ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ጃፓን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት የቪዲዮ መልዕክት አስተላለፉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ከመጪው ኅዳር 9-16/2012 ዓ.ም ድረስ ወደ ታይላንድ እና ጃፓን በቅደም ተከተል እንደሚያቀኑ ተገልጿል። ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊትም ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው ለሚሄዱባቸው አገሮች የቪዲዮ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ይታወቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ለጃፓን ሕዝቦች ያለኝን ወዳጅነት መግለጽ እወዳለሁ” ባሉት የቪዲዮ መልዕክታቸው የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ለሐዋርያዊ ጉብኝቴ የተመረጠው መርህ ሃሳብ ‘መላውን ሕይወት ከአደጋ መከላከል’ የሚል ነው። በልባችን ውስጥ ያለውን የርህራሄ ስሜት በማድመጥ፣ ስነ ምግባራዊ እሴቶችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅ ያስፈልጋል። የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶችን እንዳይጣሱ ጥበቃን በማድረግ፣ የሕዝቦችን ሰላማዊ ሕይወት የሚያናጉ የጦርነት እና የአመጽ ፈተናዎችን ዓለማችን መቋቋም ያስፈልጋል።

ጦርነት የሚያስከትለውን ስቃይ የጃፓን ሕዝብ በሚገባ ያውቀዋል። አውዳሚ የኒውክሌር ጦር መሣርያ ጥቃት በሰው ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደገም ከጃፓን ሕዝብ ጋር በመሆን በጸሎት እተባበራለሁ። የኒውክሌር ጦር መሣርያን መጠቀም በሰው ሕይወት እና በፍጥረት ላይም ጥፋትን የሚያስከትል ግብረ ገብ የጎደለው ተግባር ነው።

የጋራ ውይይት ባሕል በሕዝቦች መካከል በተለይም በሐይማኖት ተቋማት መካከል ወንድማማችነትን  ለማሳደግ፣ ልዩነቶችን ለማስወገድ፣ ሰዎች ተከባብረው እና ተቻችለው በመኖር እያንድንዱ ሰው የእድገት  ተጠቃሚ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጃፓን ሕዝብ በሚገባ ያውቀዋል።

ወደ ጃፓን የማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝቴ የጃፓን ሕዝብ እርስ በእርስ ተከባብሮ በሕብረት ለመጓዝ፣ ወደ ኋላ የማይታጠፍ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲገኝ በማድረግ ብርታትን እንደሚሰጣችሁ እተማመናለሁ። በሕዝቦች መካከል እውነተኛ ሰላም መውረድ መልካምነቱ ወደ ኋላ የማይታጠፍ እና ጠንካራ በመሆኑ ነው።

ወደ ጃፓን በማደርገው ሐዋርያዊ ጉብኝቴ አማካይነት እጅግ ውብ የሆነውን የጃፓን የተፈጥሮ ሃብት የማየት እድል እንደሚኖረኝ እርግጠኛ ነኝ። ይህን ዕድል በመጠቀም ለጋራ መኖሪያ ለሆነው ምድራችን አስፈላጊው ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲደረግለት የሚል ሃሳቤን ከእናንተ ጋር የምካፈልበትን ዕድል አገኛለሁ።

ወደ ጃፓን የማደርገውን ሐዋርያዊ ጉብኝቴን ፍሬያማ ለማድረግ በርካታ ሰዎች የበኩላቸውን ጥረት እና ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን በመገንዘብ ለሚያበረክቱት መልካም ተግባር ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የሐዋርያዊ ጉብኝቴ ቀናት እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ እና ደስታ የተሞሉ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ። ሁላችሁንም በጸሎቴ እንደማስታውሳችሁ በማረጋገጥ እናንተም በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ እና ጃፓን የሚያደርጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው የቪዲዮ መልዕክታቸውን ለጃፓን ሕዝብ ልከዋል።

“መላውን ሕይወት ከአደጋ መከላከል” በሚለው መርህ መልዕክት በኩል ቅዱስነታቸው ወደ ጃፓን በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የሰላም አስፈላጊነትን የሚመሰክሩ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ዘገባው አክሎም ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በአቶሚክ ቦምብ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሁለት የጃፓን ከተሞችን፣ በሂሮሽማን እና ናጋሳኪን የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል። በጉብኝታቸው ወቅት የአደጋው ሰለባ ከሆኑት የፉኩሺማ ነዋሪዎች ጋርም የሚገናኙ መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 November 2019, 14:38