ፈልግ

2ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ከድሆች ጋር ማዕድ በተካፈሉበት ወቅት 2ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ከድሆች ጋር ማዕድ በተካፈሉበት ወቅት  

ር.ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮስ 3ኛው የዓለም የድሆች ቀን ያስተላለፉት መልእክት

1ኛው ዓለም አቀፍ የድኾች ቀን በሕዳር 08/2009 ዓ.ም  በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “አባታችን ሆይ!” የሚለው ጸሎት የድኾች ጸሎት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው እኛ ሁላችን አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት “አባታችን ሆይ” በማለት ሁላችንም የአንዱ የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን  በመግለጽ አባት ለልጁ እንደ ሚያደርገው ሁሉ “‘የዕለት እንጀራችንን ስጠን’ ብለን እንደ ምንጠይቀው እና እርሱም እንደ ሚሰጠን ሁሉ እኛም በየጎረቤቶቻችን እና በእየአከባቢዎቻችን የሚገኙ ርዳታ ፈላጊ ድኾች  የእኛን እገዛ ፈልገው በሚማጸኑን ወቅት ሁሉ ካለን ማካፈል ይገባናል፣ በቃላት ብቻ ሳይሆን እምነታችንን በተግባር መግለጽ ይኖርብናል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊክ ከተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ በመቀጠል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለበርካታ ድሆች እና የእኔ ቢጤዎች የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በሮም ከተማ እና በአከባቢው የሚገኙ የምግብ ቤቶች ሳይቀር በገዛ ፈቃዳቸው ለድሆች የነጻ የምሳ ግብዣ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 09/2010 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ይሆን ዘንድ የመረጡት መሪ ቃል “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም  ሰማው” (መዝሙር 34፡7) የተሰኘው መሪ ቃል እንደ ሆነ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም  ሰማው” (መዝሙር 34፡7)፣ “እነዚህ የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ጸሐፊ  ቃላት የእኛ ቃላት ሊሆኑ የሚችሉት እኛ ራሳችን በተለምዶ ስማቸው “ድሆች" ተብለው የተፈረጁ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያጋጠሟቸውን የተለያዩ መከራዎች እና መገለሎች መቋቋም  እንዲችሉ ስናደርግ ብቻ ነው።  የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ የሚናገረው ስለመከራ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የሚናገረው በተቃራኒው ነው። ዘማሪው ዳዊት ቀጥተኛ የሆነ የድህነት ተመክሮ የነበረው ሰው ሲሆን ይህንን የድህነት ተመክሮ እግዚኣብሔርን ማመሰገኛ ወደ ሆነ መዝሙር ይቀይረዋል። ይህ መዝሙር ዛሬ ብዙ ዓይነት ድህነት ተጠናውቶን ለምንገኝ ለእኛ እውነተኛ ድሃ ማን እንደሆነ ለመረዳት እና የእነሱን ጩኸት ለመስማት እና የእነሱን ፍላጎት ለማወቅ እንደ ተጠራን እንድንገነዘብ እድሉን ይሰጠናል” ማለታቸው ይታወሳል።

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በኅዳር 07/2012 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን ለእዚህ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ቅድመ ዝግጅት ይደረግበት ዘንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 06/2011 ዓ.ም “የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም” (መዝ 9፡19) በሚል መሪ ቃል መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ይህ አለም አቀፍ የድሆች ቀን በኅዳር 07/2012 ዓ.ም ይከበራል። ለእዚህ 3ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ይሆን ዘንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 06/2011 ዓ.ም ያስተላለፉንት መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም” (መዝ 9፡18)።

1.     “የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም” (መዝ 9፡18)። እነዚህ የመዝሙረ ዳዊት ቃላት ወቅታዊ ናቸው። እነዚህ ቃላት ድሆች በልባቸው ውስጥ ከሁሉም ነገር በላይ የሆነው እምነት እንዳላቸው ግልጽ አድርጎ በማሳየት የፍትሕ መዛባት፣ ስቃዮች እና የኑሮ አለመረጋጋት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ያጡትን ተስፋ ወደ ነበረበት መመለስ የሚችል አቅም እንዳላቸው ያሳያል።

ይህ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የችግረኞችን ሁኔታ እና የሚያስጨቁኗቸውን እብሪተኞች ሁኔታ ይገልፃል። ፍትህ እንዲሰፍን እና ክፉን ለማሸነፍ የእግዚአብሔር ፍርድ ይመጣ ዘንድ ይማጸናል። በእዚ በመዝሙረ ዳዊት ቃል በጣም የቆዩ ጥያቄዎችን በድጋሚ ለማንሳት እንገደዳለን። አምላክ ይህን ልዩነት እንዴት ይታገሣል? ድሆችን በመከራቸው መጥቶ ሳያግዛቸው ችግረኞች እንዲዋረዱ እንዴት ያደርጋል? በተለይም ድሆች እየተሰቃዩ ባለበት ሁኔታ ላይ ጨቋኞች እንዲበለፅጉ ለምን ፈቀደ?

ይህ የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ክፍል የተጻፈው የተደላደለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በነበረበት ወቅት እና እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ልዩነት በነበረበት ወቅት የተጻፈ ነው። እምብዛም የማይታየው ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድሆችን እንዲፈጠሩ ያደረገ ሲሆን እነዚህም እጅግ በጣም ደካማ በሆኑ ሰዎች ከሚያገኙት ሐብት ጋር በንጽጽር ሲታይ ጥቂት የሚባሉ ሰዎች የሚያገኙት ሐብት ይበልጡኑ የተጋነነ ነው። የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊም ሁኔታውን በመመልከት ስዕላዊ በሆነ መልኩ ስለሁኔታው እውነትነት ተጨባጭ በሆነ መልኩ ያቀረባል።

ይህ ወቅት እብሪተኞችና ፈርሃ እግዚኣብሔር የሌላቸው ሰዎች ድሆችን ለመውረር እና ያላቸውን ጥቂት የሆነ ንብረት እንኳ ሳይቀር ለመንጠቅ እና ወደ ባርነት ቀንበር ውስጥ ሊከቱዋቸው ኣንደ ሚፈልጉ እናያለን። ዛሬ ያለው ሁኔታ ከዚህ እንብዛም የተለየ አይደለም። የኢኮኖሚ ቀውሱ አብዛኛዎቹ ሰዎች ተመጣጣኝ ባለሆነ ሁኔታ ብዙ ሀብት ከማከማቸት አላገዳቸውም፣ በተቃራኒው ደግሞ በከተሞቻችን አውራ ጎዳናዎች ላይ በርካታ ሰዎች በየዕለቱ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ፍለጋ ዚባዝኑ እና ብዙዎቹ ድሆች ደግሞ ለጉልበት ብዝበዝ እና ለውርደት ተዳርገዋል። በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ውስጥ “ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም” (ራእይ 3፡9) ይለናል። ዘመናት ያልፋሉ፣ ነገር ግን ከታሪክ ምንም እንድላተማርን በማስመሰል በሐብታም እና በድሃ መካከል ያለው ልዩነት እንዲሁ እየሰፋ በቋሚነት ቀጥሉዋል። በእዚህ አግባብ ስንመለከተው የመዝሙረ ዳዊት ቃላት በእዚያን ባለፈው ጊዜ የነበሩ ቃላት ብቻ ሳይሆኑ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን እየተከሰተ የሚገኝ እውነታ ነው፣ በእዚህም የተነሳ በእዝጊኣብሔር ፍርድ ፊት ጉዳዩ ይቀርባል።

2.     ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና ሕጻናት በአዲስ መልክ በተዘረጉ በርካታ ዓይነት የባርነት ቀንበር ውስጥ እንደ ሚገኙ አምነን መቀበል መቻል ይኖርብናል።

እናት አገራቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰደዱ የተገደዱ ቤተሰቦቻችን፣ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕጻናትን ወይም ደግሞ ጭካኔ በተሞላው መንፈስ ጉልበታቸውን ለመበዝበዝ ከወላጆቻቸው የተነጠቁ  ሕጻናትን፣ ሙያዊ ክህሎቶቻቸውን በተግባር ለማዋል የሚፈልጉ ነገር ግን የአጭር ጊዜ ትርፍ በሚፈልገው የኢኮኖሚ መዋቅር የተነሳ ይህንን ሙያቸውን እውን ለማደረግ ያልቻሉ ወጣቶችን፣ የተለያዩ የሃይል ድርጊቶች ሰለባ ወይም ተጎጂዎች የሆኑ፣ አስገዳጅ በሆነ መልኩ ከዝሙት አዳሪነት እስከ የአደንዛዢ እጽ አዘዋዋሪነት በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ዛሬም ቢሆን በእየለቱ እንመለከታለን። በተደጋጋሚ ጊዜ ለፖለቲካዊ ንግድ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙትን፣ ብዙን ጊዜ ለጥቂት ሰዎች የገል ጥቅም ማስገኛ እየዋሉ የሚገኙትን እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሁኔታ አጋርነት እና እኩልነት የተነፈጉ ስንቶቹ ናቸው? ኑሮዋቸው የተዛባ እና በየከተማዋችን ጎዳናዎች ላይ ፈሰው የሚገኙ ቤት አልባ የሆኑ ሰዎች ስንት ናቸው?

የቆሻሻ መጣያ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተትረፈረፈ ኑሮ ያላቸው ሰዎች የጣሉትን ለኖሮዋቸው የሚጠቅማቸውን ወይም የሚለበስ ነገር ፈልጋ በእየለቱ የሚኳትኑ ድሆች ስንት ናቸው! በእዚህ አኳኋን እነሱ እራሳቸው የሰዎች የቆሻሻ መጣያ እቃዎች አካል ይሆናሉ፣ በዚህ ቅሌት ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች ጥቂት የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማቸው ድሆችን እንደ ጉድፍ ይመለከታሉ። ብዙውን ጊዜ ድሆች በማኅበረሰቡ ላይ የተመሰረቱ ጥገኛ ህዋሳት ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን ለድህነታቸው ይቅርታ አይደረግላቸውም። ፍርድ ሁል ጊዜም ቢሆን የሚሰጠው በእነርሱ ዙሪያ ነው። እነሱ ድሆች እንዲፈሩ ወይም ተስፋ እንዲቆርጡ አይፈቀድላቸውም; እነሱ ድሆች ስለሆኑ ብቻ እንደ ማፈሪያ ወይም እንደ ጥቅም የለሽ ነገር ተደርገው ይቆጠራሉ።

ይባስ ብሎ ደግሞ እጅግ የከፋ የድህነት ዋሻ ጫፍ አይታያቸውም። እነርሱን ድሆችን ከተቀረው ማኅበረሰብ የተገለሉ ለማደረግ በማሰብ የስነ-ሕንጻ ሙያዎችን በመጠቀም ለድሆች ካለው ጥላቻ የተነሳ ድሆን የሚያገል የግንባታ ሥራ የሚሰራበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ድሆች ከከተማችን ከአንዱ ጫፍ ተነስተው ወደ ሌላው ጫፍ ድረስ በመሄድ ሥራ፣ ቤት እና ፍቅር በመፈለግ በመኳተን ላይ ይገኛሉ። በእዚህ ሂደት ውስጥ ለእነርሱ ያላቸው ትልቁ ሐብት የጸሐይ ብርሃን ብቻ ሲሆን ይህንን እንኳን በሚገባ ማግኘት እንዳይችሉ ጥቃት እና በደል ይደርስባቸዋል። ወቅታዊ የሆኑ ፍራፍሬዎችን ለመሰብሰብ ንዳድ በሆነ ብርቱ ፀሐይ ሥር ሆነው ለበርካታ ሰዓታት በጣም ዝቅተኛ በሆነ ክፍያ ይህንን ከባድ ሥራ እንዲሰሩ ይገደዳሉ። ሥራቸው ለአደጋ የተጋለጠ እና በተጨማሪም ኢሰብአዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ የገደዳሉ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንደ ልባቸው እንዳይገናኙ ይከለከላሉ። የሥራ አጥነት ካሳ፣ ጥቅማጥቅሞች አይከፈላቸውም ወይም ሲታመሙ የሕክምና ዋስታና እንኳን አይሰጣቸውም።

ዘማሪው ዳዊት ድሆችን የሚዘርፉ ሀብታሞችን አሰቃቂ እውነታዎችን “ በስውር ያደባሉ . . .ረዳት የሌለውን ለመያዝ ይሸምቃሉ፤ ድኻውንም አፈፍ አድርጎ በወጥመዱ ይጐትታሉ” (መዝ. 10፡9) በማለት ሰለሁኔታው አስከፊነት ይገልፃል። በእዚህ አደን ምክንያት ድሆች ተጠምደዋል፣ ተይዘዋል፣ ለባርነት ተዳርገዋል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ተስፋ ቆርጠዋል፣ ከመጠን በላይ በሆነ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል። በአጭሩ በፊት ለፊታችን የምናያቸው ድሆች ስለእነርሱ መጥፎ ነገር የሚነገር እና ለተጋነን መከራ የተዳረጉ ናቸው። ሁሉም ድሆች በተጽእኖዎች ሥር የወድቃሉ ድምጻቸው በህብረተሰብ ውስጥ እንዲሰማ እንኳን አይደረግም።

3.     የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ አቀማመጥ በፍትህ መዛባት፣ በችግረኞች እና በስቃይና መከራ ውስጥ ያሉትን ድሆች በተመለከተ በሐዘን ያናገራል። በተመሳሳይም መልኩ ልብን በሚነካ መልኩ ድሃ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ትርጉሙን ይናገራል፣ እነርሱ "በእግዚአብሔር ላይ እምነታቸውን የጣሉ" በእርግጠኝነት እርሱ ፈጽሞ እንደማይተዋቸው እርግጠኛ የሆኑ ናቸው በማለት ይናገራል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ድሆች በእግዚኣብሔር የሚያምኑ ናቸው በማለት ይናገራል! ዘማሪው ዳዊት ለዚህ ምክንያት መልስ ሲሰጥ እነርሱም ጌታን በሚገባ "ያውቁታል” በማለት ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ እንዲህ ዓይነቱ "እውቅና" የግል ስሜትን እና የፍቅር ግንኙነትን ያካትታል።

በሚያስደንቅ እና ፈጽሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ እግዚኣብሔር ከድሆች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ይገልጻል። የእሱ የመፍጠር ኃይል ከሁሉም ሰብዓዊ ፍላጎቶች በላይ የሆነና እያንዳንዱ ግለሰብ "በማስተዋል” እንደ ሚመለከት ያሳያል። ይህም በጌታ ላይ ያላቸው መታመንን ተስፋ እናድይቆርጡ እና በእየጊዜው ተስፋቸው እየለመለመ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል። ድሃዎች እግዚአብሔር ሊተዋቸው እንደማይችል ያውቃሉ፣ ስለዚህ እነሱ ሁልጊዜ በሚያስታውሳቸው አምላክ ፊት ናቸው። የእግዚያብሄር እርዳታ አሁን ካለው የስቃይ ሁኔታ ባሻገር በመሄድ ጥናካሬን እና የሰውን ልብ የመቀየር ከእዚያምም ወደ ነጻነት መንገድ የመምራት አቅም እንዳለው ይታወቃል።

4.     መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በድሆች ፈንታ ስለሚወስደው እርምጃ በተደጋጋሚ ይናገራል። እርሱ ጩኸታቸውን "ይሰማል" እና "ያድናቸዋልም"፣ እርሱ ይከላከልላቸዋል እንዲሁም ይጠብቃቸዋል. እርሱ "ይታደጋቸዋል"  "ያድናቸዋልም"! በእርግጥ ድሆች በስቃያቸው ውስጥ እግዚአብሔር ግድየለሽ ሆኖ ወይም ዝም ብሎ አይመለከታቸውም። እግዚአብሔር ፍትህን የሚሰጥና የማያሳፍር ነው (መዝ 40:18; 70: 6); እርሱ የሚረዳቸው መሸሸጊያቸው ነውና መዝ 10፡4)።

በሌሎች ትክሻ ላይ ተንጠላጥለው ያገኙትን ሐብት እንዳይነካ እና ደህንነቱ አስተማማኝ በሆነ መልኩ የጠጠበቀ ይሆን ዘንድ በማሰብ ማንኛውንም ዓይነት የግድግዳ መስመሮች መገንባት እና በሮችን ለመዝጋት በከንቱ እንደክማለን። በዚህ ዓይነት መንገድ ለዘላለም ልንጓዝ አንችልም። በነቢያት እንደተገለጸው "የእግዚአብሔር ቀን" (በአሞጽ 5:18፣ ኢሳ፡ 2-5፣ ኢዩሄል 1-3) በአገራት መካከል የተፈጠሩትን መሰናክሎች በማፈራረስ የጥቂት ሰዎች እብሪትን በብዙ ሰዎች ሕበረት ይተካዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እየገጠማቸው ያለው የማግለል ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል አይችልም። ጩኸታቸው በፍጥነት እየጨመረና መላውን ምድር ሊያዳርስ ይችላል። አባ ሚሪሞ ማዞላሪ የሚባሉ ካህን “ድሆች በፍትሕ መጓደል ላይ የማያቋርጥ ተቃውሞ አላቸው፣ ድሆች እንደ ባሩድ ዱቄት ናቸው፣ በእሳት ከተያያዙ ዓለም ይፈነዳል” ይሉ ነበር።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

15 November 2019, 16:40