ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለህዳር ወር ያሉትን የጸሎት ሃሳብ ይፋ አደረጉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለምዕመናን በሚያስተላልፉት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸው ለመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች እርቅ እንዲወርድ በያዝነው የህዳር ወር መላው ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለውናል። በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ በሚገኙ የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ፍሬያማ ውይይቶችን በማድረግ ለሰላም  በርትተው እንዲሠሩ ማሳሰባቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ የላከችልን ዘገባ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል ሰላምን ለማውረድ የእውነተኛ ውይይት ፍላጎት ሊኖር ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው በአካባቢው አገሮች መካከል እርቅን ለማድረግ የጋራ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው የህዳር ወር የጸሎት ጥሪያቸውን ለመላው ዓለም ክርስቲያኖች በቪዲዮ መልዕክት አማካይነት ይፋ ማድረጋቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።  በመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች የሚገኙ የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነቶች በመካከላቸው ያለው የረጅም ዘመናት መንፈሳዊ ግንኙነት ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ የሚቻለው የጋራ ውይይቶችን በማድረግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል 93% የእስልምና እምነት ተከታይ፣ 5% የክርስትና እምነት ተከታይ፣ 2% በእስራኤል የሚገኙ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ለሰው ልጆች ፍቅር ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና ወደ ዓለም ሁሉ የተሰራጨው ከመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች መሆኑን አስረድተው፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ከአይሁድ እምነት ተከታዮች እና ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ለይቅርታ፣ ለእርቅ እና ለሰላም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የጋራ ውይይት ባሕልን ማሳደግ ያስፈልጋል፣

በጋራ ውይይት ላይ ከፍተኛ እምነትን የጣሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር 27/2011 ዓ. ም. በአቡዳቢ ከተማ ከፍተኛ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ባደረጉት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የዓለም ሰላም እና የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት መፈረማቸው ይታወቃል። በሁሉም የእምነት ተከታዮች መካከል የጋራ ውይይትን ማድረግ ማለት በመካከላቸው የሚገኙትን በርካታ መንፈሳዊ፣ ሰብዓዊ እና ማሕበራዊ እሴቶችን በጋራ መካፈል መሆኑን ያስረዳው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ጥሪ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት በሃይማኖቶች መካከል ያለው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ሃብት እንዲያድግ የሚያደርግ መሆኑን መልዕክታቸው አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተማ ወደ ሆነችው ባሪ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሰው የቅዱስነታቸው የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሰሙት ንግግር “እርስ በእርስ መደጋገፍ፣ ወንድማዊ ውይይቶችን በማድረግ፣  የአንድነትን አስፈላጊነት በሚገባ  በመረዳት፣ ልዩነቶቻችን ሳንፈራ እና ሳንሸማቀቅ ሰላማዊ ውይይቶች በመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች መካከል መከናወን እንዳለበት ማሳሰባቸውን አስታውሶ፣ ሃይልን በመጠቀም እና ግድግዳን በመገንባት የሚመጣ የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ዘላቂ ሰላም ሊመራ አይችልም ማለታቸውንም አስታውሷል። ጽሕፈት ቤቱ በማከልም መደማመጥ የሰፈነበት ወይይት ወደ ሰላም መንገድ የሚመራ በመሆኑ አብሮ በመጸለይ እና አብሮ በመሥራት በአመጽና በግጭት ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት በሕብረት መጓዝ እንደሚያስፈልግ፣ በጎ ፈቃድ ካላቸው የእምነት ተቋማት መሪዎች የሚቀርቡትን መልካም ሃሳቦች ለማዳመጥ ዝግጁዎች መሆን ያስፈልጋል ማለታቸውን የቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የክርስትና እምነት የተወለደው በመካከለኛው የምስራቅ አገር ውስጥ ነው፣

የመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች ሕዝቦችን በጸሎት እንድናስታውስ አደራ ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የህዳር ወር የጸሎት ጥሪ ያስታወሱት፣ የዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፣ መካከለኛው ምሥራቅ የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነቶች የተወለዱበት፣ የነቢያት አገር፣ የአብርሐም፣ የይስሐቅ እና የያዕቆብ የትውልድ አገር፣ ኢየሱስ ክርስቶስም የተወለደበት አገር መሆኑን አስታውሰዋል። የቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ በማከልም አካባቢው ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት እና ክርስቲያኖች እስካሁንም የሚገኙበት ሥፍራ መሆኑን ገልጸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የህዳር ወር የጸሎት ጥሪ፣ ጸሎት ከማቅረብ በተጨማሪ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚገኙትን የስርዓተ አምልኮ ባሕሎችንም እንድናስታውስ የሚጠይቅ መሆኑን ክቡር አባ ፍሬደሪክ አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 November 2019, 14:59