ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ደቡብ ሱዳንን በጋራ ለመጎብኘት ማሰባቸውን አስታወቁ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ትናንት ህዳር 3/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ባደረጉት ውይይታቸው በክርስቲያኖች ላይ በሚደርስ ስቃይ፣ በዓለም አቀፍ ቀውሶች እና ደቡብ ሱዳንን በጋራ መጎብኘት በሚሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አንድሬያ ደ አንጀሊስ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ለደቡብ ሱዳን ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ መሆኑን የገለጸው የቫቲካን ዜና ሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ደቡብ ሱዳንን በጋራ ለመጎብኘት ሃሳብ ያላቸው መሆኑን በውይይታቸው ገልጸዋል። ከውይይታቸው በኋላ ይፋ የተደረገው የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስረዳው በደቡብ ሱዳን የተቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት በሚቀጥሉት መቶ ቀናት ውስጥ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት አገሪቱ የደረሰችበት የፖለቲካ ሁናቴ ዕድሉን ሊያመቻች እንደሚችል ሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች መወያየታቸውን አስታውቋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ዌልቢ ትናንት ከሰዓት በኋላ ባደረጉት ውይይት ላይ በሮም የአንግሊካን ማዕከል ዳይሬክተር እና በቅድስት መንበር የአንግሊካን ሕብረት ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ያን ኤርኔስት መገኘታቸው ታውቋል። ከፍተኛ የሐይማኖት መሪዎች በጋራ ባደረጉት ውይይታቸው የዓለም ክርስቲያኖች የሚገኙበት ሁኔታ፣ የዓለማችንን ቀውስ እና በከፍተኛ ችግር ላይ የምትገኝ የደቡብ ሱዳን ጉዳይን መመልከታቸው ታውቋል።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ወደ ደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ላማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ጋር የተደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነት፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሆነው የተመረጡት መስከረም 4/2005 ዓ. ም. መሆኑ ሲታወቅ በተመሳሳይ ወር 2005 ዓ. ም. ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢም የካንተርቤሪ ሊቀ ጳጳስ ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል። ሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙትም በሰኔ ወር 2005 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። ቀጥለውም መስከረም 10/2009 ዓ. ም. በጣሊያን አሲዚ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የሰላም ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ መገናኘታቸው ይታወሳል።

ለሱዳን የተሰጥ ክፍተኛ ትኩረት፣

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት በጋራ ከሚያዚያ 2-3/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሁለት ቀን ሱባሄ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ሱባሄ የተካሄደው  በቫቲካን በሚገኘው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የእርሳቸው የቅርብ የሥራ ባለሟሎች በሚጠቀሙበት በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን የሱባሄው ዋና ዓላማ ደግሞ በአገሪቷ እየተካሄደ የነበረው የእርስ በእስር ግጭት ተወግዶ ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲፈጠር ያደርጋል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ስምምነት እ.አ.አ በግንቦት 12/2019 ዓ.ም ላይ በባለድርሻ አካላት በይፋ ስምምነት እንደሚፈርሙ፣ ይህ ሱባሄ የአገሪቷ ባለስልጣናት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመንፈሳዊ ሕይወት እገዛ እውን እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ እና ዓላማውም ከቤተክርስቲያን በኩል በቀረበው ሃሳብ መሠረት የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር ሆነው በጸሎት እና በአስተንትኖ የሚተባበሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር፣ በመካከላቸው የመከባበርን እና የመተማመንን መንፈስ ለማሳደግ፣ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ሰላም እና ብልጽግና የተጣለባቸውን ሃላፊነት በጋራ በመሥራት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ የሁለት ቀን ሱባኤ እንደነበር ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 November 2019, 16:26