገለጸዋል።

በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 21፡5-19 ላይ ተወስዶ በተነበበበው እና በዘመኑ መጨረሻ ላይ ስለሚሆኑ ምልክቶች በሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከታቸው “ከደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ በውብ ድንጋዮችና በስእለት ስጦታዎች እንዳማረ ሲነጋገሩ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ይህ የምታዩት ሁሉ ሳይፈርስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደ ተካበ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል” ብሎ ኢየሱስ በሰጠው ምላሽ ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ኢየሱስ ታላቅ በሆነችው የኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ እንደ ሚመጣ መግለጹን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ምዕመናን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መመልከት እንደ ሚገባቸው ገልጸው “ከእለት ወደ እለት እርግጠኛ የመሆን መንፈስ እየተሸረሸረ በመጣባት ዓለማችን ጌታ ይበልጡኑ እርግጠኞች እንዳንሆን ለምን ፈለገ?” በማለት ጥያቄ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን መልሱም አንድ እና አንድ ብቻ ነው በእርግጠኝነት እውነተኛ እና ትክክለኛ ለዘለዓለም የሚኖረው ነገር ምን መሆኑን እንድንማር ስለፈለገ ነው” ብለዋል። አሁን ይሁን ወይም  ዘግይተው እየተፈጠሩ የሚገኙት ክስተቶች፣ ጦርነቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እየተከሰቱ የሚገኙ ነገሮች ምንም እንኳን ግዙፍ ወይም ተጨባጭ ክስተቶች ቢሆኑም ከምድር ገጽ እንደ ሚጠፉ የገለጹት ቅዱስነታቸው ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖረው ግን እግዚኣብሔር ብቻ ነው ብለዋል።

እግዚኣብሔር አይቸኩልም

ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለመረዳት እና ለመማር በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ሁለት ፈተናዎችን መመልከት ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው በቀዳሚነት የሚጠቀሰው መቸኮል የሚለው ነው ብለዋል። ይህን በተመለከተ ቅዱነታቸው የሚከተለውን ብለዋል. . .

ኢየሱስ “መጨረሻው ሰዓት ተቃርቡዋል” እያሉ ከሚናገሩ ሰዎች ጀርባ መሄድ እንደ ሌለብን ይናገራል። በሌላ አገላለጽ ፍርሃትን የሚያስፋፉ እና በአሁኑ ጊዜ እና የወደፊቱን ጊዜ በማንሳት ፍርሃት የሚነዙ ሰዎችን መከተል የለባችሁም ማለት ነው። ምክንያቱም ፍርሃት ልብንና አእምሮን ያበላሻል። ሆኖም ፣ ሁሉንም ነገር በችኮላ ለማወቅ ያለን ፍላጎት፣ አዳዲስ አስደንጋጭ ወይም ቀልብን የሚስቡ አሰቃቂ ዜናዎችን ለመስማት ጮክ ብለው እና በከፍተኛ ቁጣ በመጮኽ የሚናገሩትን ሰዎች ለማዳመጥ “ዛሬ የመጨረሻው ቀን ነው” በማለት ሰዎችን የሚያጣድፉ ሰዎች፣ ፍጠን አሁን ሁሉንም አከናውን የሚሉት ጩኸቶች በሙሉ ከእግዚአብሔር የመጡ አይደሉም።

ድሆች ምቾት ይነሱናል

ሁሉንም ነገር በፍጥነት አከናውኑ በሚለው ጩኸት ተወስደን ለእግዚኣብሔር እና በአጠጋባችን ላለው ለወንድማችን ጊዜ አንስጠም በማለት ስብከታቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሁሉንም ነገር በፍጥነት አከናውኑ ለሚለው በሽታ ፈውስ የሚሆን መድኃኒት መኖሩን ገልጸው ይህም የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነው ጽናት በመባል የሚታወቀው ጸጋ ነው ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . ይህ ጉዳይ ዛሬ እውን የሆነ ነገር ነው! ለመሮጥ ያለን ፍላጎት፣ ሁሉንም ነገር በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ለማዋል በምናደርገው ሩጫ ወደ ኋላ የሚቀሩ ሰዎች ይበሳጩናል። እናም የእዚህ ዓይነቱ ሰው ከንቱ ነው ተብሎ ይፈረጃል፣ ብዙ አዛውንቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ድሃ የሆኑ ሰዎች ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ተደርገው ይታያሉ። ወደ ኋላ የቀሩ የድሆች ጉዳይ ሳያሳስበን ወደ ፊት በፍጥነት ለመሮጥ እንፈልጋለን፣ በእዚህ የተነሳ እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎች ሃብታሞች ሲሆኑ በተቃራኒው ወደ ኋላ የቀሩ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ለድህነት ይዳረጋሉ። የጉዞ ርቀት እየጨመረ በሚሄድበት ወቅት በእዚያው ልክ ድሆች ወደ ኋላ ይቀራሉ። ለእያንዳንዳችን ለእኛ የቤተክርስቲያን አባል ለሆንን ሁላችን በመልካም ነገር ላይ ብቻ ጸንተን እንድንኖር እና በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማስታወስ እንችል ዘንድ እንዲረዳን ጸጋውን እንጠይቅ።

ራስን ማዕከል የማድረግ ፈተና

ሊወገድ የሚገባው ሁለተኛው ማታለያ “እኔ ብቻ” የሚለው የራስ ወዳድነት፣ ራሳችንን ብቻ እንደ ማጣቀሻ አድርጎ መውሰድ፣ እኔ “ጎበዝ ነኝ” ብን ለራሳችን ከፍተኛ ግምት መስጠት የሚለው ሁለተኛው የሰው ልጆች ፈተና መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው የክርስትና እምነት እንደ ሚያስጠነቅቀን የእዚህ ዓይነቱ “እኔ ብቻ” የሚለው ስሜት የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት እንዳንሆን እንቅፋት እንደ ሚሆን ገልጸው  “እኔ ብቻ” የሚለው ስሜት ራሳችንን ብቻ የሚገልጽ ስሜት እንጂ የፍቅርን ጥሪ የሚከተል መስመር አይደለም ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል።

“ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ” ይላል ጌታ እነርሱን ግን መከተል የለባችሁም፣ “ክርስቲያን” ወይም “ካቶሊክ” መሆን በራሱ የኢየሱስ ለመሆን በቂ አይደለም። ኢየሱስ የሚጠቀምበትን የፍቅር ቋንቋ መናገር አለብን። ስለራሱ መልካም ነገር ሳይሆን ስለሰዎች መልካም ነገር የሚናገር ሰው እርሱ የኢየሱስን የፍቅር ቋንቋ ይከተላል። መልካም ነገር በምናደርግበት ወቅት “እኔ ነኝ ይህንን ያደረኩት” ብለን በግብዝነት የምንናገርባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ፣ በሌሎች ዘንድ ጎበዝ ለመባል በማሰብ መልካም ነገሮችን የሰራንባቸው ወቅቶች ስንት ናቸው? “መልካም ነገር የማደርገው ሰዎች በተራቸው መልካም ነገር እንዲያደርጉልኝ በማሰብ ነው” ብለን በእዚህ መንፈስ ሂሳባችንን ለማወራረድ የሰራንባቸው ጊዜያት ስንት ናቸው? “እኔ ብቻ” የሚለው ቋንቋ የሚናገረው በእዚሁ መልክ ብቻ ነው።

ልግስና ግብዝነት መሆን የለበትም

እያንዳንዳችን በድሆች ፊት ማሳየት ስለሚገባን ባሕሪይ በማንሳት ስብከታቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔር ቃል በግብዝነት ወደ አልተሞል የልግስና ተግባር እንደ ሚገፋፋ የገለጹት ቅዱስነታቸው የልግስና ተግባር የምንፈጽመው ከሌሎች መልካም ምላሽ ወይም ሽልማት በመጠበቅ መሆን እንደ ሌለበት ጨምረው ገለጸዋል።

በእውነቱ ድሆች በእግዚአብሔር ፊት ውድ የሆኑ ሐብቶች ናቸው፣ ምክንያቱም እኔ ብቻ የሚለውን ቋንቋ መናገር ስለማይችሉ፣ ሁልጊዜ የሌሎች ድጋፍ ስለሚያሻቸው፣ ቅዱስ ወንጌል ድሆች ወደ እግዚኣብሔር እኛን የሚያደርሱ መንገዶች መሆናቸውን ያስታውሰናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 November 2019, 15:32