ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቶኪዮ ከወጣቶች ጋር በተወያዩበት ጊዜ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቶኪዮ ከወጣቶች ጋር በተወያዩበት ጊዜ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጃፓን ወጣት ትውልዷን በጽኑ የምትፈልግ መሆኗን ገለጹ።

32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝትታቸውን በታይላንድ እና ጃፓን ውስጥ ለማድረግ ወደ ሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች የተጓዙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ የጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር በሆነችው ጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ በሚገኝ የፍልሰታ ማርያም ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት መፈጸማቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ለተገኙት በርካታ ወጣቶች ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ስነ ስርዓት ወቅት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ የጃፓን ወጣቶች በአገራቸው በጃፓን እና በመላው ዓለምም የሚፈለጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቶኪዮ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የፍልሰታ ማርያም ካቴድራል ውስጥ በቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ላይ በጃፓን ውስጥ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ባሕሎችን እና የእምነት ተቋማትን የሚወክሉ ወጣቶች ተካፋይ ሆነዋል። ከቡዳ እና ከካቶሊክ እምነቶች እንዲሁም በአገሪቱ ከሚገኝ የስደተኛ ማሕበረሰብ የተወጣጡ ወጣቶች በስነ ስርዓቱ መካከል ምስክነታቸውን አቅርበው ያደረባቸውን ፍርሃት ለቅዱስነታቸው በመግለጽ ምክርን እንዲለግሱላቸው ጠይቀዋል። ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክርን ከጠየቁት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ሚኪ ሲናገር በአገሩ ወጣቶች መካከል የሚታየው ዕለታዊ የኑሮ ውድድር ከእግዚአብሔር የሚገኘውን የደስታ ሙላት ለመቀበል ያላቸውን ዕድል እንደቀነሰ እና ከወጣቶችም በኩል የሚታየው ስንፍና እየጎዳቸው መምጣቱን ገልጿል። ምስክርነታቸውን ከገለጹት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ማሳኮ በወጣቶች መካከል ጉልበተኝነት እና ራስን ማጥፋት ተግባር እያደገ መምጣቱን ገልጾ ይህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በሚጠቀሙ ወጣት ተማሪዎች መካከል ጎልቶ ይታያል ብሏል። ምስክርነታቸውን ካቀረቡት ወጣቶች መካከል የፊሊፒን ስደተኛ ቤተሰብ ተወላጅ የሆነች ወጣት ለቅዱስነታቸው ባቀረበችው ጥያቄ በዓለም ዙሪያ እየተሰራጨ ያለውን አድልዎ እና ጉልበተኝነትን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ እንዲያሳዩ ጠይቃለች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶችን ለጥያቄዎቻቸው አመስግነው በርካታ ወጣቶች እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን ለማቅረብ ድፍረትን በማግኘት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጉልበተኝነት በሕይወት መካከል የሚመጡትን አዳዲስ ገጠመኞች ተቀብሎ ለማስተናገድ ያለንን ጥንካሬን እና በራስ መተማመንን የሚጎዳ ማሕርይ እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው ማስወገጃ መንገድም ወጣቶች በመሰባሰብ ይህ መጥፎ አመል እንዲያበቃ በጋራ በመነሳት ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የጉልበተኝነትን ስሜት ለሚያሳዩ ወጣቶች የተሳሳተ አካሄድ መሆኑን ያለ ፍርሃት ማስረዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ፍርሃት የመልካም ባሕርይ እንቅፋት መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው ይህ ብቻም ሳይሆን ፍርሃት የፍቅር እና የሰላም እንቅፋትም ነው ብለዋል። ሐይማኖቶች በሙሉ የሚያስተምሩት ይቅርታን፣ መግባባትን እና ምሕረትን እንጂ ፍርሃትን፣ ልዩነትን እና አመጽን አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስም ለተከታዮቹ ያስተማረው ፍርሃት እንዳይዛቸው ነው ብለዋል። ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ፍርሃትን ያስወግዳል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከማሕበረሰብ መካከል መገለል፣ መሰቃየት እና ለስቅላትም መደረስ ምን ማለት እንደሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ያውቀዋል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቱ እንግድነትን፣ ስደተኝነትን እና ብቸኝነትን ተለማምዷል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሕይወት መካከል ያጋጠሙንን መጥፎ ገጠመኞቻችንን እና ችግሮቻችንን ወደ ፍቅር በመለወጥ ዓለምን መለወጥ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። አንድ ግለ ሰብ፣ ወይም ማሕበረሰብ ወደ ከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ሊደርስ ቢችልም ትክክለኛውን የሕይወት ትርጉም ያልተገነዘበ ከሆነ ምንም አላደገም ብለው በወጣቶች መካከል የሚታየው ጉልበተኝነት የሕወትን ክብር እና ታላቅነት ካለመገንዘብ የተነሳ ነው ብለዋል።

መንፈሳዊ ድህነትን ለመዋጋት ተጠርተናል ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህ ረገድ ወጣቶች ትልቅ ሚናን መጫወት ይችላሉ ብለው፣ ወጣቶች በሚያደርጓቸው ምርጫዎች አማካይነት ትላልቅ ለውጦችን ማምጣት ይችላሉ ብለዋል። በሕይወት ውስጥ ይህን መገንዘብ ማለት ብዙ ንብረትን ማፍራት እና ማግኘት ሳይሆን ያለንን ትንሿን ሃብት ከሌሎች ጋር መጋራት ነው ብለዋል። ለምን እንደምንኖር ሳይሆን ከማን ጋር እንደምንኖር ማወቅ ነው ብለዋል። በወጣቶች መካከል ጓደኝነት እንዲያድግ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ከሌሎች ጋር መልካም ሕይወት እንዲኖረን ያሉንን መንፈሳዊ እሴቶች ከሌሎች ጋር መጋራት እንደሚያስፈልግ ወጣቶችን መክረዋል። ለምታልሙት መልካም ህልም በቂ ሥፍራን በመስጠት በምትቀዳጁበት ጊዜም የሚሰጣችሁን የደስታ ብዛት ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

25 November 2019, 15:51