ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሲያመሩ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሲያመሩ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታይላንድ ሕዝብ መካከል ወዳጅነት የበለጠ እንዲያድግ ተመኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህዳር 9 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ በሁለት የእስያ አገሮች የሚያደርጉትን 32ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ትናንት ህዳር 10/2012 ዓ. ም. መጀመራቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለቱን የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮች የሆኑትን ታይላንድ እና ጃፓን የሚጎበኙ መሆናቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው የ32ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ አገር ወደ ሆነችው ታይላንድ ሲደርሱ በባንኮክ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተገኙት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ጋር፣ የተለያዩ ሐይማኖት መሪዎች፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት እና የባንኮክ ከተማ ሀገረ ስብከት  ምዕመናን ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ታይላንድ እና ጃፓን ለሚያደርጉት 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በወጣው መርሃ ግብር መሠረት ቅዱስነታቸው ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች እና ለሐይማኖት መሪዎች በአገሪቱ ቤተመንግሥት ተገኝተው ንግግር አድርገውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ለተገኙት በሙሉ ባሰሙት ንግግር፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በታይላንድ ለማድረግ የነበራቸው ምኞት እውን መሆኑ፣ በተፈጥሮ ሃብት የታደለችውን፣ ረጅም ዘመናትን ባስቆጠሩት መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ባለቤት የሆነችውን ታይላንድ፣ በሕዝቦ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአንድነት እና የወዳጅነትን ባህል በአካል ተገኝተው ለመመልከት ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።     

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በጀኔራል ፕራዩይ ቻን ኦሸ በኩል ለተደረገላቸው የክብር አቀባብል እና በብሔራዊ ቤተመንግሥት ላደረጉላቸው የእንኳን ደህና መጡ ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩን አመስግነዋል። ቅዱስነታቸው በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት የታይላንድ ንጉሥ ግርማዊነታቸው ራማ 10ኛን እና ንጉሣዊ ቤተሰብን የሚጎበኙ መሆናቸውን ገልጸው ለግብዣው ግርማዊነታቸውን አመስግነዋቸዋል።

በቤተመንግሥቱ ከተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት እና የሕዝባዊ ማሕበራት መሪዎች ጋር ሰላምታን ለመለዋወጥ እንዲሁም ንግግር እንዲያደርጉ ለተሰጣቸው ዕድል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ በቤተመንግሥቱ ውስጥ በተገኙት ተወካዮች በኩል ለመላው የታይላንድ ሕዝብ ሰላምታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በብሔራዊ ቤተመንግሥት ለተገኙት የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅርቡ በታይላንድ የተካሄደውን ሰላማዊ ምርጫ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምርጫው በዴሞክራሲዊ ሂደት በመከናወኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ወደ ታይላንድ ከመድረሳቸው በፊት በቪዲዮ መልዕክታቸው እንደገለጹት ሁሉ በታይላንድ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ለተባበሩት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ዛሬ የምንገኝበት ዓለም የሁላችን ትብብር የሚጠይቅ፣ መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብን የሚያካትት ነው ብለው፣ ስለሆነም በሕዝቦች መካከል ዓለም አቀፍ ፍትሕን እና አንድነትን ለማምጣት የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል። ታይላንድ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች የሊቀ መንበርነትን ሚናዋን በማገባደድ ላይ መሆኗን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በአካባቢው አገሮች የሚታዩትን ዘርፈ ብዙ ርዕሠ ጉዳዮች፣ ከእነዚህም መካከል ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ርዕሠ ጉዳዮችን በጋራ ተመልክተው ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የአካባቢው አገሮች ሕብረት የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ታይላንድ በብዙ ጎሳዎች መካከል መቻቻልን እና በሰላማዊ አብሮ የመኖርን ባሕል መገንባት አስፈላጊነትን ከረጅም ጊዜ አንስቶ ታውቀዋለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለተለያዩ ባህሎች፣ የሃይማኖት ቡድኖች እና አስተሳሰቦች አድናቆትንም  በማሳየት የምትታወቅ አገር መሆኗን ገልጸዋል። የደረስንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የኤኮኖሚውን ዘርፍ ብቻ በመመልከት የሕዝቦችን ሕብረት እና በሰላም አብሮ የመኖርን ባሕል ለማሳነስ ወይም ለማጥፋት እንደሚከጅል ቅዱስነታቸው በንግግራቸው አስረድተዋል። ሆኖም የሕዝቦች በሰላም ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር ባሕል ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የምንፈልጋትን እና የምንመኛትን ዓለም ለመገንባት ያግዘናል ብለዋል።

በታይላንድ የሚገኙ ባህላዊ ሃይማኖቶች በማሕበራዊ ሕይወት በንቃት እንዲሳተፉ የሚያደርግ የማህበራዊ ሥነ ምግባር ኮሚሽን መቋቋሙ ደስ አሰኝቶኛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህም ለሕዝባቸው የሚያበረክቱት መንፈሳዊ እሴቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል። ይህን አስመልክተው ማሕበራዊ ሰላምን፣ ፍትሕን እና ሁሉ አቀፍ ማሕበረሰብን ለመገንባት በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይት መኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከቡዳ እምነት መሪ ጋር ለመወያየት እቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል። በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም በታይላንድ ሕዝብ መካከል አንድነትን እና ፍቅርን ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ ብለው የሚያደርጉትን ጥረቶች ለመደገፍ ፍላግት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። የታይላንድ ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ የበርካታ ወንድሞች እና የእህቶች ስቃይ ለማስወገድ፣ የጭቆና ቀንበርን አውልቆ ለመጣል፣ ድህነትን ለመቀንስ አመጽን እና ኢፍትሃዊ ስርዓትን ለማስወገድ ያደረጓቸው ጥረቶች በሙሉ ጥሩ ምሳሌ ሆነውናል ብለዋል። ታይላንድ የነጻነት አገር መሆኗን የተናገሩት ቅዱስነታቸው እንደምናውቀው ነጻነት የሚገኘው አንዱ ለሌላው ሲጨነቅ እና ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት ለማስወገድ የጋራ ሃላፊነት ሲኖር ነው በማለት አስረድተዋል። ይህ ከተስተካከለ ግለሰቦች እና ማህበረሰቦች ጥራት ያለውን የትምህርት እና የሥራ ዕድል፣ እንዲሁም በቂ የጤና እንክብካቤን የማግኘት ዕድል የሚረጋገጥ በመሆኑ የሰው ልጅን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ዘላቂ ልማትን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በዘመናችን ከሚታዩ ማሕበራዊ ቀውሶች መካከል ስደት አንዱ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስደት ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ፣ ከአገር ወደ አገር ያሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የትውልድን ሥነ ምግባር ከሚመለከቱ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል። በሕዝቦች ላይ የደረሰው የስደት ቀውስ በቀላሉ መታየት የለበትም ያሉት ቅዱስነታቸው የታይላንድ ሕዝብም የአጎራባች አገሮች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ልምድ አለው ብለዋል። ስደትን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የችግሩን አሳሳብነት በመገንዘብ ሃላፊነት በተመላ መልኩ ስርዓትን እና ሕግን የተከተለ ተግባር እንደሚያከናውን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ እያንዳንዱ አገርም በሰደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የተደቀነውን አደጋ እና ብዝበዛ በማስወገድ፣ ሰብዓዊ መብታቸውን እና ክብራቸውን በመጠበቅ፣ ለቤተሰቦቻቸውም ነጻነትን እና የተስተካከል ኑሮን በማዘጋጀት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አደራ ብለው ይህ መልካም ምሳሌ ለስደተኞች ብቻ ሳይሆን ለመላው ማሕበርሰባችን ይተርፋል ብለዋል።

በአመጽ የመቁሰል፣ የመበዝበዝ፣ የመደፈር እና የባርነት አደጋ ያጋጠሟቸውን ሴቶች እና ሕጻናት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የታይላን ሕዝብ በእነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ ለወደቁት የማሕበርሰብ ክፍሎች በግልም ሆነ በጋራ እርዳታቸውን ላቀረቡት ድርጅቶች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።  ዘንድሮ 30 ዓመቱን ለሚያከብረው የልጆች እና የጎልማሶች መብቶች ድንጋጌ ሰላሳኛ ዓመት መታሰቢያ በሚከበረው በዚህ ዓመት የልጆቻችን ደህንነት እና ማህበራዊ እድገታቸውን የመጠበቅ አስፈላጊነት እንድናስታውስ ተጠርተናል በማለት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 27/2019 ዓ. ም. ለተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ለሕጻናት የትምህርት ዕድል ማሳደግ፣ የአካል የስነ ልቦና እና መንፈሳዊ እድገትን ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ይህም ለወደ ፊት የተስተካከለ ሕይወት ጥሩ መንገድን የሚያመቻችላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በጠቃለሉበት ወቅት ማሕበረሰባችን ከምን ጊዜም በበለጠ የእንግዳ ተቀባይነት፣  ማሕበራዊ ፍትህ፣ አንድነት እና ወንድማማችነት ባሕል እንደሚያስፈልገው ገልጸው እያንዳንዳችሁ በምትችሉት አቅም ለጋራ ጥቅም የቆመ አገልግሎት ለአገራችሁ ማበርከት ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ለእያንዳንዳችሁ የተሰጣችሁን ተልዕኮ በፍሬያማነት እንድትወጡት በጸሎት የተሞላ መልካም ምኞቴን በመግለጽ በዚህች አገር ላይ፣ በመሪዎቿ እና በሕዝቦቿ የእግዚአብሔር ቡራኬ እንዲወርድ ተመኝተው፣ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው እና ቤተሰብ ወደ ጥበብ፣ ፍትህ እና ሰላም እንዲመራ ጸሎቴን አቀርባለሁ በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 November 2019, 16:06